ኢትዮጵያና አሐዱ ሬድዮ – በጥበቡ በለጠ አንደበት

0
1474

‹የኢትዮጵያውያን ድምጽ› የሚለው ሐሳብ የተነሳበት ዓላማ እንዲሁም የሚደርስበት ግብ እንደሆነ ያስቀመጠ፣ ያለማቋረጥ ስለኢትዮጵያ በመሥራት የተጠመደ የሬድዮን ጣቢያ ነው፤ አሐዱ ሬድዮ። 94.3 ሜጋ ኸርዝ ላይ የሚገኘው ይህ ጣቢያ ላለፉት ሦስት ዓመታት አድማጮቹን ቤተሰብ እያለና ቤተሰብ አድርጎ የዘለቀ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜም ብዙ ቤተሰብ፣ ሰፊ ተደማጭነትና ተዓማኒነትን አትርፏል። ትላንት አርብ ሐምሌ 17 ቀን 2012ም የ3ኛ ዓመት ልደቱን ሻማ ለኩሷል።

ይህን የሬድዮ ጣቢያ ከምሥረታው ጀምሮ በዋና አዘጋጅነትም በመምራት ደግሞ ጥበቡ በለጠ ይገኛል። በቅንነት፣ በትጋትና በሙያተኝነቱ ይታወቃል። በሠራባቸው አዲስ ዜና እንዲሁም ሰንደቅ የተሰኙ ጋዜጣዎች ላይ ሊወሱ ከሚችሉ ኹነቶች ባለፈ በጋዜጦቹ ባህል፣ ታሪክና ኪነጥበብ ላይ በብዙ ሠርቷል።

ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችን ሲያዘጋጅ የኢትዮጵያ ባለውለታዎችን ታሪክና ሥራዎች ከትቦ አኑሯል። ‹ንባብ ለሕይወት› የተሰኘው የመጻሕፍት አውደ ርዕይ የንባብ አምባሳደር ከመሆኑም በላይ ከአዘጋጆቹም አንዱ ነው። ጥበቡ ለሚቀርብለት የትኛውም ጥያቄ ማሰሪያና መቋጫው አገሩ ኢትዮጵያ ናት። እንደሚዘምርላቸው የአገር ባለውለታዎች ሁሉ እርሱም ለአገሩ የራሱን ትልቅ ድርሻ በእውቀት፣ በእድሜና በአቅም እየሰጠ ይገኛል።

ጥበቡ በለጠ የአሐዱ ሬድዮን ሦስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ስለጣቢያው ምሥረታና ጉዞ እንዲሁም እርሱም ስላለፈባቸው መንገዶች ከብዙ በጥቂቱ በማንሳት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

በቅድሚያ እንኳን ለአሐዱ ሬድዮ ሦስተኛ ዓመት በደኅና አደረሳችሁ። አሐዱ ሬድዮ አሐዱ ወዳለበት ጊዜ መለስ እንበልና ሐሳቡ እንዴት መጣ፣ ወደሥራ የተገባበት ሂደትስ ምን ይመስል ነበር ከሚለው እንነሳ?
የአሐዱ ሬድዮ ዋናው ድርጅት ኤዲ-ስቴላር (ED Stelar Broadcasting) ይባላል። ኤዲ-ስቴላር ከዛሬ አስራ ስምንት ዓመታት ጀምሮ በሚድያው ኢንዱስትሪ [ሚድያውም በርካታ የሰው ኃይል ስለሚይዝ በውጪ አገራት እንደ ኢንዱስትሪ ነው የሚቆጠረውና] እንደቢዝነስ ብዙ የሚሠራበት እንደሙያም ብዙ የሚበረከትበት ስለሆነ ብሎ እዛ ላይ ለመሥራት ጥረት ያደርግ ነበር። ሌሎች ተያያዥ የንግድ ድርጅቶች አሉት።

በወቅቱ ደግሞ እዚህ አገር ቴሌቭዥን እና ሬድዮ መክፈት በጣም አስቸጋሪ ነው። ከመንግሥት አንጻር ፈቃድ የለም። አይገኝም ማለት ይቻላል። ችግሩም እስከ አሁን ቀጥሏል፤ እንደ ልብ ሬድዮ ጣቢያ መክፈት አይቻልም። በጣም ትልልቅ ጨረታዎች የሚደረጉበት ነው እና በዓመታት ለተወሰኑ ድርጅቶች ይሰጣል።

ከዚህ ሁሉ ተብሎ በተሰጣቸው ጣቢያዎች ላይ አየር ሰዓት በመውሰድ እንደ አውቶሞቲቭ ጆርናል ዓይነት ፕሮግራሞችን አውቶሞቲቭ ዘርፍን ማስተዋወቅ፣ ልዩ ልዩ የመንገድ ደኅንነትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያስተዋውቁ ፕሮግራሞች ሲሠራ ቆየ፣ ስቴላር። የራሱን ፕሮግራሞች ራሱ ነበር ፕሮድዩስ የሚያደርገው፣ የስቱድዮ ግንባታ ላይ ነበር። የመጀመሪያው ጨረታ ተከናውኖ ካለፈ በኋላ እንዲወድቅ ተደርጎም ነበር። ሌሎች ኹለት ጣቢያዎች ተሰጣቸው።

እንደገና ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ጨረታ ውስጥ ገብቶ የመጀመሪያ ሬድዩ ጣቢያ ሕልሙን እንዲያገኝ ሆነ። የሚድያ ኢንቨስትመንት በተለይ ብሮድካስቲንግ ወጪው ብዙ ነው። ይህን ለማድረግ ድርጅቱ ተያያዥ የሚሠራቸው ሥራዎች ስለነበሩ፣ ወደ ውጪ ምርቶችን መላክና ከውጪ ማስገባት፣ የተለያዩ ክዋኔዎችንና አውደ ርዕይ ስለሚያዘጋጅም የአቅም ችግር የለበትም ነበር። ሚድያውን እንዴት አድርጌ ይዤው እሄዳለሁ የሚለው ነው ችግሩ።

የሬዲዮ ፈቃዱ ከተሰጠው በኋላ ምን ዓይነት የሬድዮ ጣቢያ ይሁን የሚለው ነበር ቀጣዩ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰኑ የሬድዮ ጣቢያዎች አሉ፣ ከእነርሱ ጋር ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ሆኖ ሲመጣ ምን ዓይነት ፕሮግራም ይዞ ይምጣ የሚል ጥያቄ ነበር። በዚህ ላይ ብዙ ውይይቶችና ጥናቶች ተደርገው መልሰነዋል። ያሉት/የነበሩት ሬድዮ ጣቢያዎች የሚሠሩትን ደግሞ ለመሥራት አልመጣም። ይልቁንም በተለየ አተያይ ሚድያዎቻችን ውስጥ ባሉ ክፍተቶች እንዴት አድርን እንግባና የተሻለ አማራጭ ሆነን እንምጣ የሚል ነው።

