የህዳሴው ግድብ ድርድር ውጤትና ቀጣይ መዳረሻ

0
756

የኢትዮጵያን የነገ ብርሃን ፈንጣቂና የልማት ተስፋ አንፀባራቂ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሀብት ተገንብቶ ኢትዮጵያን ለማልማትና ከጎረቤት ሀገሮች እኩል እንድትራመድ ሊያስችላት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተከትሎ ግብጽ የማይጨበጥ እና በቀናት ልዩነት የሚቀያየር ዓባይ የኔ ነው፣ በዓባይ ላይ አዛዧ እኔ ልሁን የሚለው የህልመኝነት አባዜዋ በኢትዮያ፣ በሱዳንና በራሷ በግብጽ መካከል የኢትዮጵያ አብራክ ክፋይ በሆነው ዓባይ ግድብ ላይ የረዥም ጊዜ የሦስትዮሽ ድርድሮች ተካሂድዋል።

በሦስቱ አገራት መካከል እስካሁን የተደረጉት ድርድሮች በግብጽ በኩል ይታይ በነበረው የከረረ ኢምክንያታዊ የተጎጅነትና በዓባይ ላይ አዛዥ ካልሆንኩ አሻፈረኝ ስትል በመቆየቷ የድርድር ሂደቱ ያለ መቋጫ አስካሁን ደርሷል። ይሁንና ኢትዮጵያ ግብጽ የምታቀርበውን ውል አልባ ጥያቄ ባለመቀበሏ የኢትዮጵያዊያንን የወደፊት የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የመጀመሪያውን ፈር ቀዳጅ መንገድ ጀምራለች።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን ህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች ድፍን ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል። የግድቡ ግንባታ አብዛኛውን የአገሪቱን ህዝብ በአንድ ዓላማ ያሰለፈ ቢሆንም፣ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይም ከግብጽ በኩል የሚነሳው ስጋትና ተቃውሞ አሁንም ድረስ መቋጫ አላገኘም። ግብጽ በኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነትና ልማት እንደማትቃወም በተደጋጋሚ ብትገልጽም፣ በሌላ በኩል ወንዙ የህልውና ጉዳይ ነው በሚል በግድቡ ላይ ያላትን ስጋት ስትገልጽ ቀይታለች። ይህንን ስጋትና አለመተማመን ለመፍታት ሌላኛዋን ወንዙ ተጠቃሚ አገር ሱዳንን ጨምሮ ሦስቱ አገራት በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በሦስቱ አገራት ለረጅም ዓመታት በዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት ላይ በርካታ ድርድሮች ተደርገዋል። ይሁን እንጅ ግብጽ ለዘመናት በዓባይ ውሃ ላይ ያለ እኔ ፈቃድ ማንም አያዝበትም በሚለው “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት” ይሉትን አባባል በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ ለማሳደር ሞክራለች።

የአገራቱ ድርድር ወደ አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት በአዲስ አበባና በካይሮ በሦስቱ አገራት መካከል በተደረጉት ድርድሮች ግብጽ ኢትዮጵያ እንድትስማማላት በምትፈልገው መንገድ ባለመገዛቷ፣ በድርድሩ ላይ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ አሜሪካ እና አለም ባንክ በሦስቱ አገራት መካከል በዋሽንግተን በተደረገው ድርድር በታዛቢነት ገብተው በስተኋላ አሜሪካ የግብጽ ቀኝ እጅ በመሆን ኢትዮጵያ ላይ ተጽኖ ለማድረግ በመሞከሯ ኢትዮጵያ ከድርድሩ እራሷን ባገለለችበት ጊዜ ነበር የአሜሪካ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት የተሸጋገረው ሚና መስመር መሳቱ ለአለሙ ማህበረሰብ ገሀድ የወጣው።

የሦስቱ አገራት ድርድር ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ ኀብረት
በሦስቱ አገራት የህዳሴው የውኃ አሞላልና የግድቡ አስተዳደርን በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር በወሳኝ ነጥቦች ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ድርድሩ በተደጋጋሚ አንድ ጊዜ ሲቋረጥ፣ አንድ ጊዜ ሲጀመር እንዲሁም ወደ አሜሪካ እና ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተመርቶ ያለ መቋጫ ወደ አፍሪካ ህብረት ሊመለስ መቻሉ ይታወሳል።

ለዓመታት ሲደረግ የነበረው በዚሁ ድርድር መግባባት ላይ ለመድረስ ካላስቻሉት የልዩነት ነጥቦች መካከል ግብፅ የህዳሴ ግድቡን ድርድር መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ወደፊት በዓባይ ውሃ የመጠቀም መብት የሚገድብ አንቀጽ በድርድሩ የስምምነት ሰነድ እንዲካተት በመፈለጓ እንደሆነ፣ ከኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በኩል በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ግብጽ ለአሜሪካ ኢትዮጵያን እጇን ጠምዝዘሽ እኔ በምፈልገው ተስማምታ እንድትፈርም አስገድጅልኝ አይነት የተማጽኖና የሴራ ስልታዊ ተንኮል መሸረቧን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት የጽጥታው ምክር ቤት በድርድሩ ላይ ተጽኖ ማሳደሩን በማስረዳት የሦስቱ አገራት ችግር “ለአፍሪካዊያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚል መርህ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት ተመልሶ በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በሆኑት ደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ መሪነት አስካሁን በተደረጉ ድርድሮች ግብጽ እንደተለመደው በማይያዝ በማይጨበጥ አቋሟ ስትወጣና ስትገባ ተስተውላላች።

ግብጽ በድርድሩ ስምምነት ላይ እንዳይደረስ ዋነኝዋ እንቅፋት እንደሆነች በኢትዮጵያ ቴክኒካል ተደራዳሪዎች በኩል የተገለጸ ሲሆን፣ ግብጽ ድርድሩ በዋሽንግተን ሲካሄድ በነበረው ድርድር ያሳየችው በዓባይ ግድብ ላይ የአዛዥነት ድርሻ ይኑረኝ አይነት ግትርነት በአፍሪካ ህብረትም ተደግሞ ኢትዮጵያ ከዓባይ ግድብ በላይ በራሷ ክልል ውስጥ ወደፊት የምታከናውናቸውን የልማት ስራዎች የሚገድብና ግብጽን አስፈቅዳ እንድትሰራ መፈለጓ ኢትዮጵያ በፍጹም የማትቀበለው በመሆኗ ድርድሩ መቋጫ አላገኘም።

ከዚህም አልፎ ግበጽ በኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት በተገነባው እና የኢትዮጵያ ብቻ የሆነውን ትልቅ የነገ ተስፋ የተጣለበትን የታላቁ የህዳሴ ግድብ በጋራ እናስተዳድረው እስከማለት መድረሷ ኢትዮጵያን ሳታስብ የግል ጥቅሟን ብቻ መፈለጓ ትልቁ ማሳያ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

ከሳምንታት በፊት በአፍሪካ ኀብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን የሚታወስ ሲሆን፣ ሦስቱ አገራት በ11 ታዛቢዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ለአስራ አንድ ቀናት ውይይት አድረገው ሐምሌ 7/2012 መጠናቀቁን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሩ ኢንጅነር ስለሽ በቀለ መግለጻቸው ይታወሳል። እስካሁን በተደረጉት ድርድሮች መሻሻሎች ቢታዩም በአጠቃላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ሚኒስቴሩ ጠቁመው ነበር።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆኑት አንባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግብጽ የምታነሳው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የወደፊት ተጠቃሚነት ላይ ጥላ የሚያጠላ ማንኛውንም አይነት ሀሳብ እንደማትቀበል እና በወደፊት ጥቅሟ ላይ ጽኑ አቋም እንዳላት አስታውቀዋል። አምባሳደሩ አክለውም ወደፊትም ቢሆን ግብጽ የፈለገችወን ነገር ብታመጣ ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቷን አደጋ ላይ የሚጥል ስምምነት እንደማታደርግ ጠቁመዋል። እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ግብጽ ወደፊት በሚደረጉ ድርድሮች ትስማማለች ብለው እንደሚምኑ እና ለተፋሰስ አገራቱም የሚጠቅመው የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ስምምነት ማድረጉ ነው ብለዋል።

በሦስቱ አገራት መካከል በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሲደረግ የነበረው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ አፍሪካ ኅብረት ቀደሞ የድርድር ነጥቦችን ገምግሞ ድርድሩ ዳግም እንደሚካሄድ መግለጹ ይታወሳል። የተቋረጠው ድርድር የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27/2012 እንደሚጀመር ቃል አቀበዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። አምባሳደሩ አክለውም በቀጣይ በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ አቋሟን እንደማትቀይርም ጠቁመዋል።

የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅና ፋይዳው
ኢትዮጵያ የታላቁ ህደሴ ግድብ የመረጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት ሐምሌ 14/2012 ተፈጥሮ ባደላት ዝናብ በድል አጠናቃ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የብስራት ዜና መሆኑ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለመሙላት አቅዳ ስትሰራ መቆየቷ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም የግድቡን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ስራ በኹለት ተርባይኖች ለማስጀመር ያስችላል።
የግድቡ ግንባታ አሁን ላይ ከባህር ጠለል በላይ 560 ሜትር ከፍታ የደረስ ሲሆን የግንባታ ሂደቱም እስከ 640 ሜትር ከፍታ እንደሚቀጥል ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት እቅዷን ያለ ምንም መስተጓጎል በድል መጠናቀቋ ወደፊት ለሚደረጉ ድርደርሮች እና ኢትዮጵያን ወክለው በግድቡ ጉዳይ ግብጾችን ለሚሞግቱ ግለሰቦች ከፍተኛ ወኔ እንደሚፈጥር ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያጋሩ ተደራዳሪዎች ጠቁመዋል።
በሦስቱ አገራት መካከል በሚደረገው ከኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ውስጥ አንዷ የሆኑት አዳነች ያሪድ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌቱን ማጠናቀቋ በተለይ ለተደራዳሪዎች የሚፈጥረው የሞራል መነቃቃትና ወኔ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ተደራዳሪዋ አክለውም “የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ትልቅ ታሪክ ነው። በፊት ስንደራደር የነበረው እየተገነባ በነበረ ግድብ ነበር። አሁን ውሃ በያዘ ግድብ ነው የምንደራደረው ለኛ ለተደራዳሪዎች ትልቅ ሞራል ፈጥሮልናል።” ሲሉ የሚያስገኘውን ጥቅም ያስረዳሉ።
አዳነች(ዶ/ር) አክለውም የውሃ ሙሌቱ እንደ አገር የፈጠረው መነቃቃት ለድርድሩ እና ለግድቡ መጠናቀቅ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩ ታሪካዊ ኹነት ነውም ብለውታል።

የዓባይ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቅ ለአገሬው ህዝብ ታላቅ ደስታን መፍጠሩ እና በህዝቡ በኩል ወደፊት ስላለው ዓባይን በድል ለማጠናቀቅ በገንዘብና በሞራል የሚደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ከማጉላቱም በላይ ዓባይ ተጠናቆ እውን እንደሚሆን የመጀመሪያው ማሳያ እንደሆነ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ዓባይ በመጀመሪያው ዙር ሞልቶ በመፍሰሱ ከመቀነታቸው እየፈቱ ያላቸውን አዋጥተው እዚህ ላደረሱት ኢትዮጵያዊያን የፈጠረው ደስታና መነቃቃት ታሪካዊ ቀን ሆኖ አልፏል።

ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዜደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለኢትጵያ የሚደርገውን ድጋፍ የመቀነስ ፍላጎት ማሳየቱን የውጭ ሚዲያዎች ሲዘግቡት እንደበር ይታወሳል። ፎሪን ፖሊሲ በተባለ መጽሔት ላይ በወጣው ዘገባ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን ድጋፍ ትቀንሳለች ስለተባለው ጉዳይ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ የትራንፕ አስተዳደር ይፋ የሆነ ስለጉዳዩ የሚገልጽ ምንም አይነት መረጃ እንዳልደረሳት ጠቅሰው፣ አንድ ባለስልጣን የተናገረውን ነገር ይዞ ያልተረጋገጠ ነገር ከማሰራጨት ያለፈ ነገር እንደሌለው ተናግረዋል።

አምበሳደሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ለረጅም ዓመታት የነበራትን መልካም ግንኙነት እንደምትፈልገው እና የኹለቱ አገራት ጥሩ ግንኙነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካም ነው የሚጠቅማት ብለዋል። አሜሪካ አደርግዋለሁ ብላለች የተባለውን ነገርም እንደማታደርገው እምነታቸው እንደሆነ ዲና ጠቁመዋል።

አዳነች(ዶ/ር) በበኩላቸው በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ድፕሎማሲያዊ ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ እውነት ስላላት እውነቱን እያስረዳን የአገራችንን ጥቅም በማስጠበቅ መክፈል ያለብንን ዋጋ እንከፍላለን በማለት ድል በሚጎናጽፍ ተስፋ ያብራራሉ።

የድርድሩ የወደፊት መዳረሻ እና የኢትየጵያ ጥቅም ማስከበር አቋም
የሦስቱ አገራት ድርድር ለአመታት ሲንከባለል ቆይቶ ዛሬ ላይ ደርሷል። የድርድሩ ነጥብና ዋና አጀንዳም በየጊዜው ሲለዋወጥ ይስተዋላል። በግብጽ በኩል የሚነሱት ከዕለት ዕለት ይዘታቸውን የሚቀያየሩ የመደራደሪያ ነጥቦችና አቋም ለድርድሩ አጀንዳና አቋም መለዋወጥ ዋነኛ ምክንያቶች አንደሆኑ ይነሳል። ዛሬም ግብጽ የዓባይ መገደብ እኔን ይጎዳኛል ከሚለው የሀሰት ፐሮፖጋንዳ አሁን እስከደረሰችበት ግድቡን በጋራ እናስተዳድረው እና በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ወደፊት ከዓባይ ግድብ በላይ በሚሰሩ የልማት ስራዎች ፈቃጅ ልሁን እስከማለት የደረሰ ጥያቄዋን አንግባ መጥታለች።

አንባሳደር ዲና ሚፍቲ የድርድሩን እና የኢትዮጵያን የወደፊት ጥቀም ማስከበር ላይ ወደፊት በሚደረጉ መንኛውም ስምምነቶች ኢትዮጵያን የሚጎዳ ሆኖ ከተገኘ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው እና የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለ ድፕሎማሲያዊ አካሄድ እንዲሆን የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ግብጽ ወደፊት በሚደረጉ ድርድሮች እንደምትስማማ አመላካች ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ተደራዳሪዋ አዳነች (ዶ/ር) እስካሁን የነበረው ድርድር ግብጽና ሱዳን ለዓባይ ወንዝ 86 በመቶ ውሃ ድርሻ ያላትን ኢትዮጵያን ድርሻ አልባ አድርገው ያስቡ ከነበሩ አገሮች ጋር እንደሆነ በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ እንደ ግብጽ በየሁኔታው የሚለዋወጥ አቋም የለንም ሲሉ አስረድተዋል። እኛ ኢትዮጵያዊያን እውነታን ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው ያሉት አዳነች(ዶ/ር)፣ ኹለቱ አገራት ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ሳትጠቀምበት የግላቸው አድርገው ሲጠቀሙበት የነበረውን ታሪክ ማስቀጠል ስለሚፈልጉ ኢትዮጵያ ያን ታሪክ እንደማትቀበለው እና አንዳችም የኢትዮጵያን በዓባይ ውሃ የመልማትና የወደፊት ጥቅም የሚጎዳ ሀሳብ ግብጽና ሱዳን ቢቀርቡ በፍጹም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አረጋግጠዋል።

እንደ አዳነች ገለጻ ግብጾች አሁን ላይ እውነታውን በተወሰነ ደረጃ እየተረዱ የመጡበት ነገር እንዳለ ጠቁመ፣ አሁንም እውነታው እስከሚገባቸው ድረስ እናስረዳለን ሲሉ ጠቁመዋል።

የፊታችን ሰኞ 27/2012 ያለ ስምምነት የተቋረጠው የሦስቱ አገራት ድርድር እንደሚጀመር የጠቆሙት አዳነች የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት የሚፃረር ማንኛውም አይነት አስገዳጅ ስምምነት እንደማትቀበል እና እስካሁን እውነትን በመያዝ የቀጠልንበትን መንገድ የሚያስቀይረን ኃይል የለም ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here