ለመጀመሪያ ጊዜ ፈሳሽ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተከፋፈለ

0
949

በ2012 ዓመት የምርት ዘመን በዓይነቱ ልዩ የሆነ የፈሳሽ ማዳበሪያ በኢትዮጵያ መከፋፈሉን ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ በተወሰኑ አካባቢዎች የመሬቱ እና አፈሩ ዓይነት እየተጠና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጉ የነበሩና በአንጻሩም በኹሉም ስፍራዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማይደረጉ ማዳበሪያዎች ከዚህ ቀደም ወደ አገር ውስጥ ይገቡ ነበር። የፈሳሽ ማዳበሪያው ግን በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ ቢደረግ ውጤታማ እንደሚሆን በመታመኑ መሆኑ ተጠቅሷል።

ከተለመደው የማዳበርያ አቅርቦት ጋር ተገናኝቶ አዳዲስ የግብርና ግብአቶችን በማስተዋወቁ ረገድ በምርት ዓመቱ 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የፈሳሽ ማዳበርያ እንደተሰራጨ የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የማዳበርያ ፍላጎቱ ከዚህ ቀደም ላቅ ባለ ሁኔታ መጨመሩን እና እንደውም የአዲሱ ፈሳሽ ማዳበርያ አይነት ፈላጊው በመብዛቱ እጥረት እያጋጠመ መሆኑም ተገልጿል።

እያደገ ከመጣው የማዳበሪያ ፍላጎት አንጻር በተገቢው ሁኔታ ማዳበሪያዎችን ማቅረብ እንዳልተቻለ እና በተለይም ደግሞ ከውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ጋር ተዳምሮ ችግሩን እንደሚያበረታው ተጠቅሷል። በተለይም ደግሞ የፈሳሽ ማዳበሪያው በአርሶ አደሮች ዘንድ ተፈላጊነቱ በመጨመሩ እና እንደልብ ማቅረብ ሳይቻል በመቅረቱ ዕጥረቱ መባባሱን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በ2012/2013 የሰብል ምርት ዘመን 14.58 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን የተለያዩ አይነት የአፈር ማዳበርያ ግዢ መከናወኑንም የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል። ከተገዛው ውስጥም 13.55 ሚሊዮን ኩንታል (92) በመቶው ማሰራጨት መቻሉም ነው በባለፈው በጀት ዓመት ሪፖርት ላይ የተመላከተው።

ከተሰራጨው ማዳበርያ የቀረውን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በምርት ዓመቱ የአሮጌ ኬሚካሎች እና መርጫ መሣሪያዎች አቅርቦት የብር 658.9 ሚሊዮን ግዢ ተፈፅሞ፤ ለክልሎች በግብርና ሚኒስቴር ድልደላ መሰረት በመከፋፈል ላይ እንደሚገኝ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2012 በጀት ዓመት ሪፖርቱ አካቷል።

ከዚያም ባለፈ በበጀት ዓመቱ ከምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከ2011 እስከ 2012 የምርት ዘመን በሰፋፊ ኮንትራት የምርጥ ዘር አባዢ መሣሪያዎች እና በአርሶ አደር ማሳ በድምሩ 11,845 ሄክታር መሬት ላይ ዘር በማባዛት 254,774 ኩንታል የዘር ምርት ለማምረት ታቅዶ፣ 12,607 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 255,717 ኩንታል ምርት መመረቱ ተነስቷል።

ኮርፖሬሽኑ ከሰፋፊ የግል እና የመንግሥት እርሻዎች እና አርሶ አደሩ ማሳ ላይ በኮንትራት ካባዘው ዘር 94,980 ኩንታል በብር 174.29 ሚሊዮን ግዢ ለመፈፀም ታቅዶ 82,964 ኩንታል በብር 169 ሚሊዮን ግዢ ተፈፅሟል። ይህም አፈፃፀሙ ከታቀደው 87 በመቶ መሆኑም ነው የተገለፀው።

ከዛም በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ በመደበኛ ኦፕሬሽን ለአርሶ አደሮች እና በግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩ የእርሻ ልማቶች እንዲሁም በኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በድምሩ 4,500 ሄክታር እርሻ፣ 2,000 ሄክታር ክስካሶ እንዲሁም 1,000 ሄክታር መስመር የማውጣት ሥራዎችን በማከናወን የብር 15,024 ሚሊዮን ገቢ ተገኝቷል።

የማጓጓዝ ሥራውም በበጀት ዓመቱ ሲታይ ደግሞ 21,555 አጭዶ ውቂያ፣ 3,780 ቆሞ ውቂያ፣ 4,279 ኩንታል ደግሞ በቆሎ ፈልፍሎ እና 5,271 ኩንታል የምርት መጓጓዝ ሥራዎችን በማከናወን 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ገቢ ለማግኘት ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎችን አቅርቦት በማከናወን 129.19 ሚሊዮን ገቢ መመዝገቡ ነው በሪፖርቱ የተመላከተው።

ከማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጋር ተያይዞም በበጀት ዓመቱ 30 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የእንስሳት መድኃኒቶችን በማቅረብ ለመሸጥ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ 5.3 ሚሊዮን ብር ብቻ ማከናወን መቻሉን እና አፈፃፀሙ ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር 18 በመቶ መፈፀም መቻሉ ተገልጿል። ይህም የሆነው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ነው።

በበጀት ዓመቱ ኮርፖሬሽኑ ከዕቅዱ 92 በመቶ የሚሆነውን በማከናወን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here