የአፋር ክልል የ2013 በጀት 7 ቢሊዮን አፀደቀ

0
735

የአፋር ብሄራዊ ከልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስኛ ዓመት የስራ ዘመን አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2013 ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀትና የተለያዩ ሹመቶችን አጸደቀ። የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ሃሰን የክልሉን የ2012 የስራ አፈጻጸምና ተያያዥ ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ በጀቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። “በጀቱ ከ2012 በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው” ብለዋል ።

የበጀት ምንጩም ከፌዴራል መንግስት ግምጃ ቤት፣ ክልሉ ገቢ፣ ከውጭ እርዳታ የሚሸፈን መሆኑን አብራርተዋል ። በጀቱ በዋናነት በክልሉ የድርቅ ተጋላጭነት ለሚቀንሱ የማህበራዊና የኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶች ማስፋፋትና ለልማት ስራዎች ማኪያሄጃ የሚውል መሆኑን አመልክተዋል ።

በክልሉ በ2013 በጀት ዓመት ለተለያዩ የልማት ስራዎች ማስፈጻሚያ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት ተደርጎ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል:: የምክር ቤቱ አባላት በጀቱ ከብክነት በጸዳ መልኩ የህብረተሰቡን ችግር ለሚፈቱ ስራዎች አግባብ ባለው መልኩ እንዲውል አሳስበዋል ።

የክልሉ ርዕሰመስዳድር አወል አርባ ወቅታዊ ሀገራዊ የለውጥ ጅምሮችን ጫፍ ለማድረስ የተሻለ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ያላቸው አመራሮች ክፍተት በታየባቸው ቦታዎች የአስፈጻሚ አካላት መተካትና ሸግሽግ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በርዕሰ መሰተዳድሩ የቀረበውን የካቢኔ ሹመት በአብላጫ ድምጽ አድቋዋል። በዚህም መሰረት ኢለማ አቡበከር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ውሃ ሃብት ቢሮ ኃላፊ፣ መሃመድ ጠይብ የጤና ቢሮ ኃላፊ፣ አህመድ መሃመድ ቦዳ የትምህርት ቢሮ፣ ጠሐ አህመድ የመንግድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ ኢብራሂም ሁመድ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ መሀመድ ኡዳ የገጠር መሬት አስተዳደርና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ፣ መሃመድ አሊ የኪል በቲ ረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አህመድ ኢብራሂም የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here