በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች በ20 ሺሕ ጨመረ

0
605

በየቀኑ 30 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጣሉ
በኢትዮጵያ በ2012 በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከባለፈው 2011 ጋር ሲነፃፀር የኤች አይ ቪ ስርጭት በ20 ሺሕ ከፍ በማለት 2011 ከነበረው 649 ሺሕ ዓመታዊ ስርጭት በ2012 ወደ 669 ሺሕ ከፍ ማለቱን የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የስርጭቱ መጨመር ምክንያትም በኅብረተሰቡ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለኤች አይቪ የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው። በተጨማሪም በ2012 ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 በመከሰቱ የምርመራ ሥራዎች መቀዛቀዝ ሌላው ምክንያት እንደሆነ የፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት የኮምዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዳንኤል በትረ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ዳንኤል ገለጻ፣ የቫይረሱ ስርጭት ከሦስት ክልሎች (ከሶማሌ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች) ውጭ በሚገኙ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአሁኑ ወቅት በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚገኝ አመላክተዋል። የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ከተከሰተባቸው ክልሎች ውስጥ ጋምቤላ ክልል 4 ነጥብ 8 በመቶ በመሆን ቀዳሚውን ቦታ ሲይዝ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ሀረር፣ አፋር፣ ትግራይ፣ አማራና ቤንሻንጉል ጉምዝ በቅደም ተከተል ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በአንፃሩ በአሁኑ ጊዜ የቫይረሱ ስርጭት ከወረርሽኝ በታች ማለትም ከ 1 በመቶ በታች የሆነባቸው ክልሎች ሶማሌ 0.1 በመቶ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 0.4 በመቶ እና ኦሮሚያ 0.7 በመቶ በመሆን የዝቅተኛ ስርጭት ደረጃን ይዘዋል።

እንደ አገር በተፈጠረው የመዘናጋትና ትኩረት የመስጠት ችግር በኢትዮጵያ አሁን ላይ ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝባቸው ከ669 ሺሕ በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ የሚውቅት ሰዎች ከ500 ሺሕ አይበልጡም። ቀሪዎቹ 200 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ሳያውቁ የሚኖሩ ናቸው ተብሏል።
አዲስ ማለዳ ከኹለት ወራት በፊት በአገሪቱ ቫይረሱ በደማቸው እያለ ተመርምረው እራሳቸውን የማያውቁ ተጠቂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ከጽሕፈት ቤቱ አረጋግጣ መዘገቧ ይታወሳል።

በተለይም ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ወር ወዲህ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይደረግ የነበረው የኤች አይ ቪ ምርምራ በአንፃሩ መቀነሱ ለስርጭቱ ማሻቀብ ስጋት መሆኑም ተጠቁሟል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያደርጉት የነበረው በፍቃደኝነት የሚከናወን የኤች አይ ቪ ምርመራ ሙሉ በሙሉ መቋረጡንም ጽሕፈት ቤቱ ጠቁሟል።

እንዲሁም በቫይረሱ የተጠቁና መድኃኒት በመውሰድ ላይ የሚገኙ ሰዎች ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ በአንዳንድ አጋጣሚዎች መድኃኒቱን የማቋረጥ አዝማሚያ እንደታየባቸው ተመላክቷል።

ለዚህም እንደ ምክንያት የተቀመጠው በአንዳንድ የመንግሥት ጤና ተቋማት ኮቪድ-19 መከሰቱን ምክንያት በማድረግ ሌሎች በሽታዎችን ማከምና ክትትል ማድረግ መቀነሳቸውና መድኃኒት ተጠቃሚ ግለሰቦች ኮቪድ-19ን በመፍራት ወደ ጤና ተቋም በማቅናት መድኃኒት መውሰድ አለመቻላቸው ነው ተብሏል።

የቫይረሱ ስርጭት እንደ አገር ወረርሽኝ ከሚባልበት ደረጃ በታች (0.9 በመቶ) ይሁን እንጂ፣ በአብዛኛዎቹ ክልሎች የአለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው የወረርሽኝ እርከን (1 በመቶ) በላይ መሆኑ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ ዳንኤል አክለው ተናግረዋል። አያይዘውም በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ቫይረሱ ወደ ቀድሞው ስርጭት እንዳይመለስ ያሰጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአማካኝ በቀን ከ40 በላይ ሰዎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደሚጠቁና ከ30 በላይ ሰዎች በቀን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የጠቆሙት ዳንኤል፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ ኮቪድ 19 ካስደነገጠን በላይ ሊያስደነግጠን የሚገባ መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here