ኤችቱ (H2) የቋንቋ ትምህርት ቤት ባለቤት 84 ሚሊዮን ብር “አጭበርብረው” ተሰወሩ

0
1150

ኤችቱ(H2) የቋንቋ እና የኮምፒተር ትምህርት ቤት ከ100 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦችን የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ አጭበርብሮ እንደጠፋባቸው ተበዳዮች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የትምህርት ቤቱ ባለቤት የሆኑት ሀፍቶም ኃይሌ ከአንድ ወር በፊት ቁጠራቸው ከ100 በላይ የሆኑ ተበዳዮችን ገንዘብ በብድር እና የድርጅቱ ተጋሪ ትሆናላችሁ በማለት ከግለሰቦች ብር በመቀበል ድንገት አድራሻቸውን አጥፍተው እንደተሰወሩባቸው ተበዳዮች ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ትምህርት ቤቱ ባለቤት የገንብ ማጭበርበር ወንጀል ሰርቶብናል በማለት አስካሁን ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሰዎች ቁጥር ከ120 ያለፈ ሲሆን፣ እስካሁን ገንዘብ ተጭበርብረናል ብለው የተሰባሰቡ ሰዎች ብር መጠን በቲንሹ ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ከተበዳዮቹ ውስጥ አንዷ የሆኑት ሚሚ ሳህለ በደላቸውን ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት ከሆነ፣ የኤችቱ ቋንቋ እና ኮምፒተር ትምህርት ቤት ባለቤት ሀፍቶም ኃይሌ“የድርጅቱ ተጋሪ ወይም ባለድርሻ ትሆኛለሽ በማለት አራት ዓመት በውጭ አገር ያፈራሁትን ገንዘብ 180 ሺህ ብር በመቀበል እና በድርጅቱ ውስጥ ሰራተኛ ሆኘ እንዳገለግል ተስማምተን የ180 ሺህ ብር ደረቅ ቸክ ሰጥቶኝ፣ በእምነት የድርጅቱ ተጋሪ እሆናለሁ ብየ ስለፋ በ180 ሺህ ብሬ እና የአንድ ወር ደምወዜን ቀምቶኝ ተሰውሯል።” ሲሉ ደረሰባቸውን ጉዳት በምሬት አስረድተዋል። ሚሚ አክለውም ሀፍቶም በተሰወሩ ሰሞን በሰልክ ደውለው የቤት ኪራይ ብር እንኳን እንዲልኩላቸው ቢማጸኗቸውም እልክልሻለሁ ብለዋቸው በዚያው ቤተሰባቸውን እና የራሳቸውን ስልክ አጥፍተው እንደጠፉባቸው ተናግረዋል።

ሚሚና መሰል ተበዳዮች በሰላሙ ጊዜ ሀፍቶም የሰጧቸውን ደረቅ ቸክ ይዘው ወደ ባንክ ቢያመሩም ባንክ በሀፍቶም ኃይሌ ስም የተመዘገበ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ውስጥ ምንም አይነት ገንዘብ እንደሌለው እንዳረጋገጠላቸው ጠቁመዋል። ሌሎችም በውል እና በማስረጃ ለሀፍቶም ገንዘብ ያበደሩ ተበዳዮች ገንዘባቸውን የሚመልሰበት ሁኔታ አስከ አሁን ድረስ እንዳላገኙ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ተበዳይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደተጭበረበሩ ተናግረዋል።ተበዳዩ አክለውም “የተፈጸመብን አደገኛ የሆነ፣ ተደርጎ የማያውቅ ታሪካዊ ጥፋት ነው።” ሲሉ የደረሰባቸውን በደል አስረድተዋል።

ተበዳዮች ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት የትምህርት ቤቱ ሰራተኞች የነበሩ ሰዎችም ደምወዝ እንዳልተከፈላቸው እና ትምህርት ቤቱ ባለቤት በማጭበርብር ከአነስተኛ የገንዘብ ተቋም(micirofanance) በስማቸው በማሰፈረም ገንዘብ ተበድረው ባለ እዳ አድረገዋቸው እንደተሰወሩ ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ እንዳረጋገጠችው ሀፍቶም በተበዳዮች ላይ የሰሩት ማጭበርበር ተግባር ከሰራተኞች እና ከአበዳሪዎች አልፎ ከ አንድ ሺህ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የተደራጀ የማጭበርበር ስራ እንደፈጸሙ ተጠቁሟል። ምንጮች እንደገለጹት የትምህርት ቤቱ ሰራተኛ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመው የማጭበርበር ስራ የድርጅቱ ሰራተኞች እንደሆኑ በማስረዳት ከአነስተኛ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት በማስፈረም በስማቸው ገንዘብ ተበድሮ የብድሩ እዳ ከፋይነት ጉዳዮን ምንም ለማያውቁት እና የጥቅም ተጋሪ ላልነበሩት ግለሰቦች ማውረስ መሆኑ ተመላክቷል።

ተበዳዮች ፍትህ ለማግኘትና የተጨበረበሩትን ገንዘባቸውን ለማስመለስ ኮሚቴ በማቋቋም በፍትብሔር ህግ እና በሀፍቶም ቤተሰቦች በኩል ሽማግሌ ልከው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ሲሆኑ፣ አንዳንዶች የደረሰባቸውን በደል ለመናገር የሀፍቶምን በህግ ቁጥጥር ስር መዋልና ገንዘባቸውን የመግኘት እድል እንደሚያጠበው በመፍራት በደላቸውን ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አልገለጹም።

ኤችቱ የቋንቋ እና ኮምፒተር ትምህርት ቤት በአዲስ አበበባ እና በክልል ከተሞች የቋንቋ እና የኮምፒተር ስልጠናዎችን እና ትምህርቶችን ሲሰጥ የነበረ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ በመገናኛ ቤቴልሄም ፕላዛ ሶስተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ዋና ቢሮው መታሸጉን ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። የአራት ወር የቤት ኪራይ እንዳልከፈለም ተረጋግጧል። ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሙሉ በሙሉ መታሸጋቸውን አሁን ተበዳና የተቋሙ ሰራተኛ የነበሩት ሚሚ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

አዲስ ማለደ ጉዳዮን በሚመለከት ወደ ኤች ቱ ቋንቋ እና ኮምፒውተር ማሰልጠኛ ተቋም ባለንብረት ወደ ሆኑት ሐፍቶም ኃይሌ ያደረገችው ስልክ ጥሪ እና አጭር የጽሑፍ መልዕክት በዕጅ ስልካቸው ዝግ መሆን ምክንያት ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here