ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የሚቆጣጠር ሶፍት ዌር ይፋ ሆነ

0
364

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የሚቆጣጠር እና የሚያረጋግጥ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመንግሥት የሚያገኙትን አገልግሎት የሚያፋጥን ሶፍትዌር በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጎልብቶ ለከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ መሰጠቱ ተገለጸ።

ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለኤጀንሲው በዕርዳታ መልክ የሰጠው ሶፍትዌር፣ በዋናነት ተግባሩ ሥራን ከማቅለል ባለፈ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች በቀላሉ የሚቆጣጠር እንደሆነ ታውቋል።

አዲሱን ሶፍትዌር አልምቶ ለማስረከብ አንድ ዓመት እንደፈጀበት ሚኒስቴሩ ያስታወቀ ሲሆን፤ አተገባበሩም ቀላል እና ለአጠቃቀም ውስብስብ እንዳይሆን ተደርጎ መዘጋጀቱንም ተቋሙ ለአዲስ ማለዳ አሰታውቋል።

የሶፍትዌሩ መሠራት ጠቀሜታው የተዘረዘረ ሲሆን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትራንስፖርት አገልግሎት ወጪ ሳይኖርባቸው በአጭር ጊዜና በቀላሉ የዕውቅና ፈቃድ ለማግኘት፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅርንጫፍ ማስፋፊያ ለማድረግ እንዲሁም የፕሮግራም ማስፋፊያዎችን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎቶች ጊዜን እና ጉልበትን በቆጠበ መልኩ እንዲያገኙ ማድረግ ያስችላል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት እየሠሩ እንደሆነና እንዳልሆነ ቁጥጥር ለማድረግ ዋነኛ አጋዥ መሣርያም ይሆናል ሲሉ የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ማርታ አዳሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተያያዘም በእያንዳንዱ ተቋም የተመዘገቡ ተማሪዎችን ከመቆጣጠር ጀምሮ በተለይም በየትምህርት ዘመኑ ያገኘውን ውጤት ከመመዝገብ ጀምሮ ያለውን እንቅስቃሴም የሚመዘግብ እንደሚሆን ተነግሮለታል። ‹‹ማንኛውም የግል እና የመንግሥት ተቋም ማስመዝገብ የሚፈልግና በትምህርት ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ሥርዓቱን መጠቀም ይችላል›› የተባለ ሲሆን፣ በዚህም ብለሹ አሰራርን በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል መመላከቱን ነው ኃላፊዋ የጠቀሱት።

በሂደቱ ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ ለመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ ደኅንነት ወይም እራሱን የመጠበቂያ ሥርዓት ይኖረዋል ተብሏል። ለዚህም በቀላሉ መገመት የማይችል የይለፍ ቃል መጠቀምን የሚያስገድድ መሆኑን የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነቷ፣ ማንም የድረ ገጹን ምንጭ ኮድ ማየት እንደማይችል እና ድረ ገጹ በተጠቃሚው ከተከፈተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዲያበቃና በድጋሚ ፈቃድ እንዲሰጠው የሚያደርግ ክፍል ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

አግባብነት ያላቸው ወይም የተፈቀደላቸው ተጠቃሚዎች ብቻ በድረ ገጹ እንዲጠቀሙ ይደረጋልም የተባለ ሲሆን፤ የኔትወርክ መጨናነቅን ለመቀነስ ታስቦም ተጠቃሚው ሰው ወይም ሰው ሠራሽ መሆኑን የሚያረጋግጥ የሮቦት ፕሮግራም እንደሚኖረውም ታውቋል።

ከዛም በተጨማሪ በስርዓቱ ውስጥ የገቡ አላስፈላጊ ነገሮችን የማጣራት አቅም እንዲኖረው ይደረጋል። ተገልጋዮች ያላቸውን መብት መሠረት በማድረግ ለእያንዳንዱ በስርዓቱ የሚሰጠውን ተግባር ሲመለከቱ፣ ሲያከናውኑና ሲጠቀሙ ፈቃድ እና ማረጋገጫ መስጠት ይችላል።

የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ አጠቃቀም፤ ያለምንም ችግር ቀላል በሆነ መንገድ መጠቀም እንዲቻል ወይንም ዘለግ ላለ ጊዜ ሥልጠና የማያስፈልገው ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑም ተጠቁሟል። የመረጃ ስርዓቱ ሥራ ላይ እያለ የተለያዩ ቴክኒካዊ ችግሮች ቢከሰቱ ስርአቱ በነበረበት ሁኔታ ይቆያል፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ማንኛውም ሞዱሎቹ በቀላሉ ለመጨመር የሚስችሉ MVC ( የዳታ ቤዝ ፍሰት መቆጣጠሪያ) ስላለው ነውም ተብሏል።

በተጓዳኝ ኮዶችን የያዙ ሁሉም ፋይሎች እያንዳንዱን የኮድ መስመር በቀላሉ መገንዘብ የሚያስችል አስተያየት እና ተለዋዋጭ ሽሞች በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል ነው። የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችልበት ቦታ ላራቭል አቀናባሪ እና በእሱ ላይ በተጫነ My SQL (data base programming language) ዳታቤዝ በሚይዝ በማንኛውም ዊንዶው ላይ ሊሸራ ይችላል።

አዲስ የተሠራው ይህ ሶፍትዌር ሥራውን የሚጀምረው ከመጪው መስከረም 2013 በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ እና ለሚመረቁ ተማሪዎች እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here