በኢትዮጵያ በስፋት ተግባር ላይ ያልዋለና ያልተነገረው የኢትዮጵያ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ችግር ውስጥ የወደቀበት በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። እናም አሐዱ ይሄ ሚድያዎቻችን ላይ በስፋት የማይነሳውን የኢትዮጵያን ማንነትና ታሪክ አጽንኦት ሰጥቶ የሚሠራ ሬድዮ ጣቢያ ሆኖ መጣ።
ወደኋላ ሄዶ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ማንነት መሠረቷን እያስቃኘ የተለያዩ ጸሐፍያን በተለያየ ዕይታ የጻፏቸውን ነገሮች ይዞ በመቅረብ ሰዎች ብዙ አማራጭ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህም ኢትዮጵያ በታሪክ ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ፣ የመንግሥት ታሪኳን፣ የሕዝብ ታሪኳን፣ ቀዳሚ ሥልጣኔዎቿን በማሳየት የዚህችን አገር የኋላ ታሪኮች ስንሠራባቸው ቆይተናል።

ከዛ በኋላ ደግሞ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ አለች። ይህቺ የቆምንባት ኢትዮጵያ ደግሞ የኋላ ማንነትና የአሁን እንዲሁም የወደፊቷስ ኢትዮጵያ ምን ልትሆን ትችላለች የሚለው ላይ የተለያዩ ፐሮግራሞች ቀረጽን። እናም ዋናው መለያችን የኢትዮጵያውያን ድምጽ የሚለው ስለሆነ፣ የኢትዮጵያውያን ድምጽ ለመሆን ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን ሂደቶች፣ አሁን ያለችበት ሁኔታ እና የወደፊቷን ኢትዮጵያ ማሳየት ላይ ነው ያተኮርነው።

እውነት ለመናገር የተቀረጹት ፕሮግራሞች የአሐዱ ጋዜጠኞች ብቻ አይደለም የሚሠሯቸው። ከእኛ ጋር የሚሠሩ ተባባሪ አካላት፣ ጎበዝና ሚድያ ላይ በደንብ የመሥራት አቅምና ፍላጎት ያላቸው፣ የሚያነቡ አብረውን እንዲሆኑ አደረግንና በጣም ነጻነት ሰጠን።

እዚህ ቤት ይህን ለምን ሠራህ አይባልም። ነገሩ በኃላፊነት የሚሠራና አገርንም ሆነ ሕዝብን የማይጎዳ፣ ለችግር የማያጋልጥ ይሁን፣ ግን የሰው ልጅ አመለካከትና ሐሳብ ላይ በጣም ነጻነት አለው።

አድማጮቻችንን ቤተሰብ ነው የምንላቸው። ወደራስ የማቅረብ ነው። ይህን ስናደርግ በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ አድማጭ አገኘን። እንደ ቪኦኤ ያለ እንዲሁም ቢቢሲ ብዙ ጥናቶችን አብረው ለመሥራት ጥናት ሲያደርጉ፣ አሐዱ በብዙኀኑ ዘንድ ተወዳጅና ተደማጭ መሆኑ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ለአገር የሚቆረቆር መሆኑን በመስማት፣ ብዙ አድማጭ ቤተሰብ ስላሉትም፣ ከአሐዱ ጋር ለመሥራት ወስነው ሌላ አማራጭ ሆነዋል።

ከዛም የቴሌቭዥን ጣቢያም ጀምረናል። በዛም ከፍተኛ እመርታ ለማሳየት ወደሱ የምንዞርበት ጊዜ ነው። በማኅበራዊ ሚድያዎችም ሁሉ ሕዝቡ ጋር ለመድረስ ሰፊ ጥረት እያደረግን ቴክኖሎጂውን እየተጠቀምንበት እንገኛለን።

የኢትዮጵያ ኅትመት ዘርፍ በጣም ተዳክሞ ተቀዛቅዞ ከባድ አደጋ ውስጥ ነው ያለው። ጥቂት ኮፒዎች ናቸው የሚታተሙት። ይህን መታደግ አለበን። የጋዜጣዎች ጥሩ ጥሩ ፕሮሞሽን በመስጠት ሰዎች እንዲያነብቡ ማድረግ፣ እኛም ወደዚህ ዘርፍ በመግባት ሕትመት ላይ ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲኖሩ በማድረግ አብረን ለማደግ መሞከር አለብን። አንባቢ ትውልድ ካልመጣ በቀር ድንጋይ ወርዋሪ፣ ቤት የሚያቃጥል የሚዘርፍ ትውልድ ነው የሚመጣብን። ይህን ለመታደግ ሚድያው መሥራት የሚገባውን ለመሥራት ብዙ ይጠብቀናል።

እስከ አሁን ባለው ጉዟችን ውስጥ ብዙ ነገር ከፊታችን ቢቀሩም፣ በብዙ መልኩ ስኬታማ ነበርን። ወዳሰብናቸው ግቦች የሚወስዱን ስኬቶች እያገኘን ነው የመጣነው።

በእነዚህ ጊዜያት የገጠሟችሁ ፈተናዎችስ ምን ነበሩ?
በዚህ ውስጥ ብዙ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች ነበሩ። እነዚህ ግን ወደፊት እንዳንሄድ እጅ እግራችንን የያዙ አልነበሩም። በተለይ ባለፉት ኹለት ዓመታት በለውጡ የሚድያ ነጻነት የሰጠ በመሆኑ፣ በኃላፊነት ለመሥራት እንድንችል አድርጎናል፣ ጋዜጠኞቻችን እንዳይሳቀቁ ሆነዋል። እኔም ከዚህ ሙያ ውጪም አልኖርኩምና አውቀዋለሁ፣ የአገሪቱን የሚድያ እንቅስቃሴ።

