ስለማን ትሠራላችሁ?

0
443

የሴቶችና የሕጻናት ጉዳይ ሲነሳ በተለይም የሴቶች መብት ጉዳይ ረዕስ በሚሆንበት መድረክ ብዙዎች ሲናገሩ እንሰማለን። አንዳንዴ ደግሞ ብዙ ሴቶች ተደፈሩ፣ ተጠለፉ፣ ያለእድሜ ተዳሩ፣ ተገደሉ ሲባል የሚጮኽና አለን የሚለው ይበዛል። ከተጎዱ ሴቶች ይልቅም የ‹ተቆርቋሪ ነን› ባዩን እንባ አብዝተን እናያለን።

ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ይህን ባደረጉ ቁጥር ብዙ አደባባይ ወጥተው ለመናገር እድሉን ያላገኙ ሰዎች ወይም ነገሩ ሕመም ሆኖ የኖረበት ሕዝብ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋን ይሰንቃል። ይህ ግን ድምጻቸውን ሊያሰሙ ቃል የገቡ ሰዎች በሚጠቅሱትና ሊጋፉ ‹ባልቻሉት› የተለየ ምክንያት እንደ ጉም ተንኖ፣ እንደጢስ በንኖ ይጠፋል። በኢንተርኔት ላይ ‹ጉግል› ሲደረግ የሚገኝ ታሪክ ብቻ ይሆናል።

ሰዎች ስለምን የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ላይ ይሠራሉ? በጀት የሚመደብላቸው የሉምን? የሥራ እድልና ጥሩ ገቢ የሚገኝበት አውድስ አይደለምን? ስንቶች ይህን ትወና ተወኑ? ሁሌም በመኪና ወስደው ብዙ ሆነው ደፍረው ሕይወቷን የነጠቋት የሃና ላሎንጎ ጉዳይ ትዝ ይለኛል። ትንሿ ጫልቱም እንደዛው።

እነዚህ ንጹሕናቸውን ይዘው ሳይገባቸው የሄዱ ልጆች ጉዳይ ያስጮኻቸው ሰዎች፣ የሕዝብን ቁጣ ወክለናል ብለው ሕዝብ ድምጹን እንዳያሰማ እንዳደረጉ ነው የሚሰማኝ። እናም ስለማን ትሠራላችሁ ብለን ልንጠይቅ የግድ ይለናል።

በቅርቡም በርካታ ሕጻናት ተደፍረዋል የሚለውን ዘገባ ተከትሎ ብዙ የጥበብ ሰዎች ተነሱ። የተወሰኑት በጥቂት ሳምንት ውስጥ የሕጻናቱን ጉዳይ ትተው ስለክብራቸው፣ ስለሥማቸው ሲከራከሩ ሰማን። ለተደፈሩ፣ በመንፈሳቸው ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሸክም ለተጣለባቸው ሕጻናት እንሞግታለን ያሉ ሰዎች፣ ‹እኔን ለማጥቃት ነው› የሚልን ቃል ሲያወጡ ማየት ያማል!

ሁሉም የኪነጥበብ ሰው በአንድ የጥበብ ባለሞያ እኩይም ሆነ ሰናይ ምግባር አይወከልም፤ ግልጽ ነው። ገና በሥራው አሐዱ ነፍሳቸው የተጨነቀች ሕጻናትን እረዳለሁ እያሉ ‹ሥሜ ተነሳ…ክብሬ ተነካ› ማለት እንዴት ይገጥማል? ለሽልማት ነው የምንሠራው? ነገሩ ሁሉ ‹ማኅበራዊ ኃላፊነቴን ልወጣ ብዬ› ዓይነት የይስሙላ ነገር እየመሰለኝ ነው።

የምንሠራው ስለ ዝና ነው? የምንሠራው ጎበዝ ለመባልና ለመደነቅ ነው? ሠሩ ለመባል ነው? የእውነት መቆርቆር እንዲህ ነው? ተሳስቼ ከሆነ እታረማለሁ፤ ግን አይመስለኝም። በሥማቸው እንሠራለን እያልን ሥማቸውን አንስተን በእነዚህ ልጆች ስለክብራችን የምንጣላባቸው ከሆነ፣ ለጊዜአዊ ስሜታቸው ጥቃት ያደረሱትን ለመውቀስ፣ የወቀሳውን ድንጋይ ለመጨበጥ ብቁ ነን?

አይመስለኝም። ለዛም ነው የምጠይቀው፤ ስለማን ትሠራላችሁ? የእውነት ጉዳት ስለደረሰባቸው ሴቶችና ሕጻናት ወይስ ለኑሯችን? ዘርፉ በጀት ስላለው ነው? የእውነት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ምን እየሠራን ነው? ካልሆነ መንግሥትን ለመውቀስና በጎደለ እሞላለሁ፣ ሕግ እንዲቀየር እጥራለሁ ሁሉ ባዶ ናቸው። እንዲሁ ለመኖርማ ሴቶችና ሕጻናትን ማዕረግ አድርገው የሚጠሩ ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አሉን።

እውነት ነው! ስለአገር፣ ስለትውልድ ተጨንቀው፣ በልጆቻቸው የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሲመለከቱ ብዙ መሥራት እንዳለባቸው አምነው የሚሠሩ አሉ። ስለ ሰው የሚሠሩ። እነዚህን ሰዎች ለማመስገን ጊዜ ብንሰጥ የሚወቀሱት ያንሱ ነበር። የበረቱትን ከማገዝ ቀድመው በምግባር የወደቁት ላይ መተኮስ ለምዶብን ነው። ይህ ሁላችን ማስተካከል ያለብን ነው። ለጊዜው ግን እንጠይቅ፣ እንጠያየቅ። ሴቶችና ሕጻናትን የምትጠሩ ሰዎች፣ ስለማን ነው የምትሠሩት?
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here