ዓከየመን እና ሶማሊያ የተነሳው የአንበጣ መንጋ ለምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ስጋት መሆኑ ከተገለጸ ከአንድ ዓመት የዘለሉ ወራት አልፈዋል። ኹለቱ አገራት በውስጣቸው ሰላምና መረጋጋት አልነበረምና መንጋውን የሚከላከሉበት ትኩረት፣ ጊዜም ሆነ አቅም ስላልነበራቸው፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ያሉና ሌሎች አገራትም ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ የዓለም ድርጅቶች ሲያሳስቡ ተሰምቷል።
ሰላምና መረጋጋቷ በየጊዜው የሚታወከው ኢትዮጵያም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ፣ የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ስጋት ከጣለበቸው አገራት መካከል ሆናለች። ይህ የአንበጣ መንጋ የምግብ ዋስትና ላይ አደጋ የጣለ ከመሆኑ በላይ፣ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠንም ቀላል አይደለም። ለዚህም ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የሚደረገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚመድበውን ገንዘብም ከፍ እንዲያደርግ የሚያሳስቡ ብዙዎች ናቸው።
ይህ የአንበጣ መንጋ ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል፣ እያደረሰ ያለው ጥፋትና ሊመጣ የሚችለው አደጋ አልፎም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ምን ይመስላሉ የሚለውን በሚመለከት ባለሞያዎችን አናግረውና የቀደሙ በጉዳዩ የተጻፉ መዛግብትን አገላብጠው የአዲስ ማለዳዎቹ አሸናፊ እንዳለ እና ሊድያ ተስፋዬ፣ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርገውታል።
የመጀመሪያው መጀመሪያ
በደቡብ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ውጫሌ እና ጠልጠሌ ወረዳ ለሦስት ዓመት ዝናብም ሆነ የበረሃ አንበጣ ታይቶ አይታወቅም። ይልቁኑም የአካባቢው ነዋሪዎች ዝናብን አብዝተው ይናፍቁ፣ ‹ምን መጣብን!› እያሉም ፈጣሪያቸውን ይለማመኑ ነበር።
ታድያ ባለፈው ዓመት አካባቢው ዝናብ ያገኘ ሲሆን፣ ያም ከአንበጣ መንጋው ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የሆነ ነው። በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች እንዲሁም አርብቶ አደሮች አንበጣው ዝናቡን እንዳመጣላቸው ነበር ያመኑት። እናም አንበጣውን ቢያባርሩ ዝናቡም አብሮ እንዳይሄድባቸው ስጋት ገባቸው። ስለዚህም ዝም አሉ። መንጋው ከቤታቸው አፈናቅሎ እስኪያስወጣቸው ድረስ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንኳ አላሳወቁም።
በኦሮሚያ የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በውጫሌ ወረዳ የኬሚካል ርጭት የሚያካሂዱ አውሮፕላኖች ወደ አካባቢው ሲደርሱ፣ በወረዳው ብቻ 38 ሔክታር የስንዴ ማሳ ወድሞ ነበር። የበረሃ አንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ማሳዎችን ሊወር እንደሚችል የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት (ፋኦ) የበረሃ አንበጣ መረጃ አገልግሎት ከኹለት ዓመት በፊት ግንቦት ወር መግቢያ ላይ ነበር ማሳሰቢያ አዘል መልእክት ያስተላለፈው።
እስከ መጋቢት ወር ድረስ የአንበጣ መንጋው በኢትዮጵያ 1.35 ሚሊዮን ሔክታር የግጦሽ መሬት እንዲሁም 197 ሺሕ 163 ሔክታር የሰብል ማሳ ላይ ጉዳት አድርሷል። እስከተጠቀሰው ወር ድረስ በድምሩም 3.5 ሚሊዮን ኩንታል እህል ወድሟል። ከዚህም በተጨማሪ የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው የትንበያ መረጃ መሠረት፣ ይህ የበረሃ አንበጣ የ2012/13 ዓመት የግብርና ምርትን በ8 በመቶ ይቀንሰዋል ብሏል። ይህም ወደ 26.8 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ 12 ሚሊዮን ሕዝብ ሊመግብ የሚችል ነው።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር የነበሩትና አሁን በሚኒስቴሩ እጽዋት ጥበቃ አማካሪ ዘብድዮስ ሳላቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት እንዲህ አሉ፤ ‹‹ከመንጋው ብዛትና በሰፋፊ የሰብል ማሳዎች ላይ ካደረሱት ከባድ ተጽእኖ አንጻር፣ ከ80 በመቶ እስከ 100 በመቶ የሰብል ውድመት ይከሰታል ብለን ሰግተን ነበር። ነገር ግን ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ስለደረሰንና ከሰብል ማሳዎች እንዲርቁ [አንበጣዎች] ለማድረግ ዝግጅት በማድረጋችን እድለኛ ነን።›› ብለዋል።
