ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ – በኢትዮጵያ ገጾች

0
1972

ሰማዕትነትን ትልቅ ያደረገው ምንድን ነው? የሃይማኖት ሰዎች በዝርዝር የሚያስቀምጡት ሐሳብ ሊኖር ቢችልም፣ የሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ ያለው፣ የምድር ቆይታውም ኹለተኛ እድል የሌለው ስለሆነም ነው ብለው የሚሞግቱ አሉ። ሰው የነገውን ባያውቅም ነገን መኖር እንደሚፈልግ ግን እርግጠኛ ነውና ያሰበው መሳካቱን፣ የዘራው መብቀሉን፣ ያጸደቀው ማፍራቱን ማየት ይፈልጋል።

አገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ መልኩ በአርበኝነት ሰማዕትነትን የተቀበሉላት በርካቶችን ወልዳለች። ጨርቄን ማቄን፣ ልጄን ቤቴን ሳይሉ ብዙዎች ሕይወታቸውን ገብረውላታል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ተጠቃሽ ናቸው። የአገር ጽናት፣ እምነትና ጥንካሬ በአንድ እርሳቸው ሕይወትና ሰማዕትነት ውስጥም ተጽፎ ይገኛል።

የ20ኛው ዘመን ታላቅ ሰማዕት ናቸው ይሏቸዋል፤ አቡነ ጴጥሮስን። አቡነ ጴጥሮስ ልጅነታቸው እንዲሁም ወጣትነትና ጉልምስናቸው በሃይማኖት ስርዓት ውስጥ ነው ያሳለፉት። በአብነት ትምህርት ቤት ከንባብ እስከ ቅኔ ትምህርት ዘልቀዋል። አልፈውም የቅኔ እና የመጻሕፍት መምህር በመሆን አገልግለዋል። በመረጡት የምንኩስና ሕይወትም የጵጵስና ሹመት አግኝተዋል።

ቅድመ ነገር
ጣልያኖች በ1888 አድዋ ላይ ድል ከተነሱ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው እንደነበር ባሕሩ ዘውዴ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ – ከ1847 እስከ 1983› የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል።

በኋላ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመውረር የወሰነበት ወቅት ይህ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም፣ ከ1924 ጀምሮ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል። እናም ከኢትዮጵያ ጋር መጋጫ መንገድ ሲፈልግ የቆየው ሙሶሎኒ ኅዳር 26/1927 የተከሰተውን የወልወል ግጭት ምክንያት ሆነው።

መጽሐፉ ጨምሮ እንደሚያትተው፣ መስከረም 22 ቀን 1928 የኢጣልያ ጦር የመረብ ወንዝን ተሻግሮ በሦስት መስመሮች በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ከፈተ። ኢትዮጵያም አጸፋውን የማጥቃት እርምጃ የጀመረችው ጥር ወር ላይ ነበር።

ባሕሩ ዘውዴ በዚህ መጽሐፍ እንደጠቀሱት፣ በ1928ቱ የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት ላይ የአድዋ ትዝታ ያንዣበበ ነበር ማለት ይቻላል። እንደምን ቢባል፣ ጣልያኖች ሥማቸውን ለማደስ፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የአባቶቻቸውን ገድል ለመድገም ነበርና የሚዋጉት ነው። እንዲያም ሆኖ አድዋ አልተደገመም። ሆኖም በአርበኞች ትግል ምክንያት የኢጣልያ አገዛዝ በአብዛኛው በከተሞች የተወሰነ ነበር።

በድምሩ የኢጣልያ አገዛዝ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የነበረው መደበኛና የሚታወቀው ዓይነት የቅኝ አገዛዝ ባህሪይ አልነበረውም፣ እንደ ባሕሩ ገለጻ። ይህም የሆነው ባልተቋጠ የአርበኞች ትግል የተነሳ ነው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አቡነ ጴጥሮስ የሚነሱት።

አቡነ ጴጥሮስ የአርበኞችን መንፈስ በመጠናከርና ብርታትን በመስጠት ከፍተኛ ሚና ይጫወቱ የነበሩና የኢጣልያን አገዛዝ በጽኑ የሚቃወሙ ሰው ነበሩ። በኋላም በኢጣልያ እጅ ወደቁ። አርበኞችን የሚያበረቱ መሆናቸውን ጣልያኖች አልወደዱላቸውም ነበር። ለምን ቢሉ ኃይልና ጠብመንጃን ፈርቶ ጸጥ ለጥ ብሎ ሕዝቡ እንዲገዛና መንፈሱ እንዲዳከም እንጂ እንዲበረታ አይፈልጉምና ነው።

