የኮቪድ 19 ስጋት እና ያየለው መዘናጋት

0
1514

ዓለማችን ኮቪድ 19ን ካስተናገደች ግማሽ ዓመት አለፈ። አፍሪካም በተመሳሳይ አምስት ወራትን ከቫይረሱ ጋር ትንቅንቅ እያደረገች ዘልቃለች። የዚህ ቫይረስ ወረርሽኝ መድኃኒትም ሆነ ክትባቱ ይህ ነው ተብሎ ለአገልግሎት ባይቀርብም፣ በቫይረሱ ላለመያዝ የሚደረገው ጥንቃቄ ግን ለሁሉም ሰው የሚሆንና ቀላል ነበር።
ያም ሆኖ የማኅበረሰብ ቸልታና ጥንቃቄ ለማድረግ የመስነፍ አመል የወረርሽኙ ስርጭት እያደር እንዲጨምር አድርጎታል። ሰዎች በየመንገዱ ተቃቅፈው ይንቀሳቀሳሉ፣ ተጠጋግተው ይሰለፋሉ፣ ተቀራርበው ይቀመጣሉ፣ አፍ ለአፍ ገጥመው ያወራሉ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልንም በአግባቡ አይጠቀሙም። እንደ ኢትዮጵያ ላለች ደሃ አገር ደግሞ እንዲህ ያሉ የጤና እክሎች በማኅበረሰብ ደረጃ ስፋታቸው እየጨመረ ሲሄድ፣ የሚያስከፍሉት ዋጋ ቀላል አይሆንም። በሚሊዮን ለሚቆጠር ሕዝብ በጥቂት መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለይቶ ማቆያና ማከሚያ አልጋዎች ሲኖሩ፣ ለጽኑ ሕሙማን ያለው አስፈላጊ ግብዓትም ወረርሽኙ እየተዛመተ ካለበት ፍጥነት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ይህንና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን መዘናጋት እንዲሁም በመንግሥት በኩል የሚጠበቀውን እርምጃ በሚመለከት፣ ከነባራዊ እውነቶችም በማጣቀስ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።
አድርጋዋለች።

አየለ (ሥሙ የተቀየረ) ከኹለት ወር በፊት ነው አሳዳጊ እናቱን በሞት ያጣው። በጤና ዘርፍ ላይ የጤና መኮንን በመሆን ከአዲስ አበባ ውጪ ለኹለት ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ይህ ወጣት፣ አሳዳጊ እናቱ በጠና መታመማቸውን እንደሰማ ከእረፍታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነበር አዲስ አበባ የተገኘው።

ቀድሞ የመተንፈስ ችግርና የልብን ሕመም የነበረባቸው የአየለ እናት ሲያርፉ፣ ከአስክሬናቸው የኮቪድ ምርመራ ሊካሄድ ናሙና ተወሰደ። የናሙናው ውጤት ሳይመጣም ለቤተሰብ አስክሬን የተሰጠ ሲሆን፣ አየለ ከእህትና ከወንድሞቹ፣ እንዲሁም ጥቂት ከማይባሉ ዘመድና የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር የቀብር ስነስርዓቱን አከናወኑ። ሐዘናቸውን ተወጡ።

ወቅቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት ያየለበት በመሆኑ ብዙ ለቀስተኛ ወደ ቤት ውስጥ አልገባም። ከነአየለ ቤት ደጅ ላይ በተጣለው ነጭና ሰፊ ድንኳን ስር ተራርቀው በተቀመጡ ወንበሮች ላይ የሚተዋወቁ ሰዎች ተቀራርበው ተቀምጠዋል። የተወሰነ ሰው ሲወጣ የቀረው እየተተካ፣ የተወሰነውም ከደጅ ሆኖ ‹እግዚአብሔር ያጽናችሁ፣ ነፍስ ይማር› እያለ በጭልፋ ተዘግኖ በየእጁ መዳፍ የሚደረግለትን ንፍሮ እየቀመሰ ይወጣል።

ከቀብር በኋላ በሦስተኛው ቀን ለአየለ የተደወለለት ስልክ ሕይወታቸው ካለፈው እናቱ የተወሰደው ናሙና ኮቪድ 19 እንደነበረባቸው ያሳያል የሚል ነው። ስለዚህም ቤቱ እንዲዘጋና ልጆችም ከማንም ጋር ንክኪና ግንኙነት እንዳያደርጉ ተባለ። እነርሱም ናሙና ሰጥተው በራቸውን ዘግተው ውጤቱን ይጠባበቁ ነበር። ይህ ክስተት ለአየለ የቅርብ ጓደኞቹና የሆነውን ለሰሙ ሁሉ አስደንጋጭ ነበር።

