በለውጥ ሐሳብ ጎዳና ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እሳቤዎች

0
848

የግለሰቦች ተራማጅነት ወይም አፈንጋጪነት ትርጉም አልባ በሆነ ጊዜ የሞያ ክብር አይኖርም የሚሉት ፍቃዱ ዓለሙ፣ ሐሳቦች ቡድናዊ በሆነ ዲስኩራዊ ቅኝት ሊያልፍ የግድ የሚልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ያነሳሉ። ይህም ብዙ የለውጥ ሐሳቦችን ያሳጣና ያመከነ ጉዳይ ነው ሲሉ የሙግታቸውን የመጀመሪያ ክፍል እንደሚከተለው አቅርበዋል።

የማሰብ፣ ያሰበውን የማድረግ፣ የሠራውን የማድነቅ፣ ያደነቀውን እንደገና የማሻሻል ለሰው ልጅ የተሰጠ ብቸኛ ባህሪ ነው። እንስሳት እንደየ ግብራቸው የማይለወጥ ተፈጥሮ ሲኖራቸው የሰው ልጅ ግን በተፈጥሮ ሂደት እያደገና እየተለወጠ የሚሄድ እንስሳዊ ፍጡር ነው። በዚህ አግባብ ማፈንገጥ ከሰው ልጅ ባህሪ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።

አፈንጋጭነት ኹለት ዓይነት ትርጉም አለው። የመጀመሪያው ሰዎች በተፈጥሮ ሂደት በየደረጃው የሚያሳዩት ጠባይ ነው። ኹለተኛው ግለሰቦች ከተለመደው የወል ግንዛቤና ባህሪ ወጣ ያለ ወይም የተሻለ ማሰብ ሲጀምሩ ነው። ኹለቱንም በቁጥጥር ማገት አይቻልም። የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ አንድ ቀን ይቀጣጠላሉ።

እንደእኛዋ ኢትዮጵያ ባሉ በምጣኔ ሀብት ደሀ የአፍሪቃ አገሮች አብዛኛው ማኅበረሰብ ገና ያልነቃ በመሆኑ አፈንጋጭ ለሚለው ብያኔ ያለው እሳቤ ከላይ ከተሰጡት ትርጓሜዎች ጋር የሚጋጩ ናቸው። ምን አልባትም ከተለመደው አኳኋን የተለየ ጠያቂ፣ ተራማጅ፣ ደፋር፣ ቀደም ቀደም የሚል ከሆነ አፈንጋጭ ተብሎ የተሳሳተ ፍረጃ ይለጠፍበታል። መፈረጅ ብቻ ሳይሆን ግዝትና ግዞትም አለው።

የሰው ልጅ ተራማጅ መሆን የሚጀምረው አካላዊ ለውጥ ብቻ ሳይሆን አእምሯዊ ዕድገት ማምጣት ሲጀምር ነው። በትምህርት የሚያምን ማኅበረሰብ እየበዛ ሲሄድ፣ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ ባህሪ፣ ወግ፣ አኗኗር፣ ዲስኩር በትክክል ማጤን ሲጀምር፣ በአመዛኙ በነገሮች ሁሉ ምክንያታዊ ማስረጃዎችን የሚያቀርብ የማኅበረሰብ ቁጥር ሲጨምር ወይም በአጭሩ የንባብ ባህሉ እያደገ በመጣ ማኅበረሰብ ውስጥ ሁሌም አፈንጋጭነት /ተራማጅነት/ አለ። ለእንደዚህ ዓይነት ባህሪ ተስማምቶ የተፈጠረ ደግሞ የሰው ልጅ ነው። እንስሳትማ ምን ማሰቢያ ልብና አንጎል አላቸው?