በጣም አፈናዎች፣ ግድያና ስደቶች፣ በፖሊስ ጸጥታ ኃይል የመንገላታትና መሰል የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የከፈሉት ዋጋ በጣም ከባድ ነው። ያለፉት ኹለት ዓመት ግን በስኬትና በጥሩ ሁኔታ አልፏል። ይህ ማለት ግን ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። አሐዱ በዚህ ስርዓት የመጀመሪያው ተከሳሽ ነው። ለኹለት ወር ያህል እስከ ሰንዳፋ ተመላልሰን በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶብን፣ ከሳሽም ዳኛም ያው ፍርድ ቤት ሆኖ፣ የፍትሕ ሂደቱ ችግር የሞላበት እንደነበር እናስታውሳለን።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገብተውበት ነው ይህ ጉዳይ የቆመው። ምክንያቱም እርሳቸው የዓለም የፕሬስ ቀን ኢትዮጵያ እንዲከበር አድርገው፣ በዛ ማግስት ነው አሐዱ የተከሰሰው። የአገሪቱን ገጽታ በእጅጉ የሚያቆሽሽ ስለነበር፣ ወዲያው ያንን ሊያጸዱት ችለዋል። በአንድ ሚድያ ጉዳይ ገብተው ያንን መፍትሔ በመስጠታቸው፤ በዚህ አጋጣሚ እርሳቸውንም ላመሰግን እወዳለሁ።

አሁንም ግን የኢትዮጵያ ሚድያ ዘርፍ ማሳደግ አለበት። እኛ ያሰብነውና የተነሳበንበት ዓላማም የልኅቀት ማእከል መሆን የሚል ነው። ብዙ ጋዜጠኞች መጥተው ሥልጠና የሚወስዱበት፣ ሥራ ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት፣ የተለያዩ ሚድያ ላይ የሚደረጉ ኮንፈረንሶች ልናዘጋጅ፣ ጥሩ የሠሩ ሚድያዎችና ጋዜጠኞች የሚመሰገኑበት ሽልማት እንዲኖር የሚሉ የወደፊት ሕልሞች አሉ። እነዚህን የምናሳካ ይመስለኛል።

ሌሎች ጋርም አብሮ ማደግም ነው። አሐዱ ብቻውን እንዲወጣ አይደለም። ሁላችንም የዚህች አገር ሕዝብ ልሳን ነን። በጋራ ሆነን ወደ ከፍታ ካላመጣው በቀር ሚድያዎችን ተጠቅሞ የዘርና የጎሳ እልቂት፣ ግጭትና ቃጠሎ የሚመጣባትን አገር በጋራ መታደግ እንድንችል በጋራ ሆነን መሥራት አለብን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥበቡ ደውለው ይቅርታ ጠይቀውታል የሚል ነገር ተሰምቷል። ይህ ነገር እውነት ነው ማለት ነው?
አዎን! እውነት ነው። የዓለም የፕሬስ ቀን በሚከበርበት እለት ዋና መግለጫ የምሰጠው እኔ ነበርኩኝ። በተለያዩ መገናኛ ብዙኀንም ኢትዮጵያ በፕሬስ ያሳለፈችውን ውጣ ውረዶች እና ያለፉት 27ና ከዛ በፊት የደርግ 17 ዓመታት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴም የነበረውን የፕሬስ ዘመን አሳይቼ፣ አሁን ያለፉት 12 ወራት በጣም ጥሩ ነበር ብዬ በተናገርኩ በወሩ ነው የተከሰስኩት።

እና ይሄ እንደ ሲፒጄ ያሉ፣ ሂውማን ራይትስ ወች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ንግግሬን እና ክሴን ነው ያገናኙት። እና አስደንጋጭ ነበር። እሱ በመሆኑም ብቻ ሳይሆን ቀናነታቸውም ይመስለኛል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደውለው አሐዱ ላይ የደረሰው ነገር ልክ እንዳልሆነ፣ ሚድያው ጥሩ እየሠራ እንደሆነ፣ ለውጥ ውስጥ ስላለን በለውጥ ሂደት የሚፈጠር ችግር እንደሆነና የመግባባት ጉዳይ በመሆኑ እንደሚስተካከለ፣ ለልጆቹም [ለአሐዱ ጋዜጠኞች] ሞራል እንድሰጥ መልእክታቸውን አስተላልፈው ከዚያም ያ ክስ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

የአሐዱ ሬድዮ ሥራ የጀመረው ከለውጡ ጥቂት ወራት ቀድሞ ነው። ያም ጊዜ በኢትዮጵያ መረጋጋት ያልነበረበት አስጨናቂ ጊዜ ነበር። ምን ያህል ፈታኝ ነበር?
በጣም ፈታኝ ነበር። አሐዱ የመጣበት ወቅት ኢትዮጵያ በጣም ጣር እና ምጥ ውስጥ የነበረችበት ሰዓት ነው። በጣም ብዙ ቦታዎች ላይ አመጾች ነበሩ። በጎንደር የነበቀለ ገርባን ፎቶ ይዘው የወጡበት፣ በአካባቢው የነበሩት የታጋይ ኮሮኔል ደመቀ የእስር ቤት ጉዳይም አለ። ኦሮሚያው ክልል ውስጥ ትግልና ሰልፎች ነበሩ።
እኛ ለያዝነው የዜና እና የትንታኔ ሥራ እነዚህን ካልዘገብን እንደ ሚድያ አለን ማለት አንችልም። ስለዚህ በጣም ከባድ ጊዜ ነው። እንዘግብም ነበር። መሣሪያ ይዞ ስቱድዮ ድረስ መጥቶ ካልገደልኩ ያለም ነበር። ከዛ በኋላ ነው የጥበቃ ሁኔታችንን ያጠናከርነው።

ለምሳሌ ትዝ የሚለኝ አምቦ ውስጥ 10 ልጆች ተገደሉ። 10 ልጆች ተገደሉ ብለን የዛን ጊዜ ዜና ሠርተን ነበር። ብዙ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይ እኔ ጋር እየደወሉ ‹ነገ ሌላ ቦታ የሚነሳውን ጸብ ኃላፊነት ትወስዳለህ ወይ?› አሉኝ። ቢገደሉስ እንዴት ሚድያ ላይ ታወጣዋለሁ የሚል ነው። በድምሩ ከባድ ጊዜ ነበር።
እግዚአብሔር ረድቶን ከባዱ ጊዜ አለፈ። ከዛም በጣም የሚገርመው አሐዱ በአንዳንድ ፕሮግራሞች ኢትዮጵያ እንደምትለወጥ፣ ምጥ ውስጥ እንዳለች የሆነ ኃይል እንደሚወለድ ይናገር ነበር። እናም ለውጥ ከመጣ በኋላ ጣብያውን ብዙ አድማጭ ቤተሰቦች እንደ ነብይ ይቆጥሩታል። የነበረውን ሁኔታ በመቃኘት የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ይጠቁም ስለነበር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት፣ የኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እያሉ አሐዱን ያዳምጡ ነበር።
አሁን በነጻነት እንዲሠራ ሆኗል። ይህን ነጻነት እንዳንገፈፍ በሕግና በስርዓት ተደግፎ እንዲቆም ሁላችን ጥረት ማድረግ አለብን። አሁን በይሁንታና በአንድ ሰው ቀናነት ሊሆን ይችላል፣ ግን ሕግና ስርዓት ኖሮት እንዲደገፍ ጋዜጠኞች፣ ሚድያዎች፣ የፍትሕ አካላት ብዙ ሊሠሩበት ይገባል ነው የምለው።