የሆነው ሆኖ ቫይረሱ በልጆችና በማስታመም ቅርብ በነበሩ የቤተሰቡ አባላት ላይ አልተገኘም። እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ግን በተለይም ዝንጋኤ በወረሳቸው መሰባሰቦች ምክንያት ብዙዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህ እንግዲህ ከአንድ ወር ቀድሞ የሆነ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ በምታሰናዳበት ጊዜ መዘናጋቱ የበለጠ ከፍ እንዳለ ምስክር የሚሆኑ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በብዛት የተስተዋሉበት ነው። በየመገናኛ ብዙኀኑም ይህ መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍለን የሚሉ ማሳሰቢያዎች በተደጋጋሚ ተሰምተዋል።

የቫይረሱ ስርጭት ባለፉት አራት ወራት
ኮቪድ 19 ኢትዮጵያ በገባ የመጀመሪያ ወር ላይ የስርጭት ፍጥነቱ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። መጋቢት ወር በአራተኛው ቀን በቫይረሱ የተያዘ የ48 ዓመት ጃፓናዊ በኢትዮጵያ መገኘቱና ይህም ሰው የካቲት 25/2012 ከቡርኪናፋሶ ወደ አዲስ አበባ የገባ እንደሆነ ተገለጸ። ከዚህ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችን መለየት የመጀመሪያው ተግባር ሲሆን፣ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ደግሞ ጤና ሚኒስቴር ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ድምጻቸውን ማሰማት ቀጠሉ።

ቫይረሱ ለአንድ ወር ያህል ማለትም እስከ ሚያዝያ 03/2012 የስርጭት መጠኑ ዝቅተኛ ነበር። ኢትዮጵያውያንም በያሉበት በጸሎት እንዲተጉ ጥሪ ሲቀርብ፣ ሁሉንም ማለት ይቻላል የሃይማኖት ተቋማትን ያሳተፈ የምህላ ጸሎትም በጋራ ተከፍቶ ይደረግ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ምንም እንኳ የሚወቀሱና ግዴለሽነት አለባቸው የተባሉ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ ጥንቃቄዎች የበለጠ ኃይል ነበራቸው።

ሚያዝያ 3/2012 የጤና ሚኒስቴር ያወጣው እለታዊ ዘገባ በድምሩ 3577 ምርመራዎች መደረጋቸውን ሲጠቁም፣ ከእነዚህ ውስጥ 69 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈም አስታወቀ። ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 10 ነበር።

ግንቦት 3/2012 በወጣው እለታዊ ሪፖርት ደግሞ በወሩ ውስጥ የታየው የወረርሽኙ የስርጭት መጠን እንደ መጀመሪያው አልነበረም። በዛው ልክ ምርመራውም በዐስር እጥፍ አድጎ 36 ሺሕ 624 ሲደርስ፣ ከዚህ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 250 ነበሩ። በተያያዘ 105 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገግሙ፣ የአምስት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

በዚህ ጊዜ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ማግኘትና መለየት አዳጋች መሆን የጀመረበትና በፍርሃት ሲጠበቅ የቆየው ምንጩ ያልታወቀና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠረው የቫይረሱ ስርጭት የጀመረበት ጊዜ ነው። ያም ወቅት ቢሆን ግን በጥንቃቄ ወረርሽኙን መቆጣጠር እንደሚቻል ይገመትም፣ ተስፋ ይደረግም ነበር። ሆኖም በብዙ አጥፍ እያደገ ከወር ወር የተሻገረው የቫይረሱ ስርጭት ሠኔ ላይ በበለጠ ከፍ ብሎ ተመዝግቧል።

ሠኔ 03/2012 በወጣው የጤና ሚኒስቴር ዘገባ መሠረት፣ እስከ እለቱ ድረስ 158 ሺሕ 521 ምርመራዎች ሲደረጉ፣ ከእነዚህ ውስጥ 2506 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ናቸው። 401 አገግመው በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 35 ደርሷል።

በዚህ ቀጥሎ ሠኔ ወር ወደማብቂያው ሲጠጋ፣ በ22ኛው ቀን በድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት ግርግርና ኹከት ተፈጠረ። ይህም በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ሰልፎችን አስከተለ። አሳዛኝ ድርጊት ከተፈጸመባቸው፣ ልብ የሚሰብር ክስተት ከታየባቸው የግርግሩ ተከታታይ ቀናት በኋላ አንጻራዊ ሰለም ሲሰፍን፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከኖሩበት ተፈናቅለውና ንብረታቸው ወድሞ በእምነት ተቋማት ተጠልለው ተገኝተዋል። ይህና በክስተቱ ምክንያት የተፈጠሩ ኹነቶች የቫይረሱን ስርጭት ምንኛ ያስፋፉታል የሚለው አሁንም ድረስ ስጋቱ እንዳለ ነው።