ይህ የበረሃ አንበጣ አሁን ላይ ዐስር አገራትን ያዳረሰ ሲሆን፣ ከፓኪስታን እስከ ኡጋንዳ የመን፣ ሶማሊያ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያን አካሏል። ሶማሊያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇ የሚታወስ ነው። እንደ ፋኦ ዘገባ ከሆነ ደግሞ በጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ብቻ 13 ሚሊዮን ሰዎች ከባድ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ናቸው። በተጨማሪም 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በከፍተኛ የረሃብ ስጋት ውስጥ ገብተዋል ሲልም አክሏል።
ይህ ቁጥር እንግዲህ አስቀድሞ በእነዚህ አገራት ይልቁንም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚገኙ አገራት ከነበሩ 22.8 ሚሊዮን የሚጠጉ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተጨማሪ ነው።
ረሃብ፣ ጎርፍ፣ የዝናብ እጥረት አንዲሁም ግጭት የመሳሰሉ ቀውሶች ሰዎች ምግብ የሚያገኙበትን እድል ሲዘጉ ቀጥሎ ለሚፈጠሩ ቀውሶችም ተጋላጭ ያደርጓቸዋል። ይህንንም ከወዲሁ መቆጣጠር ካልተቻለ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ የምግብ ዋስትና ችግር እንደሚከሰት የተባበሩት መንግሥታትም አሳስቧል። የአንበጣ መንጋው አስከፊ ሊባል የሚችለው ጥፋትም ገና ወደፊት የሚመጣ ነው፣ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ስጋትና ማሳሰቢያ ከሆነ።
የደረሱ ጥፋቶች
የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ይህን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል አስቀድሞ በመጋቢት ያስፈልገኛል ያለው 76 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ይህ የገንዘብ መጠን ግን አሁን ጨምሮ ወደ 153 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል። የፕሮግራሙ ሥራ አስኪያጅ ዴቪድ ቢስሊ እንደጠቀሱት ደግሞ ይህ የገንዘብ መጠን በዚህ ከቀጠለ እስከ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሊዘልቅ ይችላል።
ይህ የበረሃ አንበጣ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ሰዎች ብዛት የጨመረ ብቻ አይደለም፣ ይልቁንም የምግብ ዋጋ መናርና በእንስሳት መኖ ዋጋ ላይም በተመሳሳይ ጭማሬ ያስከተለ ነው። በአንበጣ መንጋ በተጎዱና በተወረሩ አካባቢዎችም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አማራጭ መንገዶችን እየተጠቀመ ይገኛል።
እነዚህም ለዘር ያስቀመጠውን እህል ለምግብ ከማዋል ጀምሮ የሚያረባቸውን ከብቶች እንዲሁም የቤት ውስጥ እቃዎችን ቤትንም ጨምሮ መሸጥ፣ መሰደድ፣ ገንዘብ መበደር፣ ልመና መውጣትና መሰል መንገዶች ናቸው።
በአንበጣ መንጋው በኢትዮጵያ ስድስት ክልሎች ተጎድተዋል። በአንጻሩ የምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል ከዚህ የዳነ ይመስላል። ከፍተኛው የሰብል ውድመትም ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል። በመቀጠል ሶማሌ ክልል አንድ ሚሊዮን ኩንታል፣ በትግራይ 843 ሺሕ 241 ኩንታል እና በአፋር 202 ሺሕ 882 ኩንታል በተርታ ተቀምጠዋል።
በኦሮሚያ የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጌቱ እንዳሉት የእርሻ ማሳዎችን ለመጠበቅ ስኬታማ ጥረት ቢደረግም፣ አሁንም አንበጣው እየተራባ እንደሆነ ነው። ጌቱ ቀጥለው እንዲህ አሉ፤ ‹‹በክልል የአንበጣ መከላከል ሥራን የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁመናል። የፌዴራል መንግሥትም ግብዓትና ቁሳቁስ እያቀረበልን ነው። መንጋውን ከሐረር፣ ባሌ፣ አርሲ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የእርሻ ማሳ ካለባቸው አካባቢዎች ማባረር ችለናል።
