ኹለት አዳዲስ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

0
785

በተጨማሪም 18 ማይክሮ ፋይናንሶች በምሥረታ ሂደት ላይ ናቸው

ካሉብ እና ካፊ የተሰኙ አዲስ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማሟላት የሚገባቸውን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ከሠኔ ወር 2012 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት 39 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የነበሩ ሲሆን የኹለቱ ተቋማት መጨመርን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት 41 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አስፋው አበራ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በሠኔ ወር 2011 በቁጥር 34 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የነበሩ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 7 ተጨማሪ ተቋማት በመጨመራቸው የተቋማቱ ቁጠር ወደ 41 ሊያድግ መቻሉም ታውቋል።

ካሉብ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና መሥሪያ ቤቱን ጅግጅጋ ላይ በማድረግ አገልግሎት መስጠቱን የጀመረ ሲሆን፣ ካፊ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ደግሞ አዲስ አበባ እንደሚገኝ አስፋው ጠቅሰዋል። ኹለቱም ተቋማት በመላው ኢትዮጵያ ለመሥራት በማቀድና የመነሻ መቋቋሚያ ገንዘብ በዝግ ሒሳብ 10 ሚሊዮን ብር በማሟላታቸው ፈቃዱ እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ተቋማቱም በመደበኛ የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት የሥራ አዋጅ ስር በተቀመጠው ሕግ እና ደንብ መሰረት አዋጁ የሚፈቅድላቸውን አገልግሎቶች ማለትም የቁጠባ፣ የብድር እንዲሁም የሐዋላ እና ሌሎችም አገልግሎቶችን እንደሚሰጡም ታውቋል።

ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ጐን ለጐን በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ የሚባሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በተለይ ለአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች የብደር አቅርቦት ምንጭ በመሆን እያገለገሉ እንደሚገኙም ታውቋል።

በቀጣይም አሁን ካሉት በተጨማሪ ሌሎች በመቋቋም ሂደት ላይ ያሉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለፁት አስፋው፣ ነገር ግን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተለያዩ ስብሰባዎችን፣ የባለአክሲዮን እና የመሥራቾች ጉባኤን ለማድረግ እንዳልተቻለ አንስተዋል። ሆኖም በአሁኑ ሰዓት በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ 18 የሚደርሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም በምሥረታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አስፋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የተቋማቱ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ በክልሎች አሁን ያሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እና ባንኮች በየገጠር ከተሞች ዘልቀው የመሥራት እና በርካታ ደንበኞች ጋር የመድረስ አቅማቸው የተገደበ በመሆኑ እየተጨመሩ ያሉት አዳዲስ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለውን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ብለዋል።

በአጠቃላይ የ2012 የዘጠኝ ወራት የአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ትርፍ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡን አስፋው አስታውቀው፣ ይህም ከባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ትርፍ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ21.7 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም ገልፀዋል።

የተቋማቱ ትርፍ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዋናነት ይሄ ትርፍ የተገኘው በብድር ከሚገኝ ወለድ መሆኑን አስታውቀው፣ እንደ ተቋም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአገሪቱ አለመረጋጋት እና የብድር በጊዜው አለመመለስ እንደተግዳሮት ሊነሳ እንደሚችልም አስረድተዋል።

በ2012 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ላይ የነበሩት 38 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 66.6 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጡ ሲሆን፣ አጠቃላይ የተቀማጭ ሒሳብ ገንዘባቸው 41.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

በሪፖርቱም የተቋማቱ አጠቃላይ ሀብት በ20 በመቶ አድጎ 85.7 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተጠቅሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here