ይህን ክስተት ተከትሎ ኢንተርኔት መዘጋቱና መቋረጡ መረጃዎች በአግባብ እንዳይገኙ እንቅፋት የሆነ ሲሆን፣ ይህም ከተካሄዱ ሰልፎች ጀምሮ ቫይረሱ ተዘንግቶና ተረስቶ፣ ኹለተኛ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር በጉልህ ያሳየ አጋጣሚ ነው። ሐምሌ 8 ቀን 2012 በወጣ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረትም በድምሩ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 8475 ሲደርስ፣ ከዛ መካከል 148 ሕይወታቸው አልፎ፣ 4768 ያህሉ አገግመው ከለይቶ ማቆያዎች ወጥተዋል።

የዚህ ሰልፍና የሰዎች መጠጋጋት ውጤቱና ተጽእኖው በኋላላይ የሚታይ እንደሆነ ባለሞያዎች እየተናገሩ ሲሆን፣ ሐምሌ 13 እና 14 ቀን 2012 በኹለት ቀናት ብቻ 1008 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። የስድስት ሰዎች ሕይወትም አልፏል።

አዲስ ማለዳ ይህን ዘገባ አጠናቅራ እስካጠናቀቀችበት ሐምሌ 17 ቀን 2012 ማለዳ ድረስ፣ በድምሩ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺሕ 933 ነበር። አዲስ አበባ በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎች የተገኘባት ከተማ ሆናለች። ይህም በመቶኛ ሲሰላ በድምሩ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 75.5 በመቶውን የሚይዝ መሆኑ ተጠቅሷል። መጠኑ ይለያይ እንጂ በክልሎችም በተመሳሳይ የስርጭት መጠኑ ከእለት እለት ከፍ እያለ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።

ያየለው ስጋት
ረቡዕ ሐምሌ 15 ቀን 2012 የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ቫይረስ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስታውቋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሺሕ መብለጡን ያነሳው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ የጽኑ ሕሙማን ቁጥር መበራከቱ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑን ነው ያነሳው። ይህ ጥንቅር እስከ ተጠናቀቀበት ሰዓትም 35 ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ይገኛሉ።

በተለይም ኅብረተሰቡ ስለ ወረርሽኙ በቂ ግንዛቤ ቢኖረውም ራስን ከቫይረሱ ለመከላከል መደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ከመተግበር አንጻር ያለው ክፍተትም እንደ ዋነኛ ችግር ተነስቷል። በተለይም ወጣቱ ለዚህ ተወቃሽ ሆኖ የተነሳ ሲሆን፣ ኃላፊነት የጎደለው የወጣቶች እንቅስቃሴ የቫይረሱን ስርጭት ሊያስፋፋው ይችላልና ሃይ ሊባል ይገባል ተብሏል።

በወረርሽኙ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለባቸው የመጀመሪያ ጊዜያት ተጠቃሽ ምክንያት የነበረው ‹በእለት ገቢ ኑሮን የሚደጉሙ ሰዎች ይበዛሉ› የሚለው ጉዳይ ሲሆን፣ አሁን ግን ከዛ ባለፈ በግዴለሽነት እየተደረጉ ያሉ ኹነቶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው። ለዚህም አዲስ አበባ ነዋሪ በቀላሉ መታዘብ የሚችላቸው ረጅምና የትራንስፖርት ሰልፎችና ርቀታቸውን ያልጠበቁ ሰልፈኞች፣ መሰባሰብን ያልቀነሱ ምግብ ቤቶች፣ የወትሮ ሥራቸውን አድምቀው የቀጠሉ መጠጥ ቤቶች፣በመሰባሰብ የሚታዩ የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታዎች ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።

በተጓዳኝ ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ መገኘቱ ይፋ ከተደረገበት እለት ጀምሮ በመንግሥት የተወሰዱ በርካታ እርምጃዎችና የጥንቃቄ አካሄዶች ነበሩ። እነዚህም ኢትዮጵያ ቀድማ የተገበረቻቸው ከፊል የእንቅስቃሴ ገደቦች ከተለያየ አንጻር ሐሳብ ሲነሳባቸው ቆይቷል። ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ ሰው የሚበዛባቸው የመንግሥት ተቋማት ተጋላጭ የሚሆኑ ለተባሉ ሠራተኞች እረፍት እንዲሰጡ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች የሚጭኑትን ሰው ብዛት እንዲገድቡ የሚልና ወዘተ መመሪያዎች ወጥተው ተተግብረዋል።

እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅት የቫይረሱን ለውጥ ተከትሎ የሚያስተላልፋውን የጥንቃቄ መመሪያዎችም በመከተል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ቀጠሉ። እየቆየ ቫይረሱ አብሮ የሚኖርና የሚዘልቅ መሆኑ እርግጥ ሲሆን ይመስላል፣ መዘጋናቶች እዛም እዚህም መታየት የጀመሩት።

የጤና ሚኒስቴርም በበኩሉ ሠራኋቸው ካላቸው ተግባራት መካከል ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚረዱ 2724 ያህል አምቡላንሶች ለክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ተከፋፍለው ወደ ሥራ መግባታቸው አንደኛው ነው። የለይቶ ማቆያና የለይቶ መታከሚያ ማእከላትም በከተማ መስተዳደሮችና በሁሉም ክልልች የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መሰረት እንዲደራጁና አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት ተደርጓል ሲልም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀደም ሲል ባወጣው ሪፖርት አካትቷል።
በዚህ መሰረት 13,859 የለይቶ መታከሚያ አልጋዎች እና 3,576 ደግሞ የለይቶ ማቆያ አልጋዎች በአጠቃላይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ 17,435 አልጋዎች አሉም ተብሏል። እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዘገባ፣ የላብራቶሪ ዝግጅትን በተመለከተ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ናሙና ምርምራን እያደረጉ ያሉና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ የገቡ 32 የምርመራ ማእከለት ያሉ ሲሆን፣ በእነዚህም በቀን እስከ 8000 የሚደርስ የምርመራ አቅም ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተጠቅሷል።

በተመሳሳይ በዝግጅት ላይ ያሉ ላብራቶሪዎች የጨመሩ ሲሆን፣ በቀጣይ የባለሙያና የምርመራ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በቀን የምርመራ አቅምን ወደ 15 ሺሕ የማድረስ እቅድ እንዳለም ነው መሥሪያ ቤቱ ያስታወቀው።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ አሁን ላይ (እስከ ሐምሌ 17 ማለዳ ባለው መረጃ መሠረት) 357,058 የላብራቶሪ ናሙና ምርመራዎች ተካሂደዋል። ግንዛቤ ማስጨበጥና መረጃን በማድረስ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በተመለከተ ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ጋር የጋራ መደበኛ የግንኙነት አግባብ በመፍጠር ለማኅበረሰቡ ትምህርት ሰጪ መረጃዎችን በመደበኛነት የማድረስ ሥራ ተሠርቷል ሲልም መሥሪያ ቤቱ በዘገባው አካቷል።

በዚህም አሁን ላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም መሻሻሎች ቢኖሩም በትክክል ከመጠቀም አኳያ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። እንዲሁም ርቀትን ከመጠበቅ አንጻር እየታየ ያለው መዘናጋትና ቸልታም በፍጥነት ሊታረም እንደሚገባ አደራ ተብሏል።

የጥንቃቄ ነገርስ?
አዲስ ማለዳ በዚህ መዘናጋት ዙሪያ በተለይም ቫይረሱ ኢትዮጵያ በገባ የመጀመሪያ ሰሞን ያሬድ ሹመቴን እንግዳ ባደረገችበት ወቅት ይህን የመዘናጋት ጉዳይ አንስታ ነበር። ‹ቅድሚያ ለሰብአዊነት – የሰብአዊነት ድጋፍ ጥምረት› የተሰኘ የድጋፍ አሰባሳቢ ኅብረትን ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የመሠረተውና የሚያስተባብረው ያሬድ ታድያ፣ በጊዜው ስለነበረው መዘናጋት ሲያነሳ ያለውንና የሚፈጠረውን ወይም ሊፈጠር ያለውን ማኅበራዊ ቀውስ በማጉላት እንዲህ ሲል አስረድቶ ነበር፤
‹‹…አንድ ሰሞን ቀርቶ የነበረው እንቅስቃሴው አሁን ደምቆ የታየው ለምንድን ነው ስንል፣ ይህ ለእኔ ማኅበራዊ ቀውስ ለመፈጠሩ አንዱ ማሳያ ነው። ቤቱ መቀመጥ ስላልቻለ ብሞትም ልሙት ብሎ ሰው ወደ ሥራ እየገባ ነው። ይህን መታዘብ የምንችልበት ግን እውናዊ የሆነ ማረጋገጫ የለም። መንገድ ላይ የምታገኚውን ሰው እያንዳንዱን ካላናገርሽ በቀር።

