የኦነግ መሰነጣጠቅ ቱማታ

0
256

የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ ታስረዋል፣ ቤት ውስጥ የቁም እስረኛ ሆነዋል እንዲሁም የኦነግ አመራር ተሰነጣጥቋል የሚሉ ወሬዎች በሰፊው መናፈስ ከጀመሩ ሳምንት አልፏቸዋል። የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ኀላፊዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ተጠይቀው ስለቁም እስሩ ማስተባበያም ማረጋገጫም አልሰጡም፤ ብዙዎቹ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምንም መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል። ይሁንና የዓይን እማኞች የዳውድ መኖሪያ ቤትን የፌደራል ፖሊስ አባላት በተጠንቀቅ ጥበቃ እያደረጉለት ነው ሲሉ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ በኦነግ ምክትል ሊቀ መንበር አራርሳ ቢቂላ ጠሪነት እና መሪነት የፓርቲውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ አካሒደዋል የሚል ወሬ መናፈስ የጀመረው። በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ዳውድን ከሥልጣን አውርዶ ምክትላቸው ተክቷል የሚሉ መረጃዎች በስፋት ተንሸራሽረዋል። ዳውድ ከሥልጣን እንዲወርዱ የተደረገበት ምክንያትም አብሮ የወሬው ማድመቂያ ሆኗል። ዳውድ ከማዕከላዊ እና ሥራ አስፈጻሚው እውቅና ውጪ ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አድርገዋል፤ አመራርም ሰጥተዋል የሚሉት ይገኙበታል።

ይህ ወሬ በሰፊው በሚራገብበት ወቅት የኦነግ ቃል አቀባይ ቶሌራ ለኢሳት ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ በፓርቲው ውስጥ ምንም የሥልጣን ሹም ሽር አለመደረጉን ተናግረው። ሊቀ መንበሩ ከቤት መውጣት ባለመቻላቸው እና ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ ባለመቻሉ የሥራ አስፈጻሚው የፓርቲውን የዕለት ተዕለት ሥራ እንዴት ማስኬድ እንዳለበት የምክክር ውይይት አድርጎ ለጊዜው ምክትሉ እና የሊቀ መንበሩን ቦታ ተክቶ እንዲሠራ መወሰኑን አስታውቀዋል፤ ይህንንም ጉዳይ አስመልክተው በነጋታው ለመገናኛ ብዙኀን ፓርቲው መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል። አስገራሚው ነገር እስካሁን ፓርቲው ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም። በዚህም ምክንያት በፓርቲው ዙሪያ ያሉ ብዥታዎች ሊጠሩ አልቻሉም።

በኦነግ አመራር መካከል የተፈጠረውን ብዥታውንና ውዥንብር ሳዑዲ አረቢያ እና ኬኒያ የሚገኙት የኦነግ ቻፕተሮች በማዕከላዊ ኮሚቴው ተካሔደ የተባለውን ስብሰባና ተደረሰ የተባለውንም ውሳኔ የፓርቲው ሊቀ መንበር ያልመሩት በመሆኑ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፤ ሊቀ መንበራችንም ዳውድ ኢብሳ ነው ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

በዚህ ውዥንብር መካከል በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ፥ ከሰው ጋር እንዳይገናኙ፣ ስልክ እና ኢንተርኔት ተቋርጦባቸዋል እንዲሁም ማንም ወደ መኖሪያ ቤታቸው መግባትም መውጣትም እንዳይችል ተደርገዋል የተባሉትን ዳውድ ኢብሳ በቀጭኑ ሽቦ ቃለ ምልልስ አድርጎላቸዋል።

ዳውድ ለደህንነትህ ሲባል ከቤታቸው ውጪ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ፣ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቆረጠባቸው ማረጋገጫ ከመስጠት ባሻገር ፓርቲያቸው አድርጎታል ስለተባለው ስብሰባ የሚያውቁት ምንም ነገር እንደሌለ አስታወቁ። በሌላ በኩል ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበሩ አራርሳ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል፣ ስብሰባ የተካሔደው የፓርቲውን የዕለት ተዕለት ሥራ ለማካሔድ ብቻ እንደሆነና የአመራሮችን እና የአባላትን የጅምላ እስር በተመለከተ ምን ማደረግ አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ መሆኑን አስታወቁ።

የኦነግ መሰንጠቅን በተመለከተ እስካሁን የተጨበጠ ነገር ባይኖርም በአመራሩ መካከል ልዩነት መኖሩ ግን የሊቀ መንበሩ እና የምክትል ሊቀ መንበሩ ምላሾችን መሰረት አድርገው ብዙዎች ፍንጭ ሰጥቶናል ባይ ናቸው።

የሆነው ሆነና ከሰው ጋር እንዳይገናኙ ማዕቀብ የተጣለባቸው እንዲሁም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠባቸው ዳውድ ከቪኦኤ ጋር እንዴት በስልክ ሊገናኙ ቻሉ የሚለው ጉዳይ ግርምት፣ ትዝበትም፣ ሳቅም በመፍጠር የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። አንዳንዶች ዳውድም እንደ ጃዋር መሐመድ የራሳቸውን ሳተላይት ቤታቸው አስገጥመው ይሆናላ በማለት የለበጣ ይሁን የምር ጥርጣሪያቸውን ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here