በሰው ልጅ አኗኗር ውስጥ የጅምላ ኑሮ አእምሯዊና ማኅበራዊ ብስለትን /ዕድገትን/ ያጠባል። በተለይ ብዙ የተማረ ማኅበረሰብ በሌለበት አካባቢ የዚህ ዓይነት ችግር ይስተዋላል። የግለሰቦች ሐሳብና ልዩነት በቅጡ የማይጠናና ቦታ የማያገኝ ከሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚከናወኑ አዳዲስ ፈጠራዎችን ወይም ኹነቶችን ማየት አንችልም። የሚመገቡት ምግብ እንደ ቡድን ከሆነ፣ የሚተነፍሱት አየር እንደ ጅምላ ከሆነ፣ አተያያቸው እንደ ስብስብ ከሆነ ተራማጅ ይጠፋል።

ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውና አፈንጋጭ የሆኑ ግለሰቦችን ማግኘት አይቻልም። ጠቃሚና አዋጪ አሳቦች ለብዙኀኑ ሲባል ድምፃቸው ይዋጣል። እነዛን ሰዎች በሌላ ጊዜ ደግመን አናገኛቸውም፤ ሰው አላፊ ነውና።

በማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናት፣ የየትኛውም ለውጥ መነሻዎች ግለሰቦች ወይም ሰዎች ናቸው። አቀጣጣዮች ግን ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ። ትክክለኛ አፈንጋጭ የሚኖርበትን አካባቢ ወይም ማኅበረሰብ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወግ በተገቢው ሁኔታ ያጠና ከሆነ ደግሞ ቅቡልነቱን ዓለም ዐቀፍ ያደርገዋል። በተገቢው ጊዜና ቦታ አፈንጋጭነት ጤነኝነት ነው። መሀል ሰፋሪ ወይም ለዘመን አዳሪ ለውጠኛ ሊሆን አይችልም።

የአንድ ሒሳባዊ ቀመር ድምር ውጤት ኹለትና ከዛ በላይ የሆኑ ቁጥሮችን ይሁንታ ይፈልጋል። የማኅበራዊ ለውጥ ተራማጅነትም እንዲሁ ነው። የቡድኑ ውጤት የግለሰቦች ስብስብ መሆን ይገባዋል። ኅብረት ኃይል ነው። ኃያልነቱ ግን በኅብረቱ ውስጥ የግለሰቦች ድምፅ ሲሰማ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አጉል ወጎች አሉ ወደ ኋላ ያስቀሩን፣ የትኛው በጣም ጎድቶናል ለማለት ግን ሰፊ ጥናት መደረግ አለበት። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ልጅ ቀደም ቀደም ሲል አይወደድም። ‹ቀስ ብለህ እደግ›፣ ‹ዲስኩር ላንተ ምን ያደርግልሃል›…እየተባለ ብዙ የመከኑ አንጎሎች አሉ። ብዙ ወጎች አስረዋቸው የቀሩ ሰዎች አሉ።

ከተለያዩ አጉል ወግ እሥራት በራሳቸው ኃይል አፈትልከው የወጡ ትላላቅ ሰዎች ሁል ጊዜ ሞዴል እያልን የምናወራው እኛ ለዘለዓለም ስለታሰርን ነው። በእኛ አቅም ማድረግ የምንችለውን እንድናደርግ እድል ስለተነፈገን ነው።

በዓለም ላይ ብዙ አፈንጋጮች በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ እብድ፣ እንደልታይ ባይ፣ እንደ ወሬኛ፣ እንደ አፍራሽ ይታዩ ነበር። እነዚህ ታላላቅ ሰዎች የታወቁት በኋላ ነው።

በኢትዮጵያም እንደነ ዓፄ ቴዎድሮስ፣ እንደነ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ እንደነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ እንደነ አቤ ጉበኛ፣ እንደነ በዓሉ ግርማ…..የመሳሰሉትን ካየን አፈነጋገጣቸው ዘመኑን የቀደመ ነበር። ግን እንደዘመን አዳሪው በዛና እድሜያቸው አጠረ። አፈንጋጭነት በማኅበረሰቡ ወይም በመንግሥታቱ ዘንድ አይወደድም። ሁሌም እንደ ጠላት ነው የሚታየው።