ያንን ማድረግ ባንችል ኖሮ በጠቅላላው የግብርና ምርት ይወድም ነበር። ያም ሆኖ ቦረና ላይ አሁንም ተጠናክሮ ይገኛል። ምክንያቱም በአካባቢው ያሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ‹ዝናብ ያመጣልን አንበጣው ነው› ብለው በማመናቸው በቶሎ ስላላሳወቁና ምስጢር አድርገው ስላቆዩት ነው። መንጋው በሦስተኛ ዙር የሚመጣ ከሆነ፣ ከፍተኛ ውድመትና ኪሳራ ማስከተሉ አይቀርም። እንደሚታወቀው ወቅቱ የእርሻ ወቅት ስለሆነ።››
እንዲህ ያለ ከፍተኛ መጠን ያለው አንበጣ በኢትዮጵያ ሲከሰት ከ25 ዓመታት በኋላ ነው። በኬንያና አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ወደኋላ 70 ዓመታትን ይሻገራል።
ምልሰት
በምልሰት ወደኋላ አቅንተን በመርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የተጻፈውን ‹የኻያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ› የተሰኘ መጽሐፍ እንሳፈር። ይህም ወደ 1922 ይመልሰናል።
በዛን ዓመት የአንበጣ መቅሰፍት በአገር ላይ ወርዶ የቆላውንም የደጋውንም ሰብል ያጠፋ እንደነበር ተጠቅሶ ይገኛል። ‹‹በጊዜውም ግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ የአደጋውን ከባድነት ስለተመለከቱ ሕዝቡ ምህላ ይዞ በጸሎት እግዚአብሔርን እንዲለምን አደረጉ። ጉዳት ለደረሰበት ሁሉ የምህረት አዋጅ አስነገሩለት።›› ሲሉ መርስዔ ኀዘን አስፍረውታል። መስከረም 11 ቀን 1922 የወጣው የዚህ አዋጁ የተወሰነ ክፍል እንዲህ ይላል፤
‹‹…በየአደባባይ ለነገር የተቀመጥህ ሰው በየቤት ገብተህ እስከ ታኅሳስ ልደታ አዝመራህን ሰብስብ። …የዘንድሮውንም የ1922 ድሃው መኸሩን እንዲሰበስብና በአንበጣ የተጎዳውም አገር በጭራሽ እንዳይጠፋ፣ ለአንድ ዓመት የዳኝነትና የውርርድ ዕዳ ግማሹን እንዲከፍል አድርገናል።
…ቆላ አገር ግን በድርቅና በውርጭ በአንበጣም በችግር ምክንያት ሰብል ስቶብህ ከ1919 ከሦስት ዓመት ወዲህ ቤትህን ዘግተህ፣ በጭራሽ ተሰደህ፣ ቦታህን ለቀህ የሄድክ ሰው ከተሰደድህበት አገር ተመልሰህ ገብተህ እረስ። ያለፈውን የግብር ዕዳ ምረንሃል። ወደፊትም የጠፋብህን እርሻና ቤትህን የምታቀናበት ኹለት ዓመት ቀን ሰጥተንሃል።››
ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው። ከአንበጣ ጋር በተገናኘ የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳው የአውሮፕላን መድኃኒት መርጫ ሳይኖር በፊት በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1724 የበረሃ አንበጣ በተደጋጋሚ አልጄሪያን አጥቅቷታል። በአፍሪካ አንበጣን ለመከላከል ዓለማቀፍ ድጋፍ የተጀመረው ግን ወዲህ በ1905 በዓለማቀፉ የግብርና ተቋም ነው። ከ1930 ወዲህም በርካታ የጥናት ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ጥናቶች ነው አንበጣዎች በሚራቡበት ቦታ ላይ ሳያድጉ በፊት በጸረ ተባይ መድኃኒት ርጭት ማጥፋት እንደሚገባ የተመከረው።
በዓለማችን ከፍተኛውና ብዙ ወጪና ኪሳራ ያስከተለ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ከ1986 እስከ 1989 ሲከሰት ኢትዮጵያና ሶማሊያን አጥቅቷል። ይህን ችግር ያስከተለው የአንበጣ መንጋ የተነሳው ከኤርትራ እና ሱዳን ቀይ ባህር ድንበር ሲሆን፣ ይህም የበረሃ አንበጣ የሚራባበት ስፍራ እንደሆነ ብዙዎች በእርግጠኝነት ይናገራሉ።
በጊዜው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ይካሄድ የነበረውና ሠላሳ ዓመታትን የዘለቀው ጦርነት ትኩረት በመውሰዱ፣ የአንበጣ መንጋው በጊዜ እንዳይደረስበት ሆኗል። ከዛም በላይ በአራት ዓመታት ውስጥ አንበጣው ወደ 23 የአፍሪካ አገራት እንዲሁም ወደ እስያ አገራት ጭምር እንዲሰራጭ ጊዜ ሰጥቶታል።