አስደቅመውም አቡነ ጴጥሮስን ሊገድሏቸው ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን ተሰሚነታቸውን ዐይተው ለራሳቸው ተመኟቸው። ከፋሺስት ኢጣልያ ጎን ቆመው ሕዝቡ እንዲታዘዝ እንዲያደርጉና በዛም ፋንታ ጥሩ ካሳ፣ ምቹ ኑሮ እንደሚያገኙ ተነገራቸው።

እርሳቸው ግን አሻፈረኝ አሉ። ስቃይ ከበዛበት ምርመራ በኋላም በአደባባይ ተረሸኑ። ይህም የሆነው ሐምሌ 22 ቀን 1928 ከዛሬ 84 ዓመታት በፊት ነበር።

ኹነቱ ሲታወስ
አቡነ ጴጥሮስ በአደባባይ ተረሽነው የተገደሉበትን ሁኔታ የተለያዩ ጸሐፍት በተለያየ አገላለጽ ከትበው አኑረውታል። ከዚህ መካከል ‘ኮርየር ዴላ ሴራ (corriere Della sera) የተባለው ጋዜጣ ወኪል እና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረ ‹ፖጃሌ› የተባለ ጋዜጠኛ የጻፈው እንዲህ ተጠቅሶ ይገኛል።

«ሐምሌ 22 ቀን 1928 አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ። በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው ‘ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም’ ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት።

አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማሲ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር። ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ ከአዲስ አበባ ውጭ እንኳ የትም ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ።

ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ፣ መልካቸው ጠየም፣ አዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ፤ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ልብስ የለበሱ ሰው ወደ ችሎት ቀረቡ፤ አቡነ ጴጥሮስ። ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞች ሦሰት ሲሆኑ አቡነ ጴጥሮስ የቀረበባቸው ወንጀል ‘ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል’ የሚል ነበር።

ዳኛውም ‘ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣናት ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?’ ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፤

‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስትያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለአገሬና ስለቤተክርስትያኔ እቆረቆራለሁ።

ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ› አሉ።

ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሊገደሉ ቁርጡ ሲታወቅ አቡነ ጴጥሮስ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ መልእክት አስተላለፉ፤ ‹አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስትያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስትያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው።እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ። ስለውድ አገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ።

ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ሥማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ። የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም የተገዘተች ትሁን’ ብለው አወገዙ።»

በኋላም ጥይት በሰውነታቸው አርፎ ሕይወታቸውን ሊነጥቃቸው ሰዓቱ ሲቃረብ፣ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ ተሳለሙት። በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውን ሰዓት አውጥተው ከተመለከቱ በኋላ መልሰው ወደ ኪሳቸው አስገቡት…ያኔም ወታደሮቹ ጥይት አከታትለው በመተኮስ ገደሏቸው። አቡነ ጴጥሮስ በአደባባይ ሕይወታቸው ሲያልፍ በሰማዕትነት፣ በቅድስና እና በኢትዮጵያ ገጽ ላይ ዳግም ተወለዱ።

‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት›
ደራሲ እንዲሁም አርክቴክት ሚካኤል ሺፈራው ለንባብ ካቀረባቸው መጽሐፍት መካከል ‹ምሥጢረኛው ባለቅኔ› የተሰኘው መጽሐፍ የሚዘነጋ አይደለም። ይህም በ1984 በፀጋዬ ገብረመድኅን ለመድረክ በቀረበው ‹ሀሁ ወይም ፐፑ› ተውኔት ላይ መሠረት ያደረገ ቅኝት የተካተተበት መጽሐፍ ነው። በተጓዳኝ የፀጋዬ በርካታ ሥራዎችን የቃኘ ሲሆን፣ ‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት› የተሰኘው ተውኔትም ውስኝ ዳሰሳ ከተደረገባቸው ቴአትሮች መካከል አንዱ ነው። ይህም የአቡነ ጴጥሮስን የመጨረሻ ሰዓታት በምናብ የሳለና በብዙዎች ልብና ሐሳብ ውስጥ አጽድቆ ያበቀለ ነው።

በ‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት› ውስጥ ኹለት ዋነኛ ገጸ ባህርያት እንዳሉ በማንሳት ይጀምራል። እነዚህም አቡነ ጴጥሮስ እና ባሻ አባግርሻ ናቸው። ሚካኤል ሽፈራው በበኩሉ ቴአትሩ የጴጥሮስን የአርበኝነትና የእምነት ፅናት ለመስበክ የተጻፈ አይመስለኝም ይላል። እንዲህ ሲል ይቀጥላል፤

‹‹ይልቁንም በአገርም፣ በእግዚአብሔርና በራሳቸው ላይ እምነት የነበራቸውንና በዚህም እስከ ሞት መጽናት የቻሉትን ጴጥሮስንና፣ በአገርም በእግዚአብሔርና በራሱም ጭምር እምነትን ያጣውንና በነጮች ቅኝ ገዢዎች ብርቱ ክንድ ተሸንፎ የተንበረከከውን የባሻ አባግርሻን እውነት ባህሪ ያሳየናል።›› ይላል። ይህም በዘመኑ የነበሩ ኹለት የኢትዮጵያዊነት ገጾች የተሳሉበት ቴአትር ነው ሲል አክሎ ይገልጻል።

