ባሳለፍነው ሠኔ ወር ላይ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሸገር ዳቦ፣ በአንዳንድ ነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ምርቱን በተገቢው ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ማድረስ አንዳልተቻለ ፋብሪካው ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ዳቦውን ለማከፋፈል በየሰፈሩ በተቀመጡ የአንበሳ አውቶብስ ሱቆች ውስጥ ዳቦ ቤት ያላቸው ነጋዴዎች በመምጣት እና ከሻጮች ጋር በመመሳጠር በብዛት ያላቸው ዳቦዎችን አትርፈው ለመሸጥ ይገዛሉ። አብዛኛው ኅብረተሰብም ከረጅም ሰዓት ሰልፍ በኋላ የዳቦው አቅርቦት ስለሚያልቅ ሳይገዛ የሚመለስበት ጊዜ ብዙ ነው ሲል ፋብሪካው አስታውቋል።
ፋብሪካው በኮሚሽን ሥራዎች አለመጠናቀቅ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሰዓት ከ30 ሺሕ እስከ 35 ሺሕ ዳቦ እንዲሁም በቀን 7 መቶ 71 ሺሕ ዳቦ በማምረት ለኢንተርፕራይዞች እያከፋፈለ ይገኛል። በዚህም ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ምርት እያመረተ ቢሆንም ‹በአንዳንድ ስግብግብ እና አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ትርፍ አጋባሽነት› ምክንያት የዳቦ አቅርቦቱን በተሳካ ሁኔታ ወደ ኅብረተሰቡ ለማድረስ ተግዳሮት እንደገጠመው የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ኃይሉ ቡልቡላ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹እውነት ሁላችንም ለማኅበረሰቡ ነው ወይ የምንሠራው ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይገባናል።›› የሚሉት ኃይሉ፣ በእነርሱ በኩል በአንድ ዳቦ እስከ 20 ሳንቲም እየከሰሩ እንደሚሸጡ አስታውቀዋል። ‹‹እኛ ይኽን እያደረግን ሳለ ደግሞ ገበያ ውስጥ እስከ ሦስት ብር እየተሸጠ ነው። ይህ የስግብግበ ነጋዴዎች ከፍተኛ ትርፍን የማጋበስ ፍላጎት ማኅበረሰቡን እየጎዳ ነው። እኛም ከስረን ተጠቃሚውም በተባለለት ልክ ሳይጠቀም እየቀረ ነው።›› ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
ስለሆነም መንግሥት እና ኅብረተሰቡ በጋራ በመሆን ይህን ጉዳይ መታገል አለበት ያሉ ሲሆን፣ ፋብሪካው ማኅበረሰቡን ለመጥቀም በተነሳበት ሰዓት በመካከል የሚገቡ አካላት አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ሲሉ ኃይሉ አሳስበዋል።
የፋብሪካው ሥራ ዳቦውን አምርቶ ለኢንተርፕራይዞች ማከፋፈል እንደሆነ የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀመር የኅብረተሰቡን ችግርን እንደሚፈታ ትልቅ እምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ነገር ግን ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጥናት ማድረግ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ይህንን ዳቦ በሙሉ አቅም ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራው ሥራ የፋብሪካው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡም ሆነ መንግሥት በዚህ አገልግሎት ላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት እንደተጠበቀው እየሠሩ መሆኑን መከታተል እና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
‹‹በእኛ በኩል ግን የአቅርቦት ሥራው በሚቻለው እና በሚፈለገው መጠን እንዲከናወን ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ለአከፋፋይ ኢንተርፕራይዞች የማከፋፈል ሥራን እየሠራን እንገኛለን።›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ‹‹እኛ ይህን ጉዳይ እናጣራ ብንል እንኳን በኪሳራ እያመረትን የምንገኝ ከመሆኑ አንፃር አቅሙ የለንም። የሚያጣራ እና የሚመረምር አካል መመደብ አንችልም።›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የፋብሪካውን የምርታማነት አቅም ለማስተካከል እና አቅርቦቱን በማሳለጥ ሥራ ላይ በስፋት ተጠምደን ስለምንገኝ ጊዜውም የለንም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ሚድያው፣ የመንግሥት አካላትም ሆነ ይመለከተኛል የሚል አካል ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ በመግባት በትብብር መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲስ ማለዳ በዚህ ጉዳይ ላይ ክትትል እና ቁጥጥር የሚያደርገው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል ሙኤሳን ስለጉዳዩ ጠይቃ ነበር። ሆኖም ኃላፊው ስለጉዳዩ ምንም እንደማያውቁና ምንም ዓይነት ጥቆማም እንዳልደረሳቸው ገልፀዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ይሄንን ሥራ የሚሠሩ ኅብረተሰቡን ለማገልገል እና ለራሳቸውም የሥራ እድልን ለመፍጠር በተለያዩ መንገዶች በየወረዳው ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ ግለሰቦች ናቸው። ከዚህ ከታሰበለት ዓላማ ባለፈ ግን የሸገር ዳቦ ላይ ዋጋ ጨምረው በሚሸጡ አካላት ካሉ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀው 8588 ነፃ የስልክ መስመር ላይ በሚደርሰን ጥቆማ መሰረት ቦታና አካባቢውን አጣርተን እንደዚህ የሚያደርገው አካል ላይ ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ሸገር የዳቦ ፋብሪካ በሰአት 80 ሺሕ፣ በቀንም በሦስት ፈረቃ ኹለት ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም እንዳለው መገለጹ ይታወሳል።
ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012