በጊዜው ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ መንጋውን ለመከላከል ሥራ የሚውል 310 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል። ሆኖም የአንበጣ መንጋው እያደር የቀነሰው በነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ነው እንጂ በሰዎች ኃይል አልነበረም። በተመሳሳይ ከ15 ዓመታት በፊት የአንበጣ መንጋ በአፍሪካ ተከስቶ ይልቁንም በምዕራብ አፍሪካ በገንዘብ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የግብርና ምርት አውድሟል።
ስለ አንበጣ
ክረምት ሲገባ በልጅነት ከሚዘመሩ የልጆች ዜማዎች መካከል ‹አንበጣ አንበጣ ና ቡና ጠጣ!› የሚለው አይዘነጋም። ይህኛው በዚህ አውድ የተነሳው አንበጣ ግን የልጆች መዝሙሩ ላይ እንዳለው ዓይነት አንበጣ ቡና የሚጠጣና ጠጥቶ አመስግኖ የሚወጣ አይደለም።
አንዱ የበረሃ አንበጣ በቀን 2 ግራም እህል ይመገባል። ትንሽ ይመስላል እንጂ አይደለም። ይህም ከራሱ ክብደት ጋር የሚቀራረብ ነው። የተወሰነ የሚባል ወይም አማካይ ብዛት ያለው የበረሃ አንበጣ መንጋ ታድያ በአንድ ቀን ዐስር ዝሆኖች የሚመገቡትን አልያም የ2500 ሰዎች ሊመገቡት የሚችሉትን እህል ያወድማል።
የአንበጣ መንጋ የምግብ ዋስትና ስጋት የሚሆነውም ለዚህ ነው። በአንድ በኩል አመጋገባቸው እንደተራቡ በብዛት መብላታቸውና እህል ማውደማቸው ሲሆን፣ በዛም ላይ ‹ይሄ አይስማማኝም› የሚሉትና የሚመርጡት የሰብል/የእህል ዓይነት የለም። አንድ የሰብል ማሳ ላይ ካረፉ ከ50 እስከ 80 በመቶ ሰብሉን ሳያወድሙ አይነሱም።
በዓለም ላይ የተለያዩና ብዙ ዓይነት አንበጣዎች ሲኖሩ፣ ይህ የበረሃ አንበጣ ተለይቶ የሚታወቀው በአጭር ጊዜ ከሚያደርሰው ጥፋት፣ ከሚጓዝበት ፍጥነት እንዲሁም ከሚራባበት መጠን አንጻር ነው። ሁኔታዎች እስኪመቻቹላቸው ‹ቡና የሚጠጣውን አንበጣ› ሆነው ቆይተው፣ ምቹ የአየር ጸባይ ባገኙ ሰዓት ግን በአጭር ጊዜ ተባዝተው በብዙ መንጋ የሚገኙ ናቸው።
ከሞሪታንያ በሰሃራ በረሃ አቋርጠው እስከ ሰሜን አፍሪካ፣ አረቢያን ፔኒስዌላን አቋርጠው እስከ ሰሜን ምዕራብ ሕንድ ድረስ 16 ሚሊዮን ሔክታር ቦታ ሸፍነው፣ ድምጽ ሳያሰሙ በምሥጢራዊ ቦታ ይቀመጣሉ፤ የበረሃ አንበጦች። አንዳንድ የአንበጣ መንጋዎች ምቹ ሥነ ምህዳር እና የአየር ንብረት ሲያገኙም፣ በ60 አገራት 32 ሚሊዮን ስኲር ኪሎሜትር ወርሰው ሊቀመጡ ይችላሉ። ይህ ማለት ከታንዛንያና ናይጄሪያ እስከ ስፔን፣ ሩስያ እና ሕንድ ድረስ ይዘልቃሉ ማለት ነው። በመቶኛ ሲሰላ የምድርን 20 በመቶ ሊሸፍኑ ይችላሉ።
ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ በእድገት ሂደታቸውም በቅርጽ፣ በቀለም፣ እንዲሁም በአካል መጠን ለውጥ ያሳያሉ። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውም በእድገት ሂደታቸው የሚወሰን ሲሆን፣ እርስ በእርስ በመሳሳብ መንጋን ይፈጥራሉ። አካባቢያዊና ተፈጥሮአዊ ምቹ ሁኔታዎች ተመቻችተው ሲቀጥሉላቸውም፣ አሁን ላይ እየታየ እንዳለው በመንጋ በመጓዝ ጥፋታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ።
አንድ አንበጣ ከሦስት እስከ አምስት ወር እድሜ ያለው ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ አራት ትውልድ ሊኖር ይችላል። ትክክለኛ የሙቀት መጠን ባለው ወይም ከዛ ተቀራራቢ በሆነ አፈርም አንዲት ሴት አንበጣ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎችን ትጥላለች። አንድ የአንበጣ መንጋ ብቻ በአንድ ስኩዌር ኪሎሜትር ውስጥ ከ40 እስከ 80 ሚሊዮን አንበጣን ይዞ ሊገኝ ይችላል። በኢትዮጵያም በዚህ ወቅት 10 ቢሊዮን የሚጠጉ አንበጣዎች ይገኛሉ።
አካሄዳቸውም እንደዛው በፍጥነት ነው። በአጭር ጊዜ ረጅም ርቀት ይጓዛሉ፣ ብዙ ቦታዎችንም ያካልላሉ። በ24 ሰዓት ውስጥም ከ150 የሚጠጋ ኪሎሜትር ያቋርጣሉ። በቀናት ልዩነት ውስጥም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ሊገቡ ይቻላቸዋል።
ባለሞያዎች እንደ ማሳያ መለስ ብለው በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1988 የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ያነሳሉ። ይህ መንጋ በሰሜን አፍሪካ ተነስቶ አትላንቲክ ውቂያኖስ አቋርጦ ወደ ደቡብ አሜሪካ መድረስ ችሏል። አሁንም ታድያ ተከስተው ያሉ የአንበጣ መንጋዎች ባህሪያቸውን ሳይለቁ ቀጥለው፣ ቀይ ባህርን በተደጋጋሚ ሲያቋርጡ ይታያል።