ሚድያዎች ባለቤታቸውን ይመስላሉ ይባላል። ባለቤቶቹ የቢዝነስ ሰዎች ከሆኑ ቢዝነስ ላይ ያተኩራል ሌላውም እንደዛው። ይህ በጋዜጠኝነት ወይም ሙያተኝነት ላይ ተጽእኖ አይኖረውም?
ኤዲ-ስቴላር ብዙ የንግድ ሥራዎች ያሉት ድርጅት ነው። ግን ወደ ሚድያ ዘርፍ ሲገባ የራሱ የሆነ የሥነምግባር ደንብና መመሪዎች አሉ። ስለዚህ እነዚህን ደንብና መርሆዎች ማክበር ይገባል። እነርሱ ላይ ተመርኩዘን የተሻለ አገርና ሕዝብ፣ ቀደምት ሥልጣኔ የነበረው በኋላ በጣም ወደኋላ የቀረ ሕዝብ፣ በድህነት፣ በረሃብና በስደት የምትታወቅ አገር የሆነችው አንድም ሚድያ ስለሌላት ነው ብሎ ያምናል።

ሚድያ በብዛት ቢኖር የሰው አእምሮን እናጎለብታለን። ነገር ግን ሚድያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት ሕዝብ በበሽታ ይጠቃል። ግጭቶች አሉ፣ ዘረኝነት በጣም ተስፋፍቷል። ሕዝብ ጋር በቀላል መድረስ የሚችል ደግሞ ሚድያ ነው። ሚድያን የሥነ ምግባር ደንቡን ተጠቅሞ አገርን ወደ ማልማት መውሰድ ይቻላል የሚል ቀናነት ስለነበረው፣ አሐዱ እንደ ቢዝነስ ተቋም ለትርፍ ብዙ አልሠራም። ኤዲ-ስቴለር በሌሎች ሥረዎቹ እየደጎመው ነው የሄደው። እንደ አቢሲንያ ባንክ ያሉት ብድር በመስጠት ድጋፍ በማድረግ ሬድዮ ጣቢያው እንዲቀጥል አድርገዋል።

አሁን በጣም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው። ለቢዝነስ ለመሥራት ብሎ ጫና አላደረገም። ጋዜጠኞቻችን ኃይል ያላቸው፣ የተሻሉ ጋዜጠኞች ለመሆን የሚጥሩ ናቸው። ስለዚህ ሙያ ላይ ነው ያተኮረው። የጋዜጠኝነት ደንብና መርህ ላይ አተኩረን በመሥራታችንም በቀላሉ ሕዝቡ ውስጥ ስንገባ የሕዝብ ድምጽና ልሳን እንድንሆን፣ ሕዝቡም ቤተሰባችን እንዲሆን አስችሎታል ነው የምለው።

በብሔር ሥምና በክልል የተደራጁ መገናኛ ብዙኀን አሉ። በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ እንዲህ ባይሠለጥን ኖሮ እነዚህ መገናኛ ብዙኀን አዎንታዊ ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችል ነበር ብለህ ታምናለህ?
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የፈጠረው ችግር በብሔር መደራጀትን ነው። ያ ደግሞ አንዱ በሌለው ጨቋኝ ተጨቋኝ የሚል ነገር ሲያመጣ፣ በብሔሮች መካከል የመጠላላት፣ አንዱ ሌለውን የመጠራጠር ድባቦ መጎልበት ጀመረ። ገና ከመጀመሪያው በርካታ የብሔር ተኮር እልቂቶች ተካሂደዋል። በየጊዜው ሰዎች በብሔርና ቋንቋቸው ምክንያት ይፈናቀላሉ።

ይህን ተከትሎ የብሔር ሚድያ ተቋቋመ። የብሔር ሚድያዎች የዛን ብሔር ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ማንነቱንና ፍልስፍናውን ከመናገር ይልቅ የፖለቲካ አጀንዳ ውስጥ ገቡ። አንዱ ሌላውን ጨቋኝ ነው ሲል የነበረውን ትርክትና ግለቱን ሚድያዎች እያባባሱ መምጣታቸው ነው ትልቁ ችግር። እንጂ ያ ባይሆን እያንዳንዳችን የመጣንበትን ብሔር፣ በትዳር ያለውን ትስስርና አዎንታዊ የሆኑ ግንኙነቶች ላይ ተመሥርቶ ቢሆን ጥሩ ነበር። ግን እንደዛ ሳይሆን የፖለቲካ ቃና ነበራቸው።

ስለዚህ ኢትዮጵያን ግጭት ውስጥ እየከተቷት ነው። በቅርቡ የተከሰተውን ችግር ስናይ ሚድያ መር ነበር። ሰዎች እንዲገዳደሉ የተደረገው በሚድያ አማካኝነት ነው። ሚድያን ለበጎ ስንጠቀምበት አገር ይቀይራል፣ ለመጥፎም ሲሆን እንዲሁ አውዳሚ ነው። እና ብሔር ተኮር የፖለቲካ ጡዘትን ይዘው ነገር እንዳያቀጣጥሉ ነው ብሔር ተኮር ሚድያዎች ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆን አለባቸው የምንለው።

ፖለቲከኞችም ስለታሪክና በታሪክ ዙሪያ ሲጠየቁና ምላሽ ሲሰጡ እናያለን። ታሪክም አንዱና ዋነኛው የፖለቲካ መሣሪያ እየሆነ ይመስላል። ይህን ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት? መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ጋዜጠኞችስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?
አብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ታሪክ ሲያነብ አላውቅም። ፖለቲካ ሲናገር እንጂ ይህን መጽሐፍ እንብቤአለሁ ብሎ ካነበባቸው መጽሐፍት አንጻር ሲተነትን፣ ሲያብራራ አላየሁም፣ አልሰሁማ ወይም አላነበብኩም። ግን በአሉሽ አሉሽ እንዲህ ተብሏል ተብሎ ይወራል።