ተዘግተውና ቆመው የነበሩ፣ ከቤት መውጣትን የሚጠይቁ የሥራ ዘርፎች፣ በተለይ የእለት ገቢ የሚገኝባቸው ሥራዎች ተመልሰው ወደ መከፈት የሄዱት፣ ቤት ውስጥ በመቀመጥ ምክንያት እየደረሰ ባለው የምግብ ዋስትና ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ አድርጎ የሚተነትንና የሚያጠናም ያስፈልገናል።››

ቫይረሱ ከተከሰተበት ወር ማግስት ጀምሮ ቀስ በቀስ እየጨመረ የመጣው መዘናጋትና ወደ እንቅስቃሴ የመግባት ሁናቴ አሁን አይሎ፣ በየእለት የሚወጣው ዘገባ ባይኖር ቫይረሱ ከነአካቴው መኖሩን በቶሎ የሚረሱ እንደሚኖሩ አያጠራጥርም።

በጊዜው ታድያ ያሬድ በዚህም ላይ አክሎ፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ሰው አይሰማም የሚል ትንታኔ ትክክል አይመስለኝም። በሌላው ዓለም ሰዎች በፖሊስ በግድና በዱላ እየተደበደቡ አትውጡ ሲባል እናያለን። እንደዛ በሕግ ግዳጅ ከመጣ እኛም አገር ግርፊያው አይቀርም። ምክንያቱም አትውጣ ቢባል ቤት ለመቀመጥ የሚያስችል የተረጋጋ የገቢ ምንጭ የሌለው ሰው ያንን ማድረግ አይችልም። ስለዚህ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን፣ ተቋማት በአሁን ሰዓት ያለውን ነገር አጥንተው መግለጥ አለባቸው።›› በማለት ምክረ ሐሳቡን ጭምር ነበር የለገሰው።

ይህ ኦኮሚያዊ ጫና በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከሚያስከትለው ተጽእኖ አንጻር የታየ ሲሆን፣ በተጓዳኝ የሰዎችንም ጤና ማንሳታችን ነው። ታድያ በዚህ መሠረት ሰዎች የየእለት ተግባራቸውን ለመፈጸም በመገደዳቸውና የእለት ጉርሳቸው በእለት ገቢያቸው ላይ ጥገኛ በመሆኑ ወደሥራ ሲገቡ፣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚተላለፈውን መልእክት የማይሰሙት ስለምን ነው? ይህ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙን መቆጣጠር ዳገት በሆነባቸው የዓለም አገራት ሁሉ የሚቀርብ ጥያቄ ነው።

መከላከልና መቆጣጠር ምን ደረሰ?
ከላይ እንደተነሳው ቫይረሱ የስርጭት መጠኑ ከወር ወር ከፍ እያለና እያየለ ቀጥሏል። በዚህም ላይ የተከሰቱ አለመረጋጋቶችና ቀውሶች፣ አሁንም ተፈናቅለው የሚገኙ በርካታ ዜጎች መኖራቸውና ተያያዥ ጉዳዮች፣ የቫይረሱን የስርጭት መጠን ከዚህም በላይ እጥፍ ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ስጋት ይሰማል።

በጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በሚኒስቴሩ በኩል ኅብረተሰቡ ዘንድ የታየው መዘናጋት ጉዳቱን እጥፍ ያደርገዋል የሚል ስጋት አለ። ተገኔ አያይዘውም ቫይረሱ አገር ውስጥ በታየ የመጀመሪያ ሰሞን የነበረውን ጥንቃቄ አውስተው፣ ያ የነበረ ትኩረትና ጥንቃቄ አሁን እንደሌለ ነው ያነሱት። ይህም ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት ምናልባትም በእጥፍ ሊያሳድገው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

እዚህ ላይ የሕግ አስከባሪ አካላትን ድርሻም ጠቅሰው ነበር። በሕግ አስከባሪ አካላት በኩል ብዙ ሰዎች የሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ላይ፣ መጠጥና ጭፈራ ቤቶች አካባቢ እንዲሁም መሰል ስፍራዎች ላይ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ይደረግ ነበር ብለዋል።

ታድያ ይህን በሚመለከት አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች። እርሳቸውም ክትትሉ አሁንም እንዳለ፣ አልፎም እርምጃ መውሰድ ላይም ተጠናክሮ መቀጠሉን አፅንኦት ሰጥተው አንስተውታል።