በኢትዮጵያ ያለው የአንበጣው የስርጭት አካሄድ ከዝናባማው ወቅትና ከቦታ ቦታ እንዳለው የአየር ጸባይ ለውጥ ይለያያል። የበረሃ አንበጣ የመራቢያ ጊዜም ከዝናባማ ወቅትና ከእርሻ ወቅቶች ጋር የተሳሰረ ነው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሁም በጎረቤት አገራት መካከል የሚያደርገው ጉዞም ይህን መሠረት ያደረገ ነው።
ከዛም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ እና እየጨመረ ያለው የአፈር እርጥበታማነት አልፎም አፈሩ እርጥብ ሆኖ የሚቆይበት ጊዜ ይራዘማል ማለት ነውና፣ ይህም የአንበጣ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደርገዋል።
ምንም እንኳ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በበረሃ አንበጣ በተደጋጋሚ የተጠቁ አገራት ቢሆኑም፣ በክልሉ ይህን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል አልፎም የተጎዱ አካባቢዎች ተመልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ ተቋማዊ አቅም የለም፤ አልተፈጠረም።
የመከላከል ሥራና ፈተናው
ዓለምና የዓለም አገራት የአንበጣ መንጋ ስጋት ለጣለባቸው አገራት ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ይታያል። ከምግብ፣ ከጤና፣ ከሰዎች ደኀንነት፣ ከእርሻና ግብርና መሰል ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ያላቸው ዓለማቀፍ ተቋማትም ስለ አንበጣ መንጋው እለታዊ መረጃዎችን በማውጣትና በማጋራት፣ ስጋቶችና ሊደረጉ የሚገባ ጥንቃቄዎችንም በማሳሰብ እየሠሩ ይገኛሉ።
ኤን.ፒ.አር የተባለ አውታር ከአንድ ወር በፊት የአገራትን የመከላከል ሥራ በተመለከተ ባወጣው ዘገባ፣ ከገንዘብ እጥረት በተጓዳኝ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ያሉባቸው አገራት የሰብል ተባዮችን እንዲሁም አረምን ማጥፋት ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሆንባቸው ጠቅሷል። ይልቁንም ከአንበጣ ጋር በተገናኘ ለብዙ ዓመታት ክስተቱ ርቋቸው የቆዩ ሲሆኑ፣ መንጋውን ለመከላከል ተገቢው ቁሳቁስና ግብዓት ስለማይኖራቸው ይቸገራሉ ይላል።
እናም ቋሚ የሆነ የመለካከያ መሠረተ ልማትና አስፈላጊ ግብዓት ካልተሟላ፣ ሥራው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ይሆናል፣ ወደፊትም ድንገት የአንበጣ መንጋ ሲከሰት መሯሯጥ ይመጣል ሲሉም በዘገባው አስተያየት የሰጡ ባለሞያዎች ተናግረዋል። ስለዚህ ሂደቱም እስከ ዝንት ዓለም እንዲሁ ይቀጥላል ማለት ነው የሚል ስጋትም አለባቸው።
አሁን ላይ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ውጤታማ ነው ተብሎ የሚታመነው የጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት ነው። ምንም እንኳ በብዝኀ ሕይወትና በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል የሚል ስጋት ቢኖርም፣ ከማሳዎች ላይ አንበጣዎችን ከማባረር ተጓዳኝ አማራጭ ሆኗል።
በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የተባለው ክፍል በአገሪቱ አንበጣን ጨምሮ የተባይ መቆጣጠርን ሥራ እንዲመራ ኃላፊነት ተጥሎበታል። በጎሳ መሪዎችና በክልል ግብርና ኃላፊዎች መካከልም የመረጃ ልውውጥ መንገድ ተፈጥሯል። ነገር ግን በ2018 የጸረ ተባይና ኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች ኪራይ፣ የኬሚካል ግዢ እንዲሁም አስፈላጊውን የሰው ኃይል ማሟላት በመዘግየቱ፣ አልፎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አሁን ደግሞ በኮቪድ 19 መከሰት ምክንያት፣ የአንበጣ መቆጣጠር ሥራው ሊጓተት ችሏል።
