የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በ2012 ከዕቅዱ በላይ የስራ ዕድል መፍጠሩን አስታወቀ

0
1465

የኢፌድሪ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በ2012 የበጀት አመት ለማሳካት በዕቅድ ከያዘው ሦስት ሚሊዮን የስራ ዕድል የመፍጠር ትልም ከዕቅድ በላይ በማሳካት የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታወቀ።

የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ 3 ሚልዮን የስራ እድል እንፈጥራለን ብለን በዚህ አመት ስራ ስንጀምር በቅድሚያ የሰራነው ነገር እያንዳንዱ ክልል ባለው የስራ አጥ ምጣኔ መጠንና ባሉት የወጣቶች ቁጥር መጠን የሚጠበቅበትን በማከፋፈል ነው ብለዋል። ኮሚሽነሩ አያይዘውም በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልል 1 ሚልዮን የሚደርሰውን የስራ እድል የመፍጠር ሀላፊነት፣ አማራ ክልል 700 ሺህ፣ የደቡብ ህዝቦች እና ብሄር ብሄረሰቦች ክልል 600 ሺህ እንዲሁም እንደ አዲስ አበባ ላሉ ከተሞች 250 ሺህ እያለ ለእያንዳንዱ ክልል ባለው ምጣኔ እና የወጣት ቁጥር ብዛት ተከፋፍሏል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ፣ ኦሮሚያ ክልል እንዲሁም አማራ ክልል ከእቅድ በላይ የሆነ አፈፃፀም ማሳየታቸውም ኤፍሬም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

የስራ ፈጠራ እንቅስቀሴዎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው በትክክል እየተገመገሙና እየተመሩ እንዲቀጥሉ ማድረግ ስለተቻለ በዚህ አመት ካታቀደው 3 ሚሊዮን የስራ እድሎችን የመፍጠር እቅድ ውስጥ ከፍ ባለ የስራ አፈፃፀም 3ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆን የስራ እድል ለመፍጠር የተቻለ ሲሆን ከእነዚህም 62 በመቶ የሚሆኑት ቋሚ እንዲሁም 38 በመቶዎቹ ደግሞ ጊዜዊ ወይንም ከአንድ አመት በታች የሚቆዩ የስራ እድሎች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ከእነዚህም 3ነጥብ 3 ሚሊዮን ከሚሆኑት የስራ እድሎች ውስጥ በኮቪድ 19 ተፅእኖ ምክንያት 330 ሺህ የሚገመቱ ስራዎች መክሰማቸውንም ገልፀው በዚህም ምክንያት ጠቅላላ አፈፃፀሙ ወደ 3 ሚሊየን መጠጋቱን አፍሬም አስታውቀዋል፡፡

በመላው አገሪቱ የሚፈጠሩ ስራዎች ዘላቂነት ይኖራቸው ዘንድ በ2012 ዓ.ም 3 ሚሊዮን፣ እስከ 2017 በጀት ዓመት 14 ሚሊዮን፣ እስከ 2022 በጀት ዓመት 20 ሚሊዮን የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸት እና ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኤፍሬም ተክሌ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ አንድ አመት ታኩል ያስቆጠረ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የስራ እድል ፈጠራ ስራ የማስተባበር፣ የማቀናጀት እንዲሁም ተገቢውን ድጋፍ የመስጠት ስራ ከተቋቋመበት ዋንኛ አላማዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ ስራዎች በጠቅላላ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠ/ሚኒስቴር የሚመራ፤ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ፕሬዝዳንቶችና ከንቲባዎች እንዲሁም በአስተዳደር ስራ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሚኒስትሮች የተካተቱበት የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት መሪ ኮሚቴ መቋቋሙን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ ይህም መሪ ኮሚቴ የበጀት አመቱ ሲጀመር ባደረገው የመጀመሪያ ውይይት በአገራችን ውስጥ ለሚሰራው ስራ አንደኛው የስኬታችን ትልቁ መለኪያ ለህዝባችን የምንፈጥረው የስራ እድል እንደሆነ በግልፅ መስማማት ላይ እንደደረሰ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም እያንዳንዱን የስራ ፈጠራ አጀንዳ የሚያስተባበር እና የስራ እቅድና አፈፃፀምን የሚገመግም እንዲሁም አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ 41 አባላት ያሉትና በኢ.ፌ.ድ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚመራ የስራ እድል ፈጠራ ብሄራዊ ምክር ቤት መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የስራ እድል ፈጠራ ብሄራዊ ኮሚቴ የሚወሰኑ ዋና ዋና ውሳኔዎችን የሚያስፈፅሙ በስራ እድል ፈጠራ ውስጥ ጉልህ ሚናን የሚጫወቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተና በስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽኑ የሚመራ የዋና ዋና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ኮሚቴ መቋቋሙን አፍሬም ገልፀዋል፡፡

