ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች በመንግስት ኃላፊዎች ወደ ቤታችሁ ካልተመለሳችሁ እርዳታ አታገኙም የሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ተገቢ አለመሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ

0
599

 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተከሰተውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ ላይ  ምርመራ ማድረግ መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ከ40 በላይ ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ የምርመራ ቡድኖችን በማሰማራት ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ምስክሮችን እና የመንግስት አካላትን በማነጋገር መረጃ ለማሰባሰብ እና አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

 

ሰብዓዊ እርዳታ፣ ድጋፍ እና የተፈናቀሉ ተጎጂዎች ሁኔታ የተመለከተው ኮሚሽኑ ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ የተቻለ መሆኑን በማሳወቅ በተለይም የመኖሪያ ቤታቸው እና ንብረታቸው የወደመባቸው ተጎጂዎች አሁንም በሰው ቤት፣ በኃይማኖት ተቋማት እና በሌሎች ስፍራዎች  ተጠልለው የሚገኙ ቢሆንም እነዚህን ዜጎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

 

በሻሸመኔ እና አጋርፋ አካባቢ በአብያተክርስትያናት እና ሌሎች ቦታዎች የተጠለሉ ሰዎችን ለደህንነታቸው ማረጋገጫ ባልተሰጠበት ሁኔታ የመንግስት ኃላፊዎች ወደ ቤታችሁ ካልተመለሳችሁ እርዳታ አታገኙም የሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ  ማስቀመጣቸው ተገቢ አለመሆኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል።

 

ኮሚሽኑ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት የሚረዳ ቢሆንም መንግስት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች አፋጣኝ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበትና በተለይም አሁን ያለንበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የክረምት ወቅት ስለሆነ ተጎጂዎች ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይጋለጡ ማድረግ  ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል።

 

 

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here