መረጃዎችን በየደረጃው ካሉ አካላት ከመጠየቃችን በተጨማሪ እለታዊ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ እያከናወንን ነው ያሉት በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ አማካሪ ዘብድዮስ ናቸው። ‹‹ሸክሙና ኃላፊነቱ ኢትዮጵያ ላይ ነው ያለው›› ያሉት ዘብድዮስ፣ ይህም የሆነው ከሌሎች ጎረቤት የአፍሪካ አገራት አንጻር ኢትዮጵያ ያላት አቅም የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ነው። ‹‹በጠቅላላው በምሥራቅ አፍሪካ አገራት የተቀናጀ ቁጥጥርና ክትትል እንዲኖር ስንል ኢጋድን ጠይቀናል›› ሲሉም ተናግረዋል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር 2012 የግብርና ሚኒስቴር የአንበጣ ምላሽ ፕሮጀክትን በሚመለከት ያወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው፣ የበረሃ አንበጣን ለመዋጋት 63 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ከዚህም ውስጥ 43 ሚሊዮን ዶላሩ በበረሃ አካባቢዎች ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ሲሆን፣ የቀረው በዚህ አንበጣ ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች ኑሮና ደኅንነት እንዲሁም መልሶ ለማቋቋም የሚውል ይሆናል።
የግብርና ሚኒስቴር ለክትትልና ለኬሚካል ርጭት የሚያገለግሉ ስድስት አውሮፕላኖችን ወደ ሥራ ያሰገባ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሦስቱ በኪራይ የተገኙ ናቸው። በመንጋው በተወረሩ አካባቢዎችም 41 ተሽከርካሪዎች ተመድበዋል። በእነዚህ ስፍራዎች የሚሠሩ ሰዎችም የውሎ አበል ይፈልጋሉ፣ ያስፈልጋቸዋል።
የኢፌዴሪ መንግሥት ለዚህ የአንበጣ ቁጥጥር ሥራ አስቀድሞ ካወጣውና አገልግሎት ላይ ከዋለው 120 ሚሊዮን ብር ላይ 166 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ጨምሯል። ይህም የአውሮፕላኖቹን ነዳጅ ጨምሮ የኬሚካል፣ እንዲሁም ለ41 ተሽከርካሪዎች ነዳጅ፣ ለመስክ ሠራተኞችም የአበል ክፍያ የመሳሰሉ ወጪዎችን የሚሸፍን ነው።
ከኹለት ዓመት በፊት ታኀሳስ ወር ወይም በአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ ነበር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከ600 በላይ ለሚሆኑ በሥራው የተሰማሩና የሚመለከታቸው ግለሰቦች በተለይም በክልል ከተሞች ሥልጠናዎችን መስጠት የጀመረው።
ዘብድዮስ ታድያ ይህን በሚመለከት ሐሳባቸውን ሲሰጡ፣ መንግሥት ለዚህ ሥራ የመደበው ገንዘብ ከዓለማቀፉ ከሚገኘው ድጋፍ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ያነሱት። በአንጻሩ ደግሞ አንበጣው ከአሁን በላይ ሰብል አውድሞ ቢሆን ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም ለመደገፍ ሊወጣ ከሚችለው ገንዘብ አንጻር አንበጣውን ለመከላከል የሚጠየቀው ገንዘብ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ነው አነጻጽረው ያስቀመጡት።
የአንበጣ መንጋ የመከላከል ሥራውን የኮቪድ 19 መከሰት ደግሞ የበለጠ ፈትኖታል። እንደው ለማሳያ አንኳ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ለጸረ ተባይና ኬሚካል ርጭት የሚውሉ አውሮፕላኖችን ለማስገባት ጥረት ያደረገች ቢሆንም በኮቪድ 19 ምክንያት ግን ሊዘገይ ችሏል።
እንደ ጌቱ ገለጻ ደግሞ፣ ለመከላከል ሥራው የሚያስፈልገው ወጪ ከእለት እለት እየናረ ነው። ብዙ ባለሞያዎች፣ ባለሥልጣናት፣ ተሽከርከሪዎች፣ አውሮፕላኖች እና ግብዓቶች ለዚህ አንበጣ ሥራ ብቻ ተሰጥተዋል። ይህ የሰው ኃይልና ሀብት በሌላ የልማት ሥራ ሊውልና ብዙ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ነበር። ገበሬዎችም አንበጣን በማባረር ጊዜያቸውን እያጠፉ መሆኑንም በቁጭት ገልጸዋል።
አክለውም አሉ፤ ‹‹በጠቅላላ ወጪው ብዙ ነው። ነገር ግን የሰብል ማሳዎችን እያዳንን ነው። አንበጣውም ሆነ ኮቪድ 19 የምግብ ዋስትና ችግርን ሊያስከትሉ ይችላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ (በክልል መንግሥትና ቢሮዎች መካከል) ትብብርና ተጋግዞ መሥራት አለ፣ ተመሳሳይ ቅንጅት ግን በጎረቤት አገራት መካከል አናይም።››
አሁን በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የአንበጣውን ተጽእኖ ለመቀነስ የሚደረግ ጥረት አንበጣውን ከሰብል ማሳዎች እንዲርቅ ማባረር ነው። የአንበጣ መንጋ የሚራባባቸውን ስፍራዎችን ለይቶ አንበጣዎች ገና ሳይፈለፈሉ የማጥፈት ሥራ ግን ደካማ ነው ብለዋል። በእርሻ ቦታዎች የሚረጩ ኬሚካሎችም ሃምሳ በመቶ የሚሆኑትን ብቻ ነው የሚያጠፉት። ምክንያቱም ከባድ ኬሚካል ሰብሎቸን እንዲሁም ሰዎችን ሊጎዱ ስለሚችሉ ነው።
አገራት እንዴት ሰነበቱ?
