በ2013 በሦስት መቶ ሺሕ ሔክታር በመስኖ ስንዴ ለማልማት ዕቅድ ተይዟል

0
1558

የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር በቀጣይ 2013 በጀት ዓመት 300 ሺሕ ሔክታር መሬት በቆላማ ቦታዎች የመስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት መደረጉን አስታወቀ። በቆላማ ቦታዎች ላይ የሚለማው የመስኖ ስንዴ ግብርና ልማት ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ መልማት እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

ይህ የመስኖ ስንዴ ግብርና ልማት ከሚከናወንባቸው ቦታዎች ውስጥ አፋር ክልል፣ ሶማሌ ክልል፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልልና ኦሮሚያ ክልል መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበራ ለማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ለቆላ ስንዴ መስኖ ልማት በተለዩ ክልሎች ላይ በቂ መሬት ተዘጋጅቶ አስፈላጊው ቅድመ ዘግጅት እየተደረገ መሆኑንም የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የመስኖ ስንዴ ልማት ሥራው ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ስለሚጀመር በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ ሲሆን፣ ከቅድመ ዘግጅቶቹ መካከል የመሬት ልየታ ሥራ፣ አስፈላጊ ሥልጠና የመስጠት ሥራና ለቆላማ ቦታዎች የመስኖ ስንዴ ልማት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነቱ ተናግረዋል።

በቆላማ ቦታዎች ላይ ስንዴን በመስኖ የማልማት ሥራ ለመሥራት በቂ የመሬት ግብዓት እንዳለ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ሥራውን ወደፊትም በትኩረት እንደሚሠራበት አመላክተዋል። የመስኖ ስንዴ ከሚለማባቸው ቦታዎች ውስጥ የስኳር ፋብሪካ መሬቶች በብዛት በመስኖ ስንዴ እንደሚለሙ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካትና ከውጭ የስንዴ ምርት ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል። ለዚህም አንደኛው ከዚህ በፊት የስንዴ ልማት የማይለማባቸውን ቆላማ ቦታዎች በመስኖ ስንዴ ማልማት አንዱ መሆኑ ተገልጿል።

ስንዴን በቆላማ ቦታዎች በመስኖ የማልማት ሥራ ባለፈው 2012 በጀት ዓመት በአፋርና በሶማሌ ክልል በማስጀመር 20 ሺሕ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። በቀጣይ 2013 የሚለማው የመስኖ ስንዴ ልማት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ220 ሺሕ ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ያሳያል።
ባለፈው ዓመት የመስኖ ስንዴ ግብርና ልማት ከተሞከረባቸው ቆላማ ቦታዎች ውስጥ በአፋር ክልል ውጤታማ መሆኑ እንደተረጋገጠ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። በዚህም አፋር ክልል ከዚህ ቀደም ይታወቅበት የነበረውና ይተዳደር የነበረው በእንስሳ እርባታ ቢሆንም ከዚህ በኋላ የመስኖ ልማትን በመጠቀም በቆላማ ቦታዎች ስንዴ ማምረት እንደሚቻል የተረጋገጠበትና ወደፊትም ለመሥራት ትልቅ ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

የቆላማ ቦታዎች የመስኖ ስንዴ ግብርና ልማት ከባለፈው ዓመት በተለየ ሁኔታ ከፍ ያለበትና በትኩረት እየተሠራ ያለበት ምክንያት የመጀመሪያው ባለፈው ዓመት የተገኘው የሙከራ ውጤት አመርቂ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ኮቪድ-19 በመኸር ምርት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል በሚል የተሻለ ምርት ለማምረት አቅጣጫ በመቀመጡ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ኮቪድ-19 በዓለም ላይ ከተከሰተ ቀን ጀምሮ በግብርናው ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ቀላል የማይባል በመሆኑ ኢትዮጵያም በዓለም ግብርና ላይ ተጽዕኖውን ሊያሳርፍ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ባገናዘበ ሁኔታ ተጽኖዎችን ለመቋቋም በግብርናው ዘርፍ በትኩረት እየሠራች ነው። ለዚህም ማሳያ በዘንድሮው መኸር ወቅት ከዚህ በፊት ታርሰው የማያውቁ መሬቶች ጾም እንዳያድሩ በከፍተኛ ትኩረት አሁንም ድረስ እየለሙ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here