የስራ እድል ፈጠራ የሁሉም ሰው ስራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የፌደራል እና የክልል መንግስታትን ቅንጅት የተሻለ ለማድረግ በየሶስት ወሩ እየተገናኘ የዘርፉን እቅድና አፈፃፀም የሚገመግምና የሚመራ የፌደራልና የክልሎች የስራ ዕድል ፈጠራ አካላት የጋራ መድረክ ተቋቁሞ ሁሉም አካላት የስራ እድል ፈጠራን በአጀንዳነት ይዘው እንዲሰሩ መደረጉም ተገልጿል፡፡

ይህም በአመቱ ከታቀደው እጅግ ከፍተኛ የሚባል አፈፃፀም ነው ያሉት ኮሚሽነሩ በስብጥር ደረጃ ስንመለከት ግን የሴቶች ተጠቃሚነት እጅግ ዝቅተኛ የሆነና ከጠቅላላ ተጠቃሚዎች ውስጥ አንድ ሶስተኛ ወይንም 35.5 በመቶ የሚይዝ ሲሆን ይህም 1.2 ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን ወንዶች ደግሞ ቀሪውን 64.5 በመቶ ደግሞ ወንዶችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የስራ እድል ፈጠራው በቦታ እና አካባቢ ሲታይ ደግሞ 48 በመቶ የሚሆነው በገጠር ሲሆን ቀሪው 52 በመቶ ደግሞ በከተማ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ ስራውን ለመደገፍ የሚሆን ሀብትን ከተለያዩ አካላት ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረትም በበጀት አመቱ 500 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በተደረገ ስምምነት 384.9 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ከ22 የልማት አጋሮች ጋር አጋርነት ለመፍጠር ታቅዶ ከ10 ለጋሽ፣ 5 ተራድዖ እና 5 የግሉ ዘርፍ አካላት በድምሩም ከ22 አጋር አካላት ጋር ስምምነት መፈረሙን ከመግለጫው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ የስራ እድሎችን ለማመቻቸት በሚደረገው ጥረት ስራ የመፍጠር አቅም ኖሯቸው ብዙ ያለተሰራባቸውን ሴክተሮች ላይ ከ3 እስከ 5 አመታት የሚዘልቁ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ለ128.000 ሰዎች የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኮሚሽኑ ድጋፍ የተጀመሩ 5 የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ኤፍሬም ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በጋራ በመሆን በአጠቃላይ 1.3 ሚሊየን የስራ ዕድሎችን በ 5 አመታት ውስጥ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በ2012 በጀት አመት የሚሰበሰበው የስራ መረጃ ጥራት ከፍ እንዲል እና የመረጃ አያያዝ ጥራትን ለመጨመር ስራ ፈላጊዎችን የሚመዘግብ የሞባይል መተግበሪያ (#etworks) እንዲሁም የውጪ አገር የስራ ቅጥር መመልመያና ስምሪት መመዝገቢያ ሶፍትዌር መዘጋጀቱን ያስታወቁት ኮሚሽነሩ እስካሁንም 16,000 የውጪ አገር የስራ እድሎች መፈጠራቸውንም ገልፀዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here