የአንበጣ መንጋ በስፋት ከተሰራጨባቸውና ጥፋት እያደረሰባቸው ያሉ አገራት እህሎችንና ሰብሎችን ለመጠበቅ የሚቻላቸውን ጥረት ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ። የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅትም (ፋኦ) ይህን ሂደትና ደረሰበትን ደረጃ በድረ ገጹ ላይ በየጊዜው ያስነብባል። ከዐስር ቀናት በፊት ይፋ ባደረገው ይኸው መረጃ መሠረትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ኦማን፣ ፓኪስታን እንዲሁም ሕንድ ያሉበትን ሁኔታ አቅርቧል።
በኬንያ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ላይ የአንበጣ መንጋው መጠን ቀንሷል ተብሏል። ያም ሆኖ ቱርካና ተብሎ በሚጠራውና በአየርም በመሬትም የአንበጣ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ በሚሠራበት አካባቢ አሁንም መንጋው እንዳለ ነው። ይህ መንጋም በሰሜናዊ አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን ሊሄድ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው። የተወሰነ መንጋም ድንበር አቋርጦ ወደ ሰሜን ምሥራቅ ኡጋንዳ ሊገባ ይችላል ተብሏል።
ያም ሆኖ እየተካሄደ ባለው የቁጥጥርና የመከላከል ሥራዎች ከኬንያ ወደ ጎረቤት አገራት የሚሄዱ የአንበጣዎች ብዛት መጠን አነስተኛ ሊሆን እንደሚችልም ተቀምጧል። ይህም ስጋቱን በተወሰነ መጠን ሊቀንሰው ይችላል።
በሶማሊያ የመሬት እንዲሁም ከአየር ላይ የተለያዩ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ነው ፋኦ በድረ ገጹ ያሰፈረው። ይህም ገና እየተፈለፈሉ ያሉና በሶማሊያ ሰሜን አቅጣጫ ሐርጌሳ እና ጋሮዌ በተባሉ አካባቢዎች መካከል የሚገኙት ላይ ነው የቁጥጥር ሥራው እየተካሄደ ያለው።
መንጋው ታድያ በምሥራቅ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ነውም ተብሏል። ይህም ጉዟቸው ቀጥሎ ወደ ሕንድ ውቂያኖስ እንደሚደርስ ሲጠበቅ፣ ሕንድ እና ፓኪስታን ድንበር ላይ ሊደርስ ይችላል፤ እንደ ፋኦ ዘገባ።
በየመንም ፈተናው ቀላል አይደለም፣ ይልቁንም ዝናብ ከመጣሉና በአንዳንድ ከተሞች ጎርፍ መከሰቱ ችግሩን ድርብርብ አድርጎታል። አንበጣውም በየመን የተለያዩ አካባቢዎች መራባቱን ቀጥሏል። በቀይ ባህር ወደብ አካባቢ ይደርሳሉ የሚል ከፍተኛ ስጋትም አይሏል። በዛም አሁን ካሉበት መጠን በላይ ሊራቡና የሚያደርሱትን አደጋም በዛው መጠን ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ።
በሱዳን የአንበጣ መከላከል ሥራው አንዳንድ አካባቢዎች ውጤታማ ሲሆን፣ በነጭ ናይል፣ ናይል ቫሊ እና በኮርዶፋን ግዛት ሰሜናዊ ክፍል አሁንም አንበጣዎች በብዛት ይገኛሉ። ከሱዳን ተነስቶ ወደ ኬንያ የገባ አንበጣ እንደሌለም ፋኦ ጨምሮ አንስቷል።
በተመሳሳይ በኦማን የአንበጣ መንጋ መከላከል ሥራው ሲቀጥል፣ በቅርቡ ከኦማን ተነስቶ ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራት የሄደ የአንበጣ መንጋ እንደሌለም ተጠቀሷል።
በፓኪስታን አስቀድሞ ዝናብ ባገኙ እርጥበታማ አካባቢዎች አንበጣዎች እየተፈለፈሉ ነው። ይህም የአንበጣ መንጋውን በከፍተኛ መጠን ሊጨምረው እንደሚችል ስጋት ውስጥ ተገብቷል። በሕንድም በተመሳሳይ ምቹ የአየር ሁኔታ ያገኙት አንበጣዎች እየተፈለፈሉና እድገታቸውን እየጨረሱ ይገኛሉ። በዚህም መካከል ታድያ በመከላከል ሥራዎች በሂደት ላይ ናቸው፣ ፋኦ ብሏል።
