ኹከቱ ወረርሽኙን እንዳያስረሳን !

0
686

ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ አብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች፣ መዲናዋ አዲስ አበባ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደ አገር ውጥንቅጥ ውስጥ የገባችበት ጊዜ እንደነበር ኹሉም የሚታዘበው እና የሚያየው ጉዳይ ነው። ከድምጻዊ ሀጫሉ ግድያ ጋር የተያያዙ ግን ደግሞ ለመፈንዳት ጊዜን ሲጠብቁ ነበሩ በሚመስል አኳኋን በአንድ ጊዜ ከዳር እስከ ዳር የተስተጋባው ጩኸት እና ግርግር ብዙዎችን ለዘመናት ያፈሩትን ሀብት እና ንብረት እንዲሁም ውድ ሕይወታቸውን እንዲያጡ ያደረገ አጋጣሚ ነው። ሕንጻዎች ተቃጥደለዋል፣ ሆቴሎች ጋይተዋል፣ መኖሪያዎች ባለቤቶቻቸውን እንደያዙ ዶግ አመድ ሆነዋል ቀሩት ደግሞ ከእሳት ሸሽተው ሲያመልጡ በተደራጁ ኃይላት ጉዳት ደርሶባቸው ከሞት ተርፈው በቤተ ዕምነቶች ተጠልለዋል ወይም ጉዳታቸው ጠንቶ አሸልበዋል።

የኹከት እና የግርግር ፖለቲካው ተጉዞ አመለጥደነው ያልነውን እና አብቅቷል ከዚህ ወዲያ የንፁሀን ደም በከንቱ አይፈስም ስንባል እና ተስፋ ሲመገብ ለኖረው አብዛኛው ዜጋ እጅግ ልብን የሚሰብር እና ወደ ቀደመው አዙሪት አሁንም ኢትዮጵያ እየተንደረደረች ለመሆኑ ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደሚሆንም መገመት አያስቸግርም። በዚህ ወቅት ታዲያ መንግስት ይሆነኛል እና ዜጎችን ለመጠበቅ ይጠቅመኛል ያላቸውን አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ በተለያ አካባቢዎች ተነስተው የነበሩ ኹከቶችን ለመቀልበስ ሲንቀሳቀስም ታይቷል። ከጠመንጃ ቃት እስከ በይነ መረብ ማቋረጥን የመሰሉ እርምጃዎች በመንግስት ተወስደው መረጃዎች በእጅጉ የተያዙበት እና ዜጎች በከፍተኛ የመረጃ ዕጥረት የተቸገሩበት ሦስት ተከታታይ ሳምንታት ነጉደዋል።

ከሳምንታት ቆይታ በኋላም በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ስፍራዎች የገመድ አልባ በይነ መረብ አገልግሎትን በመልቀቅም የግንኙነት መረቡን ጭላንጭል በመልቀቅ በአገር ደረጃ ተፈጥሮ የነበረው የኹከት መንገድ እና የግርግር ሙከራ መርገቡን ማሳያ ለማድረግ ሞክሯል። የገመድ አልባው በይነ መረብ አገልግሎት ታዲያ ቀስ በቀስ ወደ መኖሪያ ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች መስፋፋት ሲጀምርም በየደረጃው ግንኙነቶች እና መረጃ ልውውጦች ቀስ በቀስ መስፋፋት ጀመሩ። በኋላም የተንቀሳቃሽ ስልክ የበይነ መረብ አገልግሎት ከኹሉ በመጨረሻ ደረጃ በመልቀቅ አዲስ አበባን ወደ ቀደመው እንቅስቃሴዋ እንድትመለስ አድርጓል።