እንደ ኢንስፔክትር ማርቆስ ገለፃ የኅብረተሰቡ መዘናጋት እና ችላ ማለት የፖሊስን ቁጥጥር መጠበቅ አስፈላጊ አድርጎታል። ይሁን እንጂ ለገዛ ጤንነቱ በማሰብ ኅብረሰተቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባ ነበር።ነገር ግን ከዚህ ይልቅ እንደውም በአንዳንድ የመዝናኛ ቦታዎች እና በጎዳናዎች ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን እና የሚያስከትለውን የከፋ ጉዳት የመዘንጋት አልፍ ሲል ጠፍቷል ብሎ የማሰብ ስሜት እየተስተዋለ እንደሆነ መታዘባቸውን ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል።

አሁንም ሕጉና መመሪያው አለ ያሉት ኢንስፔክተሩ አሁንም በሕጉ መሠረት ማስክ ወይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችእንዲሁም በየቦታው ከአራት ሰው በላይ ተሰብስበው አልያም መጠጥ ቤቶች ተከፍተው ሕዝብ ተሰባስቦባቸው ቢገኙ፣ አሁንም ተጠያቂ እንደሚሆኑ እና ፍርድ ቤት ቀርበው ከአምስት ሺሕ ብር ገንዘብ ቅጣት እስከ ዐስር ሺሕ ብር ድረስ የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ማርቆስ እንዳስረዱት ታድያ ፖሊሰች ይህን የቁጥጥር ሥራ እየሠሩ ያሉት ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ ነው። እናም ይህ ጉዳይ የበለጠ ሸክም እየፈጠረ መሆኑን ነው ያነሱት። አብዛኛው ሰውም ጭንብሉን ሳይቀር የሚያደርገው በአካባቢው ፖሊስ ሲያይ ነው። መጠጥ ቤቶች ሳይቀሩ ጠቋሚ ሰው አስቀምጠው ምልክት ሲሰጣቸው ይዘጋሉ። ይህ ሁሉ ግን ተገቢ እንዳልሆነና ኅብረተሰቡ ለራሱ እንዲሁም ለአገር ሲል ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ከመዘናጋትም እንዲታቀብ ብለዋል።

አዲስ ማለዳ የመዘናጋቱን ጉዳይ አውድ አድርጋ እየተደረጉ ያሉ የመለካከልና የመቆጣጠር ሥራዎች እንዴት ናቸው ስትል ጠይቃ ነበር። እስከ ሠኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ድረስ በጤና ሚኒስቴር በኩል ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ነበሩ ተብሏል።

ይህን በሚመለከት ሐሳብ የሰጡት ቀደም ባለው ወር ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው ናቸው። በማኅበረሰቡ በኩል ያለው መዘናጋት እንዳለ ሆኖ፣ እንደ አገር ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው አካሄድ እንዴት ይታያል ስትል አዲስ ማለዳም ለኃላፊው ጥያቄ አንስታ ነበር።

እርሳቸውም በመንግሥት የተወሰዱ በአገር አቀፍ ደረጃ መልካም እርምጃዎች ቢኖሩም መሻሻል ያለባቸውም እንዳሉ ነው ያነሱት። ወረርሽን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት በቂ ነው ማለት የሚቻለው የበሽታውን መስፋፋት መቀነስ ሲቻል መሆኑንም አውስተዋል።

‹‹ጥረታችንን መመዘን ያለብን ከውጤት አንጻር ነው። ይሄ ቫይረስ ከባድ ቫይረስ ነው። አይደለም እንደ እኛ ደሃ እና ብዙ ያላደገ የጤና ስርዓት ያለው፣ ያደጉና ገንዘብ እንዲሁም በጣም ብዙ ባለሞያ ላላቸው አገራትም ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ አይተናል።›› ብለዋልም።

ከወረርሽኙ ከባድነት አንጻርም የመንግሥት እንዲሁም የኅብረተሰቡ ምላሽ ያንን የሚመጥን መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል። ‹‹የምንፈልገውን እስካላገኘን ድረስ፣ የፈለገውን ያህል ብንሮጥም ከዛም የበለጠ መሮጥ እንዳለብን ነው።›› ሲሉም እስከመጨረሻው ጥረቶች መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተመሳሳይ ማኅበረሰቡን በማንሳት መጀመሪያ አካባቢ የነበረውን ጥንቃቄ አስታውሰው እያደር እጅ መታጠብ ሳይቀር ምን ያህል ቸል እየተባለ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረጉ መልካም ሆኖ ሳለ፣ ያም ሆኖ አጠቃቀም ላይ በትክክል የሚመከረው መንገድ አለመከተል አለና ያም ማሻሻል ይፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።