የአፍሪካ ምዕራባዊ ክፍል ብዙም በአንበጣ አልተጎዳም። በሰሜን ምሥራቅ ሞሪታኒያ፣ በሰሜን ናይጄሪያ እንዲሁም በቻድ ምዕራብና ምሥራቅ ክፍሎች ላይ ብቻ ጥቂት ቁጥር ያላቸው አንበጣዎች ተስተውለዋል። ምንም እንኳ ታድያ በአንበጣ መንጋ የመወረር ስጋቱ በአካባቢው ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ‹አይመጣልን ትተሽ ይመጣልን ያዢ› እንዲሉ፣ አገራቱ ዝግጅቶቻቸውን በሚገባ አድርገው ቁጥጥር ክትትልም ሳያቋርጡ እንደሚገኙ የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት አስነብቧል።
በኢትዮጵያም ከላይ እንደተጠቀሰው በርካታ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነበር፣ የመከላከል ሥራዎችን ቀጥለዋል። በፋኦ ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ ደቡባዊ ክልል ከኬንያ የተነሱ አንበጣዎች ታይተዋል። በአማራና ትግራይ ክልል ሰሜናዊ ክፍልም በተመሳሳይ የአንበጣ መንጋዎች ይገኛሉ። በቀጣይም አንበጣ በአካባቢዎቹ ሊራቡ እንደሚችሉ ሲጠበቅ፣ የተወሰነ መንጋም ከየመን ተነስቶ ኢትዮጵያ ሊያርፍ ይችላል ተብሏል።
ቀጣይ እርምጃ
ዘብዴዎስ ለአንበጣ ጉዳይም ከኮቪድ 19 እኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል። ኮቪድ 19 አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግ መሆኑ የታወቀ ሆኖ፣ ሀብት ማሰባሰብ፣ የሰው ኃይል ማደራጀት፣ ግብዓት ማሟላት፣ አንበጣውን መከላከልና ጉዳት የደረሰባቸው በቶሎ እንዲያገግሙ ማድረግ ላይም በተመሳሳይ ፈጠን እርምጃ ይፈልጋል ባይ ናቸው። በኮቪድ 19 ላይ ብቻ ሳይሆን አንበጣው የደረሰበትን ደረጃም በሚመለከት መንግሥት መረጃዎች ሊደርሱት ይገባል ሲሉም አክለዋል።
‹‹በክትትል ሥራው ፈጣን የአጭር የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ አሠራርም ያስፈልጋል። በተለይም የክልል መንግሥታት የአንበጣውን ጉዳይ በመከታተል ረገድ በበቂ ሁኔታ ፍጥነት የላቸውም። የተወሰኑ ባለሥልጣናትና ባለሞያዎች ያውም በፌዴራል ደረጃ ነው ለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት የሰጡት›› ሲሉም ተናግረዋል።
ጌቱ በበኩላቸው በአንጻሩ በአንበጣው ምክንያት ስጋት ላይ የወደቀው የምግብ ዋስትና ጉዳይ ጥሩ እድል ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ዕይታ አላቸው። ይልቁንም በእርሻና ግብርናው ዘርፍ የፈጠራ ሥራ እንዲበረታና አዳዲስ ሐሳቦች እንዲገኙ ያደርጋል ሲሉ ይሞግታሉ። ይህም በኮቪድ 19 ምክንያት ዲጂታል የሆነ የግብርና ትምህርት ይሰጥ መጀመሩን አያይዘው ጠቅሰው ነው።
በኦሮሞያ ግብርና ቢሮም የግብርና ምርቱን በ36 ሚሊዮን ኩንታል አሳድጎ 198 ሚሊዮን የማድረስ እቅድ እንደያዘ ነው ያነሱት። ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር 162 የነበረ ነው። የዚህ ዓመት ማለትም የ2012 የምርት ዓመት ከጠቅላላ አገራዊ ምርት ማለትም ከ335 ሚሊዮን ኩንታል እህል ውስጥ 48 በመቶውን የሚሸፍን ነው።
አዲስ ማለዳ ዘብድዮስን ነባራዊ ኹነትን በሚመለከት ከሰሞኑ ምን አዲስ ብላ ጠይቃቸው ነበር። እርሳቸውም በአገር ውስጥ ያለውንና ከጎረቤት አገራት ገባውን አንበጣ በደንብና በሚገባ መቆጣጠር እየተቻለ ነው ብለዋል። ምንም እንኳ አሁንም ቀጥሎ ከባድ ጊዜ ሊመጣ እንደሚችልና የአንበጣ መንጋው ቁጥር መበራከት ሊያደርስ የሚችለው ጥፋት ቢያሰጋም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለነው ሲሉ ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012