ለምሳሌ አንዳንዱ አጼ ምኒልክ ጡት ቆርጧል ይላል። የት፣ መች፣ የትኛው መጽሐፍ ላይ የሚለው የለም። ጋዜጠኞች ደግሞ አይሞግቱም፣ አይጠይቁም። የት ነው ያነበብከው፣ ካለበዚያ አይተላለፍም። ምክንያቱም ይሄ ሕዝብን በሕዝብ የሚያነሳሳ ነው ብሎ አይሞግትም።

ሃውልቶች ትግራይና አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ውስጥ የተሠሩ አሉ። ወንድም ወንድሙን ገድሎ። እነዚህ ሃውልቶች ራሱ የምቀኝነት፣ አንዱ በሌለው ላይ የታሪክ ጠባሳ የሚያኖሩ ሆነው ነው የምናገኛቸው። እንዲህ ያሉ ትርክቶች ፖለቲካ ውስጥ እየገቡና ወጣቱ እውነት እንዲመስለው እየተደረገ ነው። በዛም ዩኒቨርሲቲ የገቡ ልጆች በብሔራቸው ምክንያት እየተጋጩ እናቶች የልጆቻቸውን አስክሬን እስኪረከቡ እየሆነ ነው።

ይህ ትክክል አይደል። ይህ ትርክት አገር ይጎዳል፣ አገር ያበላሻል በሚል እኛ እንደ አቋም የቆምንለት ጉዳይ ነው። ከታሪክ ወደኋላ ዞር ብለን ስናይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች ናት። አፍሪካ ውስጥ በቀለማቸው፣ በዘራቸው ምክንያት አፍሪካውያን በገዛ አገራቸው የተገለሉበትን የቅኝ ገዢዎች ዘመን እናስታውሳለን።

ኢትዮጵያ አፍሪካን ከባርነት ነጻ ያወጣች አገር ናት። እንደነ ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ በአፓርታይድ ምክንያት ግፍ ሲደርስባቸው ለነበሩ የአፓርታይድን የዘር መድሎ ገፍፋ ነጻ ያደረገች፣ ማንዴላን ያስተማረች አገር ናት። ለአፍሪካ ነጻነት ቀኝ እጇን ሰጥታ የታገለች ናት። የእርሷ ልጆ ግን ከ1983 በኋላ ብሔር ተኮር በሆኑ ግጭቶችና በሐሰተኛ ትርክቶች ሲገዳደሉ ማየት ያስፈራል፣ ያሳፍራልም።

ይህን ሐሳብ ያመጡ ፖለቲከኞች ዛሬ ወደኋላ ዞር ብለው ሲያዩ መናዛዣ ጊዜ ያላቸው ይመስለኛል። አንዳንዶቹ በእርግጥ እየተናገሩ ነው። እናም ሕዝብን ማረጋጋት፣ ወጣቱን ወደተሻለ ምዕራፍ ማምጣት መቻል አለባቸው። እንዲህ ያሉ ትርክቶች ናቸው ፖለቲካውን የሚያጦዙት።

ፖለቲከኞቻችን ወደንባብ መጥተው አውቀውና አንብበው ወይም ደግሞ ታሪክን ለታሪክ አዋቂና አንባቢዎች ሰጥተው ከዛ ወስደው ቢናገሩ ይሻላል። እንጂ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የምናየው የኢትዮጵያ ታሪክ በንባብ የዳበረ አይደለም። አሐዱም ይህን እያጠራ የሚሄድ ሬድዮ ጣቢያ ነው።

ጥበቡ ለአገር ያለው ፍቅር፣ ለሙያው ያለው መሰጠት፣ ለንባብ ያለው ትኩረት፣ ከታሪክ ጋር ያለው ግንኙነትና ለአገር ባለውለታዎች የሚሰጠውን ክብር ብዙዎች ያውቃሉ፣ እናውቃለን። ይህን ከየት ወረስከው?
ወደኋላ ስሄድ የተቀራረበ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። በቤተሰብ ውስጥ የተለያየ ሙያ ላይ ያሉ አሉ፣ ነጋዴዎችም አሉ። ለትምህርት ግን በጣም ትኩረት ይሰጥበት የነበረ ቤተሰብ ነው። አያቶች ነበሩኝ። አያቶቼ በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት፣ የእነርሱ ወላጆችም እስከ ኬንያ ድረስ በተለይ ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ በጣም የተዋጉ ናቸው። አንዱ የአንዱን ሽንት እየጠጣ እንደተዋጋ፣ በረሃ ውስጥ እንዴት እንዳለቁና መሰል የእነርሱን ዘመዶችና ቤተሰቦች ታሪክ ከልጅነት እሰማ ነበር።

እነዚህ ታሪኮች ብዙ ነገር የሰጡኝ ይመስለኛል። በተለይ ሴት አያቴ በቃሏ አስታውሳ የምትተርክልኝ ብዙ ነው። ለምሳሌ ከነገረችኝ ውስጥ አንደኛው ጣልያኖች በየደረሱበት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው ያቃጠሉ ነበር። አያቴና ሌሎቹም ታድያ ጣልያኖቹ ከመምጣታቸው በፊት ሰንደቅ ዓላማውን አውርደው፣ አጣጥፈው፣ በላስቲክ አድርገው ቀብረው ወደ ውጊያ ይሄዳሉ። ከዛም የአምስት ዓመቱ ጦርነት አብቅቶ አሸንፈው ሲመለሱ ያንን ሰንደቅ ዓላማ ከመሬት ውስጥ አውጥተው በነጻነት እንደገና ሲያውለበልቡት።

እና እንደዚህ ዓይነት ታሪኮች ሰምቼ በልጅቴም ጽፌአቸዋለሁ። በኋላ ትምህርት ዓለምም በዚህ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ነው የተማርኩት። በሕይወት በጣም እድለኛ ነኝ፤ ትልልቅ የጋዜጠኝነት ሙያ መምህራን አስተማሩኝ። በውጪ አገር በጀርመን፣ በኖርዌይ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያም ተከታታይ የሆኑ የትምህርት እድሎችን አገኘሁ።