ይህ ታዲያ በመንግስት በኩል እርምጃው ትክክል እና ነገ ለሚደርሰው ጉዳት ወይም ዛሬ ላይ ደርሶ ነገ ሊፈጥር የሚችለው ችግር እና ጥሎት ለሚያልፈው ጠባሳ ፍቱን መፍትሔ ተብሎ ተቀምሮለት ነበር። ይሁን እንጂ ድምጻዊው ግድያ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ መንግስት ፊቱን ወደ ግጭቱ እንጂ ዓለምን ረግጦ ይዞ በጣር ውስጥ ለከተታት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ትኩርትን አልሰጠም ነበር። ለዚህ ደግሞ እንደ አመክንዮ የሚነሳው እንደ መፍትሔ የተቀመጡት የበይነ መረብ መዘጋትን መሳሰሉት እርምጃዎች ቤት ውስጥ ተቀምጠው እና ከሰው ርቀው በይነ መረብ ሚያስፈልጋቸውን ለሚገበዩ ሰዎች ወደ አደባባይ መውጣት እና ለበሽታው ተጋላጭነታው መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ የተሰመረበት አይመስልም ነበር። ከዚሁ በተያያዘም ቢሆን መጀመሪያ የደኅንነቱ ጉዳይ ተብሎ አፋጣኝ እርምጃ በሚወሰድበትም ወቅት በአንድ ስፍራ በርካቶችን አጉሮ የበሽታው መዛመቻ ሰፊ እና ምቹ ሜዳን መፍጠር ግን አሁንም ታስቦበታል ለማለት ሚስደፍር አይደለም። በዚህም ምክንያት ቢቢሲ የኦሮምኛው ዝግጅት ክፍል እንደዘገበው ለሳምንታት በአንድ የትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር ከጥንቃቄ ጉድለት በሆነ አያያዝ በኮቪድ ተጠቅተው ወደ ኤካ ኮተቤ ማገገሚያ ማዕከል መወሰዳቸውን በማንሳት ትኩረት ለኹከቱ ትኩረት የተሰጠበት መንገድ ወረርሽኙን ያስረሳ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሌላ በኩልም ቢሆን አለመረጋጋቶች ተከስተው በነበሩበት ወቅት በተለይም ደግሞ የሀጫሉን አስከሬን ወደ ትውልድ አገሩ ለመሸኘት በሚደረግበት ሒደት ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ በነበረች አገር እንደዛ አይነት የሰው ብዛት እና የአካላዊ ንክኪ በሽታውን ለማዛመት ምቹ ከመሆኑ የተነሳ የመንግስት አካልም ይህን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ያደረገው ቁርጠኝነት አናሳ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች። ይህንንም ተከትሎ በወቅቱ ከኹከቱ እና ከግርግሩ ሰፊነት በመነሳት በየቀኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግ የነበረው የኮቪድ 19 ምርመራ በየቀኑ ይደረግ ከነበረው ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ እንደነበርም ማንሳት ይቻላል። ይህም ከምርመራው መቀነስ ባለፈ የወረርሽኙ ፍጥነት እና ጥንካሬ በየትኛውም ሁኔታ አገር ብትሆን ሊስፋፋ እንደሚችል ግንዛቤ የተሰጠው እስከ ማይመስል ድረስ ተዘንግቶ እና መለሳለስ ታይቶበት እንደነበር አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይህም ደግሞ የሚያጠናክረው በተወሰነ ደረጃ በበርካታ አካባቢዎች ተከስቶ ነበረው ውጥንቅጥ ረገብ ማለት ሲጀምር እና ነገሮች የቀደመ መልካቸውን መያዝ ሲጀምሩ ወደ ቀደመው የመመርመር አቅም በተመለሰ ጊዜ ታይቶ የማይታወቅ እና ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ ጀምሮ ተገኝቶ የማይታወቅ በቫይረሱ ተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ። ቀጥሎም ለተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ሊባል በሚችል ደረጃ የሚያዘው ሰው ቁጥር ማሻቀብ ጀመረ።
እነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ታዲያ ከመንግስት ወገን በታየው ቸልተኝነት የተከሰቱ ለመሆኑ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይህን በተመለከተም የእስካሁኑ ጉዳይ በቁጭት ሊመልሱት ማይችል ቢሆንም ለከዚህ ቀጥሎ ለሚኖረው ጉዳይ ግን መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲተጋም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ከሐምሌ 15/2012 ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ከፊል መንደሮችን እስከ መዝጋት የተወሰደው እርምጃ ይል ሚያሰኝ ቢሆንም ግን ቅሉ ለረጅም ተከታታይ ጊዜያት ቦሌ ክፍለ ከተማን በቀዳሚ ደረጃ እንዲቀመጥ ካደረጉት መንደሮች ውስጥ አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ቀደም ተብሎ ሊወሰድ የሚቻል ጉዳይ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ ስፍራዎች ኹከቶች እና ግርግሮች ቢኖሩም መንግስት ግን አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ሙሉ ትኩረቱን ወደ አንድ አቅጣጫ በማድረግ ያለውን እና የበርካቶችን ውድ ሕይወት እየቀጠፈ ያለውን ጉዳይ ችላ ማለት እንደሌለበት እና ከሚከሰቱት ውጥረቶች እና ግርግሮች በላይ ወረርሽኙ የበርካቶችን ሕይወት እንደሚቀጥፍ ሊገነዘብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስታውቃለች።

በአዲስ አበባ ከተማ በሙሉ አቅም የተመለሰው የበይነ መረብ አገልግሎትም ወደ ክልሎች በመዳረስ በገመድ አልባ የበይነ መረብ አገልግሎት የተጀመረው ግንኙነት ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በይነ መረብ አገልግሎት ከፍ እንዲልና ስለ ወረርሽኙ በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎች እንዲደርሳቸው በማድረግ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታው እንዲጠብቁ ማድረግ ይገባል ስትልም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። በቀሩት ጊዜያትም እንደ ሰሞኑ ያሉ አስቸጋሪ ጉዳዮች እና አገርን ከዳር እስከ ዳር የናጡ ክስተቶች በሚከሰቱበት ወቅትም በይነ መረብ የመዝጋት አመራጭ ከፍተኛ ዋጋ ከማስከፈሉም ባለፈ አገር ያለችበት ኹኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች አማራጮች እንዲወሰዱ እና አማራጮችም ወረርሽኙን ከመቆጣጠር አንጻር መታየት እንደሚኖርባቸውም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

አገር በማረጋጋት ዙሪያ የተወሰዱ እና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አዲስ ማለዳ በጽኑ ምትደግፍ ሲሆን አገር በማረጋጋቱ ሒደት ውስጥም ጎን ለጎን የወረርሽኙ ስርጭት እና ለመግታት የሚወሰዱ ያላሰለሱ እርምጃዎች በተገቢው ሁኔታ ሊጤኑ እንደሚገባ እና ፤ ውዥንብሮች እና ግርግሮች በወረርሽኙ ላይ በምንሰጠው ትኩረት ላይ መዘናጋትን እንዳይፈጥርብን ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here