ታድያ በቴአትሩ ኢጣልያኖች አቡነ ጴጥሮስ ለእነርሱ [ለኢጣልያ] እንዲገዙ ለማድረግ ከሚያደርጉት ጉትጎታ ጎን ለጎን የባሻ አባግርሻ ጫና እና ተጽእኖ ጎልቶ ይታያል። የእርሳቸውን ትግልም ሊያጣጥልባቸው ሲሞክር ይታያል፣ በፀጋዬ ‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት› ቴአትር ውስጥ። ሚካኤልም ያንን ሁኔታ ዘርዘር አድርጎ ጽፏል። በመጽሐፉ የተጠቀሰውን ቃል በቃል መዋስ ሐሳቡን በተሻለ ይገልጠዋልና እንዳለ እናንሳው። እንዲህ ይላል፤

‹‹እሳቸው ሕይወታቸውን ሊሰጡለት የቆረጡት ኢትዮጵያዊነት፣ አስቀድሞ መሞቱን ከሐበሻ ምድር እና ልብ ከተደመሰሰ መሰንበቱን ይገልጥላቸዋል [ባሻ አባግርሻ ለአቡነ ጴጥሮስ]። ‹እርስዎ አለ የሚሉት ኢትዮጵያዊ ቅስሙ ተሰብሮ፣ አፍሮና አጎንብሶ ሚስቱን እንኳ ተውሰው ሲመልሱለት፣ እሺ ብሎ፣ አሜን ብሎ ተቀብሎ አብሮ ሲኖር አይቼዋለሁ። እርስዎ አለች የሚሏት ብፅዕት ኢትዮጵያዊት ክብሯን ተደፍራ፣ ተነውራና አንሳ አይቻታለሁ። ኢትዮጵያ የለችም፤ ሞታለች። እርስዎ ሊሞቱ የተነሱት አስቀድማ ለሞተች ኢትዮጵያ ነው። ይላቸዋል።››

ይህም ሁሉ የሚፈትናቸው ነው። እንደ ሚካኤል ትንታኔም ባሻ አባግርሻ በቴአትሩ አካል ነስቶ ይታይ እንጂ በአቡነ ጴጥሮስ ውስጥ ያለና የሚሞግታቸው ‹ሐሳብ› ወይም አንዱ ጎናቸው ነው።

ይህን ሐሳብ ታድያ አቡነ ጴጥሮስ ሲሞግቱና ሲታገሉት ይታያል። ‹አንተ በሞት ስለሚወለድ ሕይወት አይታይህም› ይሉታል፣ ባሻ አባግርሻን። እንዲሁም ‹አንተ አንዲት የስንዴ ፍሬ ወድቃ በስብሳ ሺሕዎች እንደምታፈራ አይገለጥልህም።› ይሉታል።

ከዚህ ሙግት በኋላ አቡነ ጴጥሮስ እንደ ነገ በጥይት ተደብድበው ሊገደሉ በመጨረሻው ሌሊት ዛሬ ላይ ለእመብርሃን የሚያደርሱት ጸሎት በፀጋዬ ቴአትር ውስጥ ጎልቶ ይታያል። እንደ ሚካኤል ገለጻም አቡኑ በመጨረሻ የፈተና ሰዓታቸው ያደረሱት ጸሎት ክርስቶስ በጌቴሰማኔ ያደረሰውን ‹የጭንቀት› ጸሎት ይመስላል ይላል።

‹‹አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምጸናበት ልብ አጣሁ
አማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሰጋሁ››፤ ፀጋዬ በምናብ ያሰፈረው የአቡኑ ቃል ነው።
ጸጋዬ እንዲህ ሲል የአቡነ ጴጥሮስን ቃል ይቀጥላል፤
‹‹…እና ፈርቼ እንዳልባክን ሲርቀኝ የኃይልሽ ወጋገን
አንቺ ከአጠገቤ አትራቂ በርታ በይኝ እመብርሃን
ቃልኪዳኔን እንዳልረሳት እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን።
…እባክሽ እመብርሃን ይብቃሽ እባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ፅናት ስጪኝ እንድካፈል የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ ከነደደችበት እቶን
የእሷን ሞት እኔ እንድሞታት ገላዋ ገላዬ እንዲሆን
አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
ሕጻን ሆኜ የእርግብ ጫጩት አንዳንዴ ራብ ሲያደክማት
ችጋር ከጎጆዋ ገፍቶ እዛፉ ግርጌ ሲጥላት
እናቷ በርራ ደርሳላት…በአክናፏ ሙቀት ታቅፋት
እፍ እያለች ግንባሯ ላይ ሕይወት ስትተነፍስባት
ወዲያው ነፍስ ትዘራለች….ሽር-ብር- ትር እያለች።
ባክሽ አንቺም አትራቂብኝ
እመ ብርሃን እናቴ ትንፋሽሽን እፍ በይብኝ
ጽናትሽን እፍ በይብኝ።
…እንደ ጳውሎስ እንድጸና በፍርሃት እንዳልታወር
ለየዕለቱ ሞት እንዳልሰንፍ…የኪዳኔ ቃል እንዳይነጥፍ
ቃልሽ በሕሊናዬ ዲብ ኃይልሽ በሕዋሴ ይረፍ።
ፍርሃት ቢረብብኝም አንቺ ካለሺኝ አልሰጋም
ኩርምት ብዬ እችልበት እሸሸግበት አይጠፋም
የግማድ መስቀሌን ጉጥ እታገስበት አላጣም
አለዚያማ ብቻዬን ነኝ ኢትዮጵያም ያላንቺ የላት
አንቺ አጽኚኝ እንድጸናላት…›
በ84ኛው የመታሰቢያ ዓመት
በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ክዋኔዎች ሳይከናወኑ ቀርተዋል። ታሪካዊ የመታሰቢያ እለታትም በተወሰኑ ሰዎች ተሳታፊነትና በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል ሐሳቦችን በመጋራት ሲታለፉ ታዝበናል።

ዘንድሮ ማለትም በ2012 ሐምሌ 22 ቀን የሰማዕቱ ጻድቅ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የተቀበሉበት 84ኛ መታሰቢያ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ይህም ዝግጅት የተካሄደው ከጣልያን ጦር መውጣት በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ባረፉ በ10ኛው ዓመት ሐምሌ 16 ቀን 1938 በአዲስ አበባ እንዲቆምላቸው በተደረገ የመታሰቢያ ሃውልት ዙሪያ ነው።
ይህን ዝግጅት እውን ያደረጉት ጉዞ አድዋ፣ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ነው። በእለቱም የተለያዩ ተግባራት መከወናቸው በጉዞ አድዋ ገጽ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ ሐውልቱ የሚገኝበትን አካባቢ ከማጽዳት ጀምሮ አበባ ጉንጉን ማኖርና በአደባባዩ ዙሪያ ችግኝ መትከል ይገኙበታል።

በእለቱ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትም መንፈሳዊ ዝማሬ ማቅረባቸው ተጠቅሷል። በተመሳሳይ ጉዞ አድዋ የጀመረውና የአቡነ ጴጥሮስን ስውር የቀብር ቦታ አስሶ አጽማቸውን አፍልሶ በክብር የማስቀመጥ እንቅስቃሴ ተዋውቋል። የከተማዋ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትም የዚህ ሥራ አካል እንዲሆኑ የሚል ጥሪ ቀርቧል።

ጉዞ አድዋ ያስተዋወቀው የአቡነ ጴጥሮስ አጽማቸው ፈልሶ በክብር እንዲያርፍ የማድረግ ተግባር የብዙ ተቋማትን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው። የቀብራቸው ነገር እንዴት ነበር ብሎ ለሚጠይቅ፣ የጉዞ አድዋ ገጽ ላይ ተከታዩ ታሪክ ሰፍሯል።

ኢጣልያ አቡነ ጴጥሮስን ረሽኖ ከገደለ በኋላ አስክሬናቸው አደባባይ ተትሎ ውሏል። ቀብራቸውም የተፈጸመው በምስጢር ነው። የቀብራቸውን ቦታ ለማግኘት ታድያ ምሁራን ሰነዶችን ከየተገኙበት ሲመረምሩ የቆዩ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ ከሚል ‹ግምት› በቀር ያገኙት ተጨባጭ መረጃ አልነበረም።

በኋላ በ1975 ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር በተገናኘ ‹ፉሪ ለቡ› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን የአቡነ ጴጥሮስ የቀብር ስፍራ ፋሽስቶች በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው ‹ሙኒሳ ጉብታ› ላይ መሆኑን ከልጅነታቸው ጀምሮ ይሰሙ እንደነበር ተናግረዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት እለት ትኩረት እንዲሰጠው የበኩልን ጥረት እያደረገ እንደሆነ በማኅበራዊ ገጹ (ፌስቡክ እንዲሁም ቴሌግራም) ያስነበበው ጉዞ አድዋ፤ አጽማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ መሪነትና በመንግሥት አጋዥነት በስውር ከተቀበሩበት ስፍራ አፍልሶ በክብር እንዲቀመጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ሲልም አብስሯል። በዚህም መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የእንቅስቃሴው አጋር እንዲሆን የሚል ጥሪም ቀርቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here