የሰው ልጅ ተፈጥሮ በአመክንዮ፤ በተጠየቅ የሚራመድ እንጂ በጅምላ የሚሄድ አይደለም። ፈጣሪ አዳምን ከፈጠረ በኋላ ከአንድ ነገር በስተቀር ሌላውን ሁሉ ፈቅዶለታል፣ አንዲመራመርና እንዲጠይቅ። በማኅበራዊ ሳይንስ እምነት በጅምላ የሚጠሩት እንስሳት ብቻ ናቸው። የራሳቸው እምነት፣ እሳቤና አመለካከት ስለሌላቸው። ይህ ከሆነ ደግሞ እንኳን ቡድናዊ ዲስኩር የግለሰቦችን ልብ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው። ከአንድ እናት ማኅጸን የተወለዱ እኅትና ወንድም እንኳ የተለያያ እምነትና ምልከታ ነው ያላቸው።

ስለዚህ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ከግለሰቦች ይልቅ ቡድናዊ ተኮር እንቅስቃሴ ካለ ዕድገቱና ለውጡ ሁሉ ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ አይሆንም። ከቡድን ይልቅ የግለሰቦች ሥራ የሚቆጠርና ውጤቱ መለካት ሲችል ነው። በዚህ ሂደት ነው ኃላፊነት የሚሰማው፤ ብቁና አስተማማኝ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው።

ፕሮፌሰር ባየ ይማም፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በ2001 ባሳተመው መድበለ ጉባዔ መጽሐፍ ‹ቁዋንቁዋና ማኅበራዊ ለውጥ› በሚል ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍቸው ውስጥ ‹ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት ከማኅበራዊ ግንዛቤ፣ ከማኅበራዊ ተግባር በተወሰነ ደረጃ ማፈንገጥ ያስፈለጋል› ይላሉ።

አፈንጋጭነት ወይም ተራማጅነት የአዲስ ፈጠራዎች፣ የአዲስ ሐሳብ ባለቤቶች፣ የአዲስ ትውልድ ውጤቶች ናቸው። ይሄ መቼም ቢሆን በየትኛውም ዲስኩር ወዳጆች ይጠላል። ኢትየጵያ ውስጥ በ1960ዎቹና በ1997 የታየው የተራማጅነት ሒደት በታሪክ አይረሳም።
ትውልዶች ለውጥ ሲፈልጉ ማፈንገጣቸው አይቀርም። ማፈንገጥ ማለት ከተለመደው ዕይታ ወጣ ያለ ምልከታ ማምጣት ማለት ሲሆን፣ በጠቅላላው ግን ለውጥ ፈላጊነት ነው። ይሄን የሚደግፍት ደግሞ ጥቂት ሰዎች ናቸው። ምክንያቱም በጅምላ መኖር የለመደ ማኅበረሰብ ‹የእኔ›፣ ‹ሐሳብ አለኝ› የሚሉ አሳቦች ይደበዝዛሉ።

የግለሰቦች ተራማጅነት (አፈንጋጪነት) በመንግሥታቱና በቡድኖች ትርጉም አልባ በሆነ ጊዜ በዛች አገር ውስጥ የሞያ ክብር አይኖርም። አንተ ኢንጅነር ስለሆንክና የተሻለ ሐሳብ ስላቀረብክ ተቀባይነት አይኖረህም። ሐሳብህ ቡድናዊ በሆነ ዲስኩራዊ ቅኝት ሊያልፍ የግድ ነው። በራሱ የማይተማመንና በውስጡ ፍርሃት ያለበት ትውልድ ለውጥን በቡድኑ ሳይሆን በውጭ ኃይል አማካኝነት እንዲመጣ ይፈልጋልና ነው።
አስተዋይ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ግን ግለሰባዊ ግንዛቤ/አስተሳሰብ/ ወይም ንግግር ከጊዜ በኋላ ማኅበራዊ ለውጥ ይሆናል። ግለሰባዊ ግንዛቤ የግል አእምሮ ውጤት ሲሆን በአደባባይ ሲገለጽ ግን ማኅበራዊ ባህሪ ይሆናል። ምክንያቱም ማኅበራዊነት የግልና የወል ባህሪያትን ስለሚያስተሳስር ነው።