‹‹አጠቃቀም፣ አወጋገድና አደራረግ ላይ መሻሻል አለብን። ብዙ ሰው አፍንጫውን ሳይሸፍን ዝቅ ያደርጋል። ማስኩን ይዞ ፖሊስ ሲይይ ለመሸፈን መሞከርም ጥቅም የለውም።›› ሲሉ በሰዎች ዘን እየታዩ ያሉ ትንሽ የሚመስሉ ስህተቶች ብዙ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ ብለዋል።

አያይዘውም እንዲህ አሉ፣ ‹‹ትልቁ ጉድለት ያለው ርቀትን መጠበቅ ላይ ነው። እንደ አገር የእለት ጉርሱን ለማግኘት የቀን ሥራ መሥራት በሚያስፈልግበት ቦታ፣ ሰውን ሁሉ ቤትህ ተቀመጥ ማለት አስቸጋሪ ነው። ሰው ማድረግ እየቻለ አላደረገውም ብዬ የማስበው፣ ግድ ብሎ ከቤት ከወጣ፣ ከዛ በኋላ በተቻለ መጠን ርቀት መጠበቅን ነው። ስለዚህ በማኅበረሰብ ደረጃ ሁሉም ካላስተካከለ፣ በሽታውን መቆጣጠር አይቻልም።››

ተግባር ደጋግመው ሲያሳስቡ የነበሩት ጉዳይም ወረርሽኙ የተወሰኑ ሰዎች ጥንቃቄ በማድረጋቸው ብቻ መቆጣጠር የሚቻል ስላልሆነ ሁሉም ሰው የሚመከረውን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ነው። ይህም ቢያንስ በሽታውን የመቆጣጠር ደረጃችንን ከፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የሐኪሞች ፈተና
የዓለም ጤና ድርጅት ባሳለፍነው ሐሙስ ሐምሌ 16/2012 ባወጣው ዘገባ በአፍሪካ ከ10 ሺሕ በላይ የጤና ባለሞያዎች በኮቪድ 19 መያዛቸውን ነው። ይህም በአርባ አገራት የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ግንባር ላይ የሚገኙ ተዋጊዎችን እንደማጣት ለአፍሪካ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትል ነው ድርጅቱ ስጋቱን የገለጸው።

በአፍሪካ በአሁን ሰዓት ከ750 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ በግንባር ቀደምነት ትገኛለች። በቫይረሱ ምክንያት የተከሰተ ሞት ብዛትም 15 ሺሕ የላቀ ሲሆን፣ ይህ ሁሉ በተከታዮቹ ወራት ይደርሳል ተብሎ የተፈራውንና ቀድሞ የተተነበየው ከፍተኛ የስርጭት መጠን ላይ በፍጥነት የሚያደርስ እንደሆነ ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል።

በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞቲ በአፍሪካ እየታየ ያለው የኮቪድ 19 ተጠቂ ብዛት በአኅጉሪቱ ባለው የጤና ስርዓት ላይ የባሰ ከባድ እንቅፋት የሚሆን ነው ብለዋል። ከጤና ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ የሕክምና ባለሞያዎች በዚህ መጠን ባቫይረሱ መያዝ የባሰ ለዚህ ምስክር የሚሆን የለም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በድምሩም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ 10 በመቶ የጤና ባለሞዎች ናቸው። ይህ ቁጥር ታድያ በአገራት ሲከፋፈል ከፍተኛውን በመያዝ አፍሪካ ሳትቀድም እንደማትቀር ነው የተገለጸው። እንደማሳያም ያሉት በ14 የአፍሪካ አገራት ብቻ እንኳ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎ ውስጥ 5 በመቶው የሕክምና ባለሞያዎች መሆናቸው ነው።

እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከሆነ ይህን የሚያባብሰው የመከላከያ ግብዓት በበቂ አለመሟላት፣ ዓለማቀፍ የእንቅስቃሴ ገደቦች መኖራቸው ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ እንዳይዳረሱ ማገዱ፣ የመከላከልናና መቆጣጠር ሥራ ላይ ያለው ድክመት ተጠቃሽ ሆነዋል።

በተመሳሳይ ቫይረሱ ከእለት እለት እያሳየው በመጣው ለውጥ ታማሚዎች የሕመሙ ምልክት ላየታይባቸው የሚችል ደረጃ ደርሷል። ይህም መሆኑ ለተለያዩ በሽታዎች ሕክምና ለማግኘት የሚሄዱ ሰዎች ሳያውቁት ቫይረሱ ኖሮባቸው ለሌላ ሰው እንዲያስተላልፉ ሊያደርግ ይችላል። በዚህም ምክንያት የሕከምና ባለሞያዎች የበለጠ ተጋላጭና ተጠቂ ናቸው።

