‹‹መጣና በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ
ቡሄ መጣ በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ
ሆያ…. ሆዬ….!ሆ….!
እዛ ማዶ ጭስ ይጨሳል
አጋፋሪ ይደግሳል፤
ያቺን ድግስ ውጬ ውጬ
ከድንክ አልጋ ተገልብጬ፤
ያቺ ድንክ አልጋ አመለኛ
ያለ አንድ ሰው አታስተኛ፤
ሆይሻ…. ሎሚሻ መጣንልሻ፤…››
እነዚህን ስንኞች በልጆች የዝማሬ ቅላጼ፣ አብሮ በሚሰማ የቆርኪዎች መንኳኳትና መሬትን በሚቀጠቅጡ ዱላዎች ታጅቦ በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ይሰማል። ከክረምቱ መብረቅ ባሻገር በዚህ ሰሞን የተለያዩ ከተሞችም በጅራፍ ድምጾች ይታጀባሉ።
የደብረ ታቦር በዓል በመላው ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ባሉበት ሁሉ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ ሃይማኖታዊ መነሻ ያለው ሲሆን፣ በተጓዳኝ ትውፊታዊና ባህላዊ ስርዓቶችን አክሎ ዘመናትን የተሻገረ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንም በድምቀት ከምታከብራቸው በዓላት መካከል ሲገኝ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
ለወትሮው የዚህ በዓል መዳረሻ ላይ ሕጻናት ጅራፍ በመግመድ በየሜዳው እና ገደላ ገደሉ ያጮኻሉ። ለችቦ መሥሪያ የሚሆኑ እንጨቶችን ይሰበስባሉ፤ እንዲሁም የበዓሉ እለት ለሚያከናውኑት የቡሄ ጭፈራ የሚሆን ዱላ እና መሰል የጭፈራው አድማቂ ቁሳቁሶችን ሲያዘጋጁ ይሰነብታሉ።
እናቶችም ለበዓሉ የሚሆን ሙልሙልን ለማዘጋጀት የሚውለውን ስንዴ ያጥባሉ፣ ይፈትጋሉ ይፈጫሉ። ከበዓሉ ዋዜማ እለት ጀምሮም እስከ በዓሉ እለት ምሽት ድረስ ሕጻናት በየሰፈሩና በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ በሉ…ቡሄ መጣ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ….›› በማለት በጋራ ይዘምራሉ።
በዚህ ጊዜ እናቶች ለበዓሉ ያዘጋጁትን ሙልሙል ዳቦ እያነሱ ለሕጻናቱ ይሰጣሉ። ነገር ግን ይህ ሙልሙል የመስጠቱ ሥነስርዓት በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በከተማዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዘነጋ እና በገንዘብ እየተቀየረ መምጣቱን እያስተዋልን እንገኛለን።
ታዲያ ይሄ ታላቅ ሀይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ስርአትን አጋምዶ የያዘው የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል ከአራት ቀናት በኋላ የፊታችን ረቡዕ ነሐሴ 13 ቀን 2012 ይከበራል። ምንም እንኳ ከወራት በፊት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የበዓል አከባበር ሥነስርዓቱን እና ባህላዊ ድምቀቱን እንደሚያደበዝዘው ቢገመትም።
ደብረታቦር እና ቡሄ?
የደብረ ታቦር በዓል መሰረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሚያስረዱት። ደብረታቦር <የታቦር ተራራ> ማለት ሲሆን፣ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ደቀመዛሙርቱን ይዞ የወጣበትና በተራራው ጫፍ ላይም ብርሀነ መለኮቱ የተገለጠበት ነው።
ቡሄ ደግሞ ‹ብራ፣ ደማቅ፣ የተገለጠ› የሚል ትርጓሜን ሲይዝ በዓሉ በአገራችን የሚከበረው የክረምቱ የጨለማ ወራት አልፈው ሰማዩ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ ወደ መፀው ወቅት የሚገባበት፣ የብርሀን ወገግታ የሚታይበት ወቅት መሆኑን ተከትሎ የተሰጠው ሥያሜ እንደሆነ የእምነቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ።
ስለ ደብረታቦር (ቡሄ) በዓል ታሪካዊ አጀማመር፣ የበዓሉ አሰያየም እንዲሁም አጠቃላይ የበዓሉ አከባበርን በተመለከተ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ሊያደረጉ የፈቀዱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መምህር መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ ስለ በዓሉ ታሪካዊ አመጣጥና አሰያየም እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።
‹‹ይሄ በዓል እንደ ሀይማኖት ዓለም ዐቀፋዊ ትርጓሜ ቢሰጠውም፤ በባህላዊ ደረጃ ግን ኢትዮጵያዊ ይዘት ያለው በዓል ነው። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የቆመችባቸው ሦስት ምሶሶዎች አሉ። እነሱም ዶግማ፣ ቀኖና እና ባህል ናቸው።›› በማለት ያስረዳሉ።
እንደ መጋቢ ሐዲስ ገለጻ በቤተክርስትያኒቱ አስተምህሮ መሠረት እነዚህ ሦስት ምሰሶዎች ካልተጋመዱ እምነት የሚለውን ትርጓሜ ሊሰጡ አይችሉም። ስለዚህም ደብረ ታቦር የበዓሉ ዶግማዊ መጠሪያ ሲሆን፣ ቡሄ ደግሞ ከባህላዊ ይዘት እና ትውፊቱ ጋር ተያይዞ የተሰጠው ሥያሜ ነው።
አክለውም አሉ፤ ‹‹ደብረ ታቦር የቦታ ሥም ነው። አንዳንድ በዓላት የበዓሉ መነሻ ድርጊት በተከናወነበት ቦታ መጠሪያ ሥም ይጠራሉ። ይህም ልማድ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተለመደ ነው። ስለዚህ ደብረ ታቦርም የክርስቶስ አምላክነት የተገለጠበት ቦታ ስለሆነ፤ መገለጡ ከተገለጠበት ቦታ ጋር ተያይዞ ደብረታቦር በመባል ለበዓሉም ስያሜ ተሰጥቶታል።›› ብለዋል።
ቡሄ ለሚለውም ቃል ትርጉሙን እንዲህ አብራርተዋል፤ ‹‹ቡሄ ማለት ደግሞ መላጣ፣ ገላጣ፣ ነጭ፣ በሀ ድንጋይ የሚል ትርጓሜ አለው። ይህም አንደኛ በደብረታቦር ተራራ የተገለጠውን ብርሃነ መለኮቱን ሲያመለክት በተጨማሪም የክረምቱ ዝናባማ ወቅት አልፎ የበጋው ወራት መምጣታቸውን ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት› እየተባለና ‹ቡሄ መጣ ያ መላጣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ› እየተባለ በዓሉን በማስመልከት ግጥም ይገጠማል።›› በማለት ስለበዓሉ ባህላዊ አሰያየም ያስረዳሉ።
የደብረ ታቦር በዓል በኢትዮጵያ
ቡሄ በሉ! ሆ!
ልጆች ሁሉ! ሆ!
የኛማ ጌታ፣ የዓለም ፈጣሪ
የሰላም አምላክ፣ ትሁት መኻሪ
ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሀን ለኛ በራልን….
ይህ ልዩ የሆነ ሀይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ይዘት ያለው የደብረ ታቦር በዓል በኢትዮጵያ መቼና እንዴት መከበር ተጀመረ ስትል አዲስ ማለዳ ለመጋቢ ሀዲስ ጥያቄዋን አቅርባ ነበር።
መጋቢ ሀዲስም ሲመልሱ ‹‹የአገራችን አብዛኞቹ በዓላት እጅግ በጣም ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው። ነገር ግን ለምሳሌ ከልደት በዓል ጋር ተያይዞ የገና ጨዋታ እንደሚታሰበው ሁሉ ችቦ የማብራት፣ ጅራፍ የማጮህ እና ሙልሙል ዳቦ የመጋገር መሰል ክንውