የከተማ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከ11 ወደ 83 ከተሞች ሊያድግ ነው

0
1298

የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ከዚህ በፊት ይሰጥ ከነበረበት 11 ከተሞች ወደ 83 ከተሞች አገልግሎቱን ለማስፋት የ730 ሚሊዮን ዶላር ስልታዊ የግዥ እቅድ መያዙን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ72 አዲስና በ11 ነባር ከተሞች በድምሩ 83 ከተሞች ለማስፋት ከዓለም ባንክ 500 ሚሊዮን ዶላር እና በኢትዮጵያ መንግሥት 230 ሚሊዮን ዶላር፣ በድምሩ 730 ሚሊዮን ዶላር በጀት በማድረግ የፕሮግራሙን ማስፈጸሚያ መመሪያ እና የ18 ወራት ስልታዊ የግዥ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

እንዲሁም ፕሮግራሙን ለማስጀመር የሚያስችሉ የቅደመ ዝግጅት ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ አዲስ የሚገቡ 72 ከተሞች በፌዴራል የቴክኒክ ኮሚቴ በኩል በማፅደቅ ከክልሎቹ ጋር በመቀናጀት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከተሞች እንዲለዩ እንደተደረገም ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ለሚተገበርባቸው 72 ከተሞችና የክልሎች እንዲሁም በየደረጃው ለሚደራጁ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አዲስ መዋቅር በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላት የማድረስና በውይይት የማዳበር ሥራ መሥራቱን ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል።

ኤጀንሲው የአምስት ዓመት እቅድ መንደፉን ያመላከተ ሲሆን፣ ከእቅዱ መካከል በ2013 በጀት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና እቅድ ዋና ዋና ግቦች እና የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ከ11 ከተሞች ወደ 83 ከተሞች ማስፋት የሚለው እንደሚገኝበት የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቦዘነች ነጋሽ ጠቁመዋል።

በመነሻ እቅዱ ላይ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በከተሞች ሰባት ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷልም ተብሏል። ከዚህም ውስጥ በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት የሚፈጠረው የሥራ እድል 1 ሚሊዮን 403 ሺሕ 860 እንዲሆን መነሻ እቅድ መቀመጡ ተመላክቷል። ከዚህ ውስጥም 75 በመቶ ወጣቶች እና 50 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ከዚህ በፊት በ11 ከተሞች ብቻ ሲተገበር የቆየው በተያዘው በጀት ዓመት በ83 ከተሞች ላይ የሚገኙ 513 ሺሕ 512 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም በመታቀፍ ድጋፍ የሚያገኙ ደግሞ 280 ሺሕ 930 ቤተሰቦች ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በየወሩ ለክፍያ ወጪ እንደሚደረግ በአምስት ዓመቱ መነሻ እቅድ ላይ መካተቱ ተጠቁሟል።

በጥቅሉ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በከተሞች ሰባት ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር የመነሻ እቅድ መያዙን ኤጀንሲው አመላክቷል።
በሌላ በኩል ኤጀንሲው የከተሞች ልማት ሴፍቲኔት ፕሮግራም በከተሞች የሚኖሩ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች በአካባቢ ልማት በማሰማራት እና የመሥራት አቅም የሌላቸውን በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረጉን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል። ባለፉት አራት ዓመታት በ11 ከተሞች ስድስት መቶ ሺሕ ዜጎችን (70% ሴቶች) ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ በአካባቢ ልማት በማሰማራት አራት መቶ ሺሕ (80.94%)፣ በቀጥታ ድጋፍ ዘጠኝ ሺሕ (15.42%) እና ስድስት ሺሕ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በድምሩ ከአምሰት መቶ ሺሕ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ኤጀንሲው አስታውቋል። ከተጠቃሚዎች ውስጥ የሴቶች ድርሻ 68 በመቶ ነው ተብሏል።

የኤጀንሲው ኃላፊነት ሥራ አጥ ዜጎችን በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ በከተማ ሥራ ፈጠራ ማሰማራት ሲሆን፣ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎችን በልማት በማሳተፍ እንዲሁም በቀጥታ ድጋፍ በማድረግ ኑሯቸውን እንዲደግፉ ማድረግ የዚህ ድርሻ አካል መሆኑንም አቦዘነች ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here