ምን ይበጃል?
ባለንበት የክረምት ወቅት የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ለጥንቃቄም ትኩረት እንዲሰጥ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ደጋግመው ማሳሰባቸውን አልተዉም። ከውጪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የሚገቡ ሰዎችን በሚመለከት ጥንቃቄዎች የበረቱ ሲሆን፣ ተጓዦች ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ይዘው እንዲገቡና የሙቀት ልኬት ተደርጎላቸው እንዲያልፉ እንዲሁም በቤታቸውም 14 ቀናት ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ መደረጉም ይታወቃል።

አሁን ላይም በማኅበረሰብ ውስጥ ቫይረሱን የመከላከያ መንገዶችን ሙሉ ለሙሉ ከመተግበር አኳያ ግዴለሽነትና ቸልተኝነት ይስተዋላል የተባለ ሲሆን፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት እርምጃዎችንና መመሪያዎችን በሚገባ አለመተግበር፣ በየብስ ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ በሮች (ድንበሮች) ለመቆጣጠር ይደረግ የነበረው ጥረት ክፍተት እንደታየበትም ጭምር ተነስቷል።

ይህንንም ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የመነጋገርና የመፍታት ሥራ እየሠራ መሆኑንም ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
አዲስ ማለዳ በዚህ ሐተታ መግቢያ ላይ ታሪካቸውን ያካፈለችው አየለ በበኩላቸው በዚህ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ፣ መገናኛ ብዙኀንና በማኅበራዊ ሚድያዎች የሚሠሩ ተደማጭነት ያላቸው አካላት እንደመጀመሪው ሰሞን እንደውም ከዛም ከፍ ባለ ሁኔታ ቅስቀሳ ማድረግ እንዳለባቸው እንደሚያምኑና እንደዛም ቢደረግ የተወሰነ ለውጥ ሊመጣ እንደሚቸል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ሰዉ ወቅታዊ አሳዛኝ አገራዊ ኹከትና ቀውሶችን ታዝቧል የሚሉት አየለ፣ ይህም በሥነልቦና ላይ የሚያደርሰው ጫና እንዳለ ሆኖ ራስን ከቫይረሱ ከመጠበቅ በላይ አሳሳቢ ጉዳዮች እንዳሉ በማሰብ ቸል ብሎ ይሆናል የሚል ዕይታ አላቸው። እናም የኪነጥበብ ባለሞያዎች መጀመሪያ ያደርጉት እንደነበር፣ መገናኛ ብዙኀንም ጉዳዩን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ቢቻል በተለየ መንገድና አቀራረብ ማኅበረሰቡን መቀስቀስና ያለውን ስጋት ማሳየት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹መጀመሪያ ያሳስበን የነበረው ቫይረሱ አይዘንም የሚል የተሳሳተ መረጃን መሠረት ያደረገ ሐሳብ ነበር። በኋላ ደግሞ ስጋቱ አይሎ አንዳንድ ሰዎች ከጭንቀት የተነሳ ወደ ሆስፒታል መሄድን ሳይቀር እርግፍ አድርገው ትተው ሌላ ችግር ተከሰተ። አሁን ደግሞ ስለቫይረሱ በሚገባ መረዳት ቢኖርም መዘናጋትና ቸልታ ይታያል። ስለዚህ ቸል አትበሉ የሚለውን መልዕክት በተለየ አቀራረብ ማድረስ ያስፈልጋል።›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ይህም የብዙ ባለሞያዎችና ሰዎች ምክረ ሐሳብ ነው። አሁን የቫይረሱ ስርጭት በማኅበረሰብ ደረጃ እየተስፋፋ ስለሆነ ሁሉንም የመከላከያ መንገዶች ያለመዘናጋት መተግበር ያስፈልጋል። አሁንም አስገዳጅ ነገር ካልሆነ ወይም ካላጋጠመ በቀር ቤት ውስጥ መቆየት፣ አካላዊ ርቀታችንን በሚገባ መጠበቅና ያንንም ተግባራዊ ማድረግ፣ በየትኛውም ሁኔታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ እጃችንን ዘወትር በንጹህ ውሃና ሳሙና በሚገባ መታጠብ። እነዚህ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመከላከል ይረዳልና፣ አሁንም ቸል አንበል፣ የባለሞያዎቹ እንዲሁም የአዲስ ማለዳም መልእክት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here