እነዚህ ትምህርቶች የኢትዮጵያን ታሪክ አይደለም የሰጡኝ። የጋዜጠኝነት ሙያ የደረሰበትን ደረጃ ነው ያሳዩኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ያነበብኳቸው መጻሕፍት፣ ትልልቅ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ እንደ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር)፣ ዩናስ አድማሱ (ዶ/ር)፣ አምሳሉ አክሊሉን የመሳሰሉ የሥነ ጽሑፍና የታሪክ ባለሞያዎች ስላስተማሩኝ፣ ውስጤ ብዙ ነገር እንዳጎለብት አድርጎኛል። ከዛም በሥራ ዓለም የገጠመኝ ነገር ሁሉ ጥሩ ነው። ብዙ ፈተናዎች በሕይወት አልገጠመኝም። ለሥራዬ ነገሮች ቀና ነበሩ።
በእርግጥ እንደ ግለሰብ አይግጠሙኝ እንጂ በአገር የሚመጡ ነገሮች በመጣሁበት ፍጥነት እንዳልሄድ አድርገውኛል። ግን ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ደግሞ ታሪኳ ነው፣ ነዳጅ ዘይት የላትም። የታሪክ ሀብታም ናት። ጀርመን ስማር የ150 ዓመት ታሪካቸውን ብዙ ሰው እየመጣ ሲጎበኝ አያለሁ።

እንደ እኛ በብዙ መቶና ሺሕ ዓመታት ታሪክና ቅርስ ያላትን አገር ገና አላስተዋወቅናትም። ሀብቷን አልተጠቀምንም። ሀብቷ ላይ ተቀምጠን የደኸየን ሕዝቦች ነን የሚል አመለካከት አለኝ። ኢትዮጵያዊ ደግሞ በአዋቂዎች ተረት ታሪክ እየተነገረው ያደገ ነው። ስለዚህ ሚድያዎች ላይ እነዚህን ታሪኮች ብናመጣ ለሁሉም መድረስና ብዙ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን።

ወደኋላ የቤተሰብ ታሪኬ፣ ቤተሰቦቼ ያስተማሩኝ፣ ከዛም በትምህርት ተቋም ያገኘሁት፣ ቀጥሎ በሥራ ዓለም ያገኘኋቸውና ንባብ ያመጣቸው ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ለዚህ ክብርና ሞገስ፣ ማዕረግ ስለበቃኝ አመሰግናለሁ።

በብዕር ሥም የጻፍካቸው መጽሐፍት አሉ እንዴ?
አሉ። አንዳንዶቹን አሁንም ባልናገራቸው ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ብቻዬን መግለጽ ስለሌለብኝ ነው። ድንበሩ ስዩም የሚል ሥም የእኔ ነው። የኢሕአፓው መሥራችና መሪ ክፍሉ ታደሰን መጽሐፍት ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ እንደሚመጡ ነበር የሚታወቀው። እነሱን አርትዖት ሠርቶ የማውጣት ሥራ ያስቀጣ ነበር።

እኔ ግን እነዚህ መጻሕፍት ለኢትዮጰያ ታሪክ አዋቂዎች፣ ተመራማሪዎች ጥሩ ናቸው ብዬ አርትዖት ሰርቼ እንዲታተም አደረኩኝ፣ አስተያየትም ስጽፍ በብዕር ሥም እጽፍ ነበር። ያኔ ‹ያ ትውልድ› የሚለው እስከ ቁጥር ሦስት ድረስ፣ ከዛም በጣም ከባድ የሚባለው ደግሞ ‹ግንቦት 7 ኢትዮጵያ ከየት ወዴት› የሚል መጽሐፍ ጽፎ ነበር። ያንን አርትዖት ሠርቶ፣ አሳትሞ ማውጣት፣ ‹ግንቦት ሰባት› ማለት በራሱ ወንጀል በነበረበት ሰዓት ነው። ይህን ከንባብና ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ስለማየው እንደሱ አድርጌአለሁ።

ሌሎችም በብዕር ሥም እጽፋቸው የነበሩ መጻሕፍት ነበሩ። ይህ ሁሉ የሆነው እንግዲህ አፈና ስለነበር ነው። አፈና ባይኖር መጽሐፎቹም ላይጻፉ ወይም በነጻነት ሊዳፉ ይችል ነበር።

ታሪክን መሻማት ካልሆነብኝ ለለውጥ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉ እኛ የጻፍናቸው መጻሕፍት አሉ። ያ ያኮራኛል። በሕይወት ኖረሽ አገር ሲለወጥ ማየት ደስ ይላል። ትልቁ ጉዳይ ግን ይህ እንዳይቀለበስ የተሻለ አገር ለልጆቻችን ለማምጣት ብርቱ ትግል ማድረግ አለብን። ሁሉ ነገር አሁንም የተስተካከለ አይደለም። አሁንም ግድያና መፈናቀሎች፣ ጎሳ ተኮር ጉዳዮች፣ የደኅንነት ስጋት አለ። ይህ በጋራ ልንታገል የሚገባ ነው። ጅማሬው ግን ጥሩ ነው። የዛ ክፍል አንድ አካል በመሆኔም ደስ ይለኛል።
‹አዲስ ዜና› የተሰኘውን ጋዜጣ ባለቤቶችና ብዙ ሠራተኞች በፖለቲካ ምክንያት ሲሰደዱ ጥበቡ እዚሁ በአገር ቆይቷል። ያንን ጊዜ መለስ ብለህ ብታስታወሰን?
በጣም ሕልም የነበረው አዲስ ብሮድካስቲንግ የሚባል ድርጅት አቋቁመን ነበር። እዛ ላይ ብዙ አሁን ፖለቲከኞች የሆኑ እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያሉ ሰዎች ነበሩበት። ከዛ ሕልም መጨናገፍ በኋላ ብዙዎቹ ፖለቲከኛ ሆነዋል። የሚድያ ኢምፓየር እንመሠርታለን የሚል ነው።

1989 ከእኔ ጋር ተገናኘን። እስከ 1991 ድረስ ብዙ ነገሮች ስናቋቁም ቆይተን የኖርዌይ መንግሥት የትምህርት እድል ሰጥቶን ልንሄድ ስንል፣ ፓስፖርታችን ብርሃኑ [በወቅቱ ዶ/ር] እጅ ተያዘ። እርሱም ተማሪዎች አነሳሳህ ተብሎ ሲታሰር በአጋጣሚ የእኛ ፓስፖርት እርሱ ጋር ስለተገኘ፣ ልክ በሌላ ጉዳይ እንደሆነ ሆኖ የተጠየቅንበት ጊዜ ነበር። እኛም ቀለበት ውስጥ የመግባት፣ በምንሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ ጥላ ሆነው የሚመጡ አካላትም ነበሩ።

ግን በጊዜው ወጣትነት ስለነበር ሕልማችንና ግባችን ሬድዮ መክፈት ነበር። ያኔ ብሮድካስት ባለሥልጣን እንኳ አልነበረም። ሬድዮን ልንከፍት እንፈልጋለን ስንል የሚቆጣጠር አካል የለም ተብሎ ነው የተቋቋመው። ከዛ በኋላ እሱ ሲቆይብን ጋዜጣውን ጀመርን።

አዲስ ዜና ብዙ ስርጭት ነበረው። በሰሜን አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠር ይላካል፣ በአውሮፓም እንደዛው። አገር ውስጥ ብዙ አንባቢ ነበረው። በሙያተኝነት ነበር የምንሠራው። ያኔ ጋዜጠኞች ትንሽ ሞቅታ ያበዙ ነበር። ግን በጣም በተረጋጋ መንገድ የሚሠራ ጋዜጣ ነበር።

ውጪ ተምረን ከመጣን በኋላ ነው ድርጅቱን እንድንመሠረት እድል የሰጡንና በዓለም ያለውን እንቅስቃሴና ምን ዓይነት ሕልም ሊኖረን እንደሚገባ ካየን በኋላ ልጆች መቅጠር ጀመርን። 20 ወጣቶች ቀጠርን። እነዚሁ ልጆች እኛ የሄንድበት ቦታ ሄደው ተማሩ።

እነዚህ ልጆች ትልቅ ሕልም የነበራቸው ናቸው። አውሮፓ ሄደው አንድም ልጅ አልጠፋም። ድሮ ምሁራን ሁሉ ይጠፉ ነበር። ለምን አልጠፉም? አዲስ ብሮድካስቲንግ ውስጥ ሠርቼ እለወጣለሁ የሚል ሕልም ስለነበራቸው ነው። እንዲህ እያለ ሬድዮ ተከለከልን። ሕልሞች ተጨናገፉ። ሰዎቻችን ወደ ፖለቲካው ዓለም ገቡ። 97 ምርጫም መጣ። ብዙ ድርጅቶች ተዘጉ። ጋዜጠኞች ብዙ እህት ወንድሞቻችን ተሰደዱ። እና እኔ ነበርኩኝ የቀረሁት።

እኔ ስቀር ሌላ የተለየ ነገር ኖሮኝ አይደለም። በሐዘንና በስሜት መጎዳት ደግሞ የወደፊቱንም ተስፋ በማድረግ አንድ እኔ ቀርቼ የሆነ ታሪክ ነጋሪ እንኳ ቢኖር ብዬ ነው። ይህ የአዲስ ብሮድካስቲንግ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ሁሉም ሚድያዎች ተዘግተዋል፣ ተባረዋል፣ ተሰደዋል።

ከዛም ወደ ታሪክ ጉዳዮች አዘነበልኩኝ። ያኔ ፖለቲካው ነው እንዲህ ያደረገው ስለሚባል የታሪክ ነገራ ውስጥ ገባሁ። ጫናም ቢኖረው ብዙ ጊዜ ለአደጋ አይሰጥም ነበር። ያኔ ለጋዜጣም የሚሆን ሰንደቅ ጋዜጣ ላይም እጽፍ ነበር። ጥሩ የጥሞና ጊዜ ነበር ማለትም ይቻላል። አጋጣሚ ሆኖ ብዙ ሥራም የሠራሁት በዛን ጊዜ ነው።

ዘጋቢ ፊልሞችን 1998/99 የኪነሕንጻ አሠራር የቅዱስ ላሊበላ፣ የጎንደርን፣ የአስክሱምን፣ የሐረርን፣ እስልምና እንዲሁም ክርስትና በኢትዮጵያ የሚሉ ዘጋቢ ፊልሞች ሠርቼ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ አገራት እንዳይ አድርገውኛል። ያኔ ሚሊንየም ይከበር ነበር። እናም ለሚሊንየም ተብሎ ሰዎች ዝም ብሎ ማንነት ይሰጣቸዋል።
የኢትዮጵያ የሚሊንየሙ ጀግና እገሌ ይባላል። ሚሊንየም ማለት አንድ ሺሕ ዓመት ነው። ስለዚህ በአንድ ሺሕ ዓመት ውስጥ እነማን ነበሩ ብዬ ታላላቅ የኢትዮጵያን ነገሥታት እነዚህ አሉ እያልኩ በቁጭት ብዙ ነገር ሠራሁ። እና የዛሬ ማንነቴ ብዙዎች በዛ ወቅት በቁጭት የተሠሩ ናቸው።

ብዙዎቹ ጓደኞቼ አሁን ከስደት መጥተዋል። ወደ ሚድያም እየገቡ ነው። እዚህ በመሆኔ እግዚአብሔር ይመስገን ሌላም አደጋ ሳይመጣብኝ ብዙ ነገር ሠርቻለሁ። የአፍሪካ ኅብረት ሃምሳኛ ዓመት ሲከበር ፕሮጀክቱ የተሰጠው ለእኔ ነበር። አፍሪካ ኅብረትና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተባብረው የሸለሙት እኔን ነው።
እናም ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ያንን ጥናታዊ መጽሔት በማዘጋጀቴ ኩራትና ክብር ይሰማኛል። ከዛ ደግሞ በስኬትም ስለጨረስኩኝ። እናም በመቅረቴ የተጎዳሁት ነገር የለም። ጫና ቢኖርም ብዙ ነገርም ሠርቻለሁ። ለበጎ ነው እላለሁ አንዳንዴ። ብሄድ ኖሮ ይህን ሁሉ አልሠራም ነበር።

አዲስ ጥበብና ባህል የሚባል ድርጅት ከጓደኞችህ ጋር መሥርታችሁ ነበር። ምን ምን ሠርቷል?
ድርጅቱ መጀመሪያ መሠረት ያደረገው አሜሪካ በተሰደዱ ጓደኞቼ ተመሥርቶ ነው። እኔም እዚህ ሥራውን ቀጠልኩኝ። በዛም የአክሱምና ላሊበላን ዘጋቢ ፊልሞች ሠርተናል። የላሊበላ እንደውም ለንደን ውስጥ በ2007 ‹ምርጥ የአፍሪካ ዘጋቢ ፊልም› ተብሎ ተሸልሟል። እኛ ለሽልማት አልነበረም የሠራነው። ማሳወቅና ክፍተቱን እንሙላ የሚል ነበር። በአጋጣሚ ሽልማቱ ተገኘ።

ጓደኞቼ ቢሰደዱም በርቀት በመንፈስ እየተጋገዝን እንሠራበት ነበር። ከዚህም አልፎ ኡጋንዳ ውስጥ ካምፓላ ከተማ የኢስት አፍሪካን ሲኒማ እና ካልቸር የሚባል ድርጅት አቋቁመው እንደ አጋር ሆኖ ‹አብዩዝ ኢኖሰንስ› የሚል ሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርስ ጭቆናና በደል የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም እኔ ዳይሬክተር ሆኜ ሠርተናል።
በዛ መጥፎ ሰዓት ውስጥ ብዙ ሥራ ሠርተናል። እዚህ መኖሬም ብዙ እንድንሠራ አድርጓል። በዚሀ አጋጣሚ የማመሰግናቸው ሰዎች አሉ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም በተለይ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት ላይ ድጋፍ አድርገውልኛል። ከኢትዮጵያ እጅ እንዳይወጣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ሊያሸንፉ ጫፍ በደረሱበት ሰዓት የእኔን ፕሮፋይል እርሳቸው ደግፈው በመገኘታቸው ያንን ጨረታ እንዳሸንፍ አድርገውኛል።

የሕዳሴ ግድብ አሁን ሙሌት ተጀምሯል። ያኔ ‹ኮኦፕሬትቭ ዋተር› የሚል የጥናት መጽሔት የተለያዩ የኢትዮጵያና የተፈሰሱ አገራት ምሁራንን በማሳተፍ እንዴት በጋራ እንጠቀም በሚል አዘጋጅቼ ነበር፣ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን። እሱን በየስድስት ወሩ የማሳተም ትልቀ ሕልም ነበረኝ። የተወሰኑ ሰዎች አጨናገፉት። ፖለቲሳይዝ ተደረገ። ከነማን ጋር ነበር ብለው የኋላ ታሪክ አይተው አስቀሩት እንጂ ብዙ ይሄድ ነበር። ወደፊት እግዚአብሔር ካለ እንቀጥለዋለን።

ንባብ ለሕይወት የተሰኘ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ በየዓመቱ ይካሄድ ነበር። በዚህም ከንባብ አምባሳደርነት ባሻገር ከአዘጋጆቹም መካከል ነህ። ንባብ ለሕይወት ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት አልተካሄደም። ቀርቷል ወይስ ይቀጥላል?
እኔ ቢንያም ከበደ፣ ኤሚ እንግዳ፣ አንተነህ ከበደ እንዲሁም እስክንድር ከበደ ሆነን የሬድዮ ፕሮግራም ፋና ላይ ነበረን። ‹አዲስ ጣዕም› የሚል። ቢንያም ለሬድዮ የተፈጠረ ሰው ነው፣ ድምጹ ለዛ የተሰጠ፣ አገሩን የሚወድ፣ አሁን የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን የከፈተው ማለት ነው።

የአገራችን ገዳይ ስለሚያሳስበን ንባብ ላይ እንሥራ የሚለውን አመጣን። የተለያዩ አገራት አውደ ርዕዮችን አነበብን። በግሌ እስከ አሁን ያለ ‹ኢትዮ ኮን› የተባለውን የኮንስትራክሽን አውደ ርዕይ አዘጋጃለሁ። እናም ልምድ ስላለኝ ወደ መጽሐፍት ስንመጣ ደግሞ የማውቀው ነገር ስለሆነ፣ ወደሥራው ገባን።

በጣም ስኬታማ እንደምንሆን እርግጠኛ ነበርን። ለሁሉም (ለቢንያም፣ ለኤሚ፣ ለአንተነህ እና ለእስክንድር) ምስጋናውን እሰጣለሁ። ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል። አውደ ርዕዩም ትልቅ ሆነ። ብዙ መጽሐፍ የሚገዛበት፣ ታሪኮች የሚቀርቡበትም ሆነ።

ሌለው የሚገርመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በነበሩበት ጊዜ ገና ‹አቶ› እያሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት የታዩት 2008 ተጋብዘው ንግግር አድርገው ነው። ብዙ ሰው ኢሕአዴግ ውስጥ ሰው አለ እንዴ ለካ ያለው እርሳቸው ስለመጽሐፍ፣ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የተናገሩትን ሰምቶ ነው።

እኛ ከዛ በኋላ አሐዱን ስንከፍት ኢትዮጵያ ወደፊት ትቀየራለች የሚለውን አባባል ያመጣነው አንድም እርሳቸው ሲናገሩ በማየት ነው። እና ያ አውደርዕይ እርሳቸውን ወደ አደባባይ አምጥቶ እንድናይ እንድናውቃቸው ያደረገ ነው። ከብዙ ደራስያን ጋርም ያገናኛቸው ነው።

ያ ኤግዚቢሽን ሄዶ ሄዶ ባለፈው አንድ ዓመት ተቋረጠ። ያም የሆነው ብዙ የመንግሥት ተቋማት አብረን እንሥራ ብለው ስምምነት ተፈራርመን እኛ በምንሄድበት ፍጥነት ሊሄዱልን አልቻሉም። ከመንግሥት ጋር ሲሠራ እንደ ግሉ አይፈጥንም። ያንን አፍርሰን ብቻችንን እንዳንሠራ አሳሪ ውል አለ። እናም በውሉ ምክንያት ቀረ። ዘንድሮ በራሳችን ልናካሂድ ነበር ግን በዚህ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ቀረ።

ነገር ግን ንባብ ለሕይወት ፈጽሞ የማይቋረጥ ነው። አናቋርጠውም። ትውልድም ይቀጥለዋል። በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በክልል ከተሞች ሁሉ መደረግ አለበት። ከኢትዮጵያም ውጪ መደረግ ያለበት ነው። የኢትዮጵያ ሀብት እንዳልኩት ታሪኳ ነው።

ንባብ ለሕይወት በዋናነት ሰዎ ከመጻሕፍት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ፣ ደራስያን ከአንባብያን እንዲገናኙ፣ ልጆች የማንበብ ፍቅር እንዲያዳብሩ፣ ጥናትና ምርምሮች እንዲቀርቡ፣ ታላላቅ ደራስያንና የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን እንድንሸልም፣ ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር የተነሳ ነው። ኹለተ ተከታታይ ጊዜ ባለመደረጉ አዝናለሁ።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here