የለማ መገርሳ ከፍታና ዝቅታ

0
691

ሰሞኑን በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ምክር ቤት እና ከሥራ አስፈጻሚ አባልነት ለጊዜው የመታገዳቸው ውሳኔ ይገኝበታል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ከፌደሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸውም ተሰምቷል። በርግጥ እገዳውና ስንብቱ ለማን ብቻ ሳይሆኑ የቀድሞዋ የሻሸመኔ ከንቲባ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ አማካሪ ጠይባ ሐሰንን እና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የካቢኔ አባል በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩትን ሚሊኬሳ ሚደጋን (ዶ/ር) ያካትታል።

ይባስ ብሎ ደግሞ በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ለማ የቁም እስረኛ እንደተደረጉ አዲስ ስታንዳርድ የተባለው የበይነ መረብ የእንግሊዝኛ መጽሔት የታመኑ ምንጮች ሹክ ብለውኛል ብሎ ዘግቧል። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል አደም ሞሐመድ በቀጥታ ለማን ሌላ ውሳኔ እስኪሰጣቸው ድረስ ከቤት ወጥተው መንቀሳቀስ እንደማይቻሉ እንደነገሯቸው ጨምሮ ዘግቧል። ይሁንና ከፓርቲው እገዳ ውጪ ሌሎች ተወሰዱ የተባሉት እርምጃዎች ትክክል ስለመሆን አለመሆናቸው በርግጠኝነት መናገር እንዳማይቻል ታዛቢዎች ይናገራሉ።

የለማ ከፓርቲ ምክር ቤት እንዲሁም ሥራ አስፈፃሚ አባልነት መታገድ ሰበብ ተብሎ የተጠቀሰው በተደጋጋሚ በፓርቲው ጥሪ ሲደረግላቸው ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታቸው ነው ተብሏል። ይህም በፓርቲው አሠራር እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንድ የአመራር አባል የልዩነት ሐሳብ እንኳን ቢኖረው በመድረኮች ላይ ተገኝቶ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሐሳቡን ማንጸባረቅ ሲገባው ከመድረኮቹ በተደጋጋሚ ራሱን ማግለሉ ተቀባይነት እንደሌለው ተጠቅሷል። ይሁንና ፓርቲው፥ ለማ ጥፋቱታቸውን እስካመኑና ለመታረም እስከተዘጋጁ ድርስ ወደ ትግሉ ለመመስስ በሩ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተዘጋባቸውም አስታውቋል።

ኢሕአዴግ ከስሞ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት ለመሸጋገር በመንደርደር ላይ በነበረበት እንዲሁም የፓርቲው ፍልስፍና ‘መደመር’ መሆኑ በሚነገርበት ወቅት፥ ለማ አሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ላይ ብቅ ብለው ውህደቱንም ሆነ የፓርቲውን ፍልስፍና እንደማይቀበሉ አስታወቁ። ይህም ለማ ከቅርብ አጋራቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ያላቸውን ልዩነት ማስፋቱ ይታመናል። በተጨማሪም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን እንመልሳልን ብለን በኦዲፒ ሥም ቃል በመግባታችን ውህደቱን ከፈጸመን ቃላችንን እንዳጠፍን ይቆጠራል ሲሉ መከራከሪያ ነጥብ ማቅረባቸውም ይታወሳል።

ለማ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በነበሩበት ወቅት በመንግሥት ደረጃ የመጣውን ለውጥ በግንባር ቀደምትነት ካስተባበሩትና ከመሩት መካከል ሥማቸው ተጠቃሽ ነው። ለዚህም ማረጋገጫ በለውጡ ሰሞን ‘ቲም ለማ’ ወይም ‘የገዱና ለማ ጥምረት’ የሚሉ ቅጽሎችን በብዛት መስማት የተለመደ ነበር። ፊተኞች ኋለኞች ሆነና ነገሩ፥ በብልጽግና ፓርቲ በተቃርኖ በመቆም፤ ነገር ግን ድምጻቸውን እምብዛም ሳያሰሙ ቀጥለውበታል። በባህሪያቸው ጭምትነት እንደሚያጠቃቸው ለማን በቅርብ የሚያውቋቸው ይገልጻሉ።

የመንግሥት ሥራን ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው የደህንነት ማሰልጠኛ የስድስት ወር ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በአዲስ አበባ የውስጥ ደኅንነት መምሪያ አኀዱ ብለው የጀመሩት ለማ፥ ከዚያም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ከፌደራል ወደ ኦሮሚያ በመዘዋወር የክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ፣ ፖሊስ ኮሚሽነር የኋላ ኋላም የፀጥታና ደህንነት ቢሮ ኀላፊ በመሆን አገልግለዋል። ሌሎች ቢሮዎችንም በኀላፊነት ከማገልገል እስከ ርዕሰ መስተዳድር የሥልጣን ማማ ተቆናጥጠው ነበር። አሁንም የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፤ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እስካልተገደዱ ድረስ።

የሆነው ሆኖ የለማ ከፍታና ዝቅታ የት ላይ መቋጫ ያገኛል የሚለውን በርግጠኝት መናገር ባይቻልም መላምቶች ግን ከግራም ከቀኝም እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፤ ዘብጥያ መውረድ፣ በኦሮሚያ ክልል ተገዳዳሪ ፓርቲ ማቋቋም፣ ወደ ውጪ መሰደድ ወይም አፍቸውን በመለጎም ቀሪ ሕይወታቸውን በዝምታ ማሳለፍ። ለሁሉም ጊዜ ሚዛን ለእንቆቅልሹ መልስ ይሰጣል!

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here