አርቲስት ሀጫሉን በመግደል ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ወንጀሉን መፈፀሙን አመነ

0
379

በአርቲስትሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ ጥይት ተኩሶ በመግደል ወንጀል የተጠረጠረው ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል አረጋገጠ። ተጠርጣሪው “ይህንን ተልእኮ የሰጡኝ ሰዎች ድርጊቱን መፈፀምህን በምስጢር የማትይዝ ከሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ጉዳት እናደርሳለን” በማለት እንዳስጠነቀቁት ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የአራዳ ምድብ፣ አንደኛ ወንጀል ችሎት ተናግሯል።
በዚህም “ለቤተሰቦቼ በቂ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና የኔም ጉዳይ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። “የፀሀይ ብርሀን አግኝቼ አላውቅም፣ ካቴና ከእጄ አልወለቀም፣ ክስ እስከሚመሰረትብኝ እንኳን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር እንድቀላቀል ይደረግልኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አቅርቧል።
ተጠርጣሪው ባለፈው የጊዜ ቀጠሮ በዚሁ ችሎት ቀርቦ “እራሴን እንዳጠፋ ይፈቀድልኝ” ማለቱን ችሎቱ አስታውሷል። በዚያው ቀጠሮው መርማሪ ፖሊስ ካቴናው ከእጁ የማይወልቀው ተጠርጣሪው እራሱን እንዳያጠፋ ለመከላከል መሆኑንም ችሎቱ ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው የካቴናውን ጉዳይ ዳግም በማንሳቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚመለከተው የሥራ ኃላፊ በቀጣይ ቀጠሮው ስለሁኔታው ያስረዳ ብሏል ችሎቱ።
ፖሊስ ባለፈው የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ያከናወነውን የምርመራ ሥራ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በቀጣይ በተለይም በቁጥጥር ስር ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጀርባ ድርጊቱን ያቀነባበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ለማደራጀት ከጠየቀው 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ 11 ቀን ፈቅዷል።
ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለነሐሴ 12 ቀን 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here