‹‹ ኢንተርኔት ሊቋረጥ እንደሚችል ጠብቀን ነበር››

0
936

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ

በ2012 በጀት ዓመት ‹‹የኢንተርኔት መዘጋት እና አልፎ አልፎ መስተጓጎል ሊኖር እንደሚችል ጠብቀን ነበር›› ሲሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናገሩ።

2012 አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት ዓመት በመሆኑና ካለፈው ተመሳሳይ የምርጫ ጊዜ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ጉዳዮችን በተሞክሮ በመውሰድ፣ የኢንተርኔት መዘጋት ሊያጋጥም ይችላል ሲል ተቋሙ በእቅዱ አካቶ እንደነበር ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የ2012 በጀት ዓመት የተቋሙን አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የተናገሩት።

እንደ ፍሬሕይወት ገለፃ ምርጫን ተከትሎ አንዳንድ ኹከቶች እና አለመረጋጋቶች ምን አልባት ቢያጋጥም ብለው ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ መዝነዋል። በአንጻሩ እንደስጋታቸው ባይሆን ደግሞ ተቋሙ ምን ያህል ሊያተርፍ ይችላል የሚለው ቀድሞ የተቀመጠ ነው ብለዋል። በመሆኑም ያጋጠመው የኢንተርኔት መቋረጥ በተቋሙ ላይ ተፅዕኖው የጎላ እንዳልነበር አስታውቀዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይህን ይበሉ እንጂ፣ ባለፈው የበጀት ዓመት ከተፈጠሩ ኢንተርኔት መቆራረጥ እና አጠቃላይ ኹከቱን ተከትሎ የአገልግሎት መስተጓጎል ተቋሙ ያጣው ምን ያህል እንደሆነ ተደጋጋሚ ጥያቄ ተነስቶላቸዋል። በምላሻቸውም ‹‹የልማት ተቋማት ሕዝብን ለመበተን አይውልም›› ያሉ ሲሆን፣ ይሄንንም ተቋሙ እንደ ኪሳራ አያየውም ብለዋል። ‹‹በእቅዳችን ያስቀመጥነው በመሆኑ እንደ ኪሳራ አናየውም። ለአገር ጥቅም ሲባል በመሆኑም›› በማለትም ምላሽ ሰጥተዋል።

ይሁን እና ኢትዮ ቴሌኮችም አስከ አሁን አስመዝግቦ ከሚያውቀው የላቀ ትርፍ ማግኘቱ ተነስቷል። ኢትዮ ቴሌኮም ከባለፈው በጀት ዓመት ያልተጣራ 47 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንም አስታወቋል። ከትርፉ ላይም 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ግብር የተከፈለ መሆኑን እና ተቋሙ 318 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈሉን ጠቁመዋል። በዚህም ተቋሙ ላይ ካለው ዕዳ 75 በመቶ የሚሆነውን እንዳቃለለ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።

የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች ደግሞ 147 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተመላክቷል። ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳነሱት ከሆነ፣ የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ31 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ አለው። በአጠቃላይ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 46 ነጥብ 2 ሚሊዮን መድረሱም የተነገረ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የሞባይል ድምፅ ደምበኞች ብዛት 44 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ 23 ነጥብ 8 ሚሊዮን፣ ብሮድባንድ ደንበኞች ብዛት 212 ሺሕ መድረሱን ተጠቅሷል። በዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ይህ ለውጥ የመጣበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችል ቀላል አሰራር ያለመኖሩን አንስተዋል። በአንጻሩ አሁን ላይ ግን እነዛ ቅድመ መስፈርቶች በማንሳት ዘዴውን ማቅለል ስለተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም የመደበኛ ስልክ 980 ሺሕ ደንበኞች አሉት ተብሏል።

ለማኅበራዊ ኃላፊነት 1 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር ወጪ ያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከዚህ ውስጥ 792 ሚሊዮን ብር ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ የመከላከያና የመቆጣጠር ሥራ በአይነት እንዲሁም በገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ነው ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም 36 ሺሕ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ለደንበኞች የሚያደርሱ ደግሞ 249 ሺሕ አከፋፋዮች እና 624 አጋሮች እንዳሉትም አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here