የግለሰብ ለውጥ፣ የግለሰብ ትምህርት፣ የግለሰብ ጤና፣ የግለሰብ ልማት በግልጽና በቀላሉ ይለካል። ከውጤቱ ተነስተን መቀጠልና መበረታታት ያለበትን በተረጋገጠ እውነት ማወቅ ይቻላል። ከዚህ ውጭ ቡድን /ሕዝብ/ በሚል እየተጨፈለቀ የሚሄድ ከሆነ ወደ ቁጥጥር ያመዝናል።
በእርግጥ ከዘመን መቅደም ወይም ማኅበረሰብ ከሚራመድበት ፍጥነት ልቆ መታየት ከራሱ ከማኅበረሰቡ ወይም ከመንግሥትም ሊሆን ይችላል፣ በሚመዘዙ ሰይፎች መበላትን እንደሚያስከትል ከላይ እንደ በዓሉ ግርማን የመሰሉ ሰዎችን ለናሙና በማንሳት ጠቀስ አድርጌዋለሁ።
እንደ አቤ ጉበኛ እና የእርሱ ዘመን ሰዎችን በተራማጅነታቸው ብናነሳ እንኳን አቤ ጉበኛ ከዘመናት በፊት አስቀድሞ ዛሬ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያን ብሎም ዓለምን በምናብ እየሳለልን አስነብቦን ተወልደን ረጅም ዘመናትን በምድር ላይ ለኖርነው ለእኛ ‹አንወለድም› እስክንል ድረስ ልባችንን ያሸፈተ አዕምሯችንን ያበራ ደንቅ ዕይታ እንደነበር አይካድም።

ለውጥን ሽተን የማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ውቅር የሆነውን ማኅበረሰብ ዕሴት በጠበቀ እና ባስጠበቀ መልኩ ማስኬድ ታዲያ ትልቁ የቤት ሥራ እንደሚሆንም አያጠራጥርም። በተለያዩ ጊዜያት ለዘመናት እና ለዕልፍ ትውልዶች ሲንከባለል የመጣውን እና የማኅበረሰቡ ስብዕና የሆነውን አንድን ዕሳቤ በመናድ አዳዲስ ለውጦችን ለማስረጽ መሞከር የሚያስከትለውን ተግዳሮት እና አንዳንዴም ፍጻሜን እስከ ማቅረብ የሚደርስ ግጭት እንደምክንያት የምናነሳቸው አገራት ጥቂት አይደሉም።

እውነት ነው በለውጥ ጎዳና ውስጥ ተግዳሮቶችን በማሸነፍ እና ለመሸነፍ ቆርጦ መነሳት እና ከመነሻው ጀምረው ባዩት መዳረሻ ላይ ለመቆናጠጥ ቁርጠኛ ትግል መሣሪያን ከማንገብ ያልተናነሰ ተጋድሎ እንደሚያስፈልግ አያጠራጥርም።

የዕሳቤዎችን ለውጥ ታዲያ በአዳዲስ ትውልዶች ላይ ለመጫን ወይም ለማስረጽ በትምህርት ቤት እና በቤት ውስጥ ብቻ የሚደረጉ ሥራዎች እጅግ ውስን የሆነ ለውጥን ከማምጣታቸው ባለፈ አመርቂም አይሆኑም። ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ከጀመርን በኋላ የእኛ ልጆች ብቻ መሆናቸው ይቀራል። የመምህራኖቹ አስተሳሰብ ውጤት፣ ባልንጀሮቻቸው የጨዋታ ድምር፣ የማኅበረሰቡ የግሳጼ ምርት ናቸው።

በዚህ ጊዜ ታዲያ የለውጡን እሳቤ ከማኅበረሰቡ ዘንድ የማይመገቡ ከሆነ የለውጡ የእሳቤ እርምጃ ከመንገድ ተቀጨ ማለት ነው። መማር ማለት የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ማለትም እንደሆነ መታወቅ ይገባል። ነገር ግን የመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ በእርግጥ ለምንኖርበት ሕዝብ እና ለምናመጣው ለውጥ ይጠቅማል ወይ የሚለው ደግሞ በጉልህ ሊታሰብበት ይገባል።

ፍቃዱ ዓለሙ ጋዜጠኛ እና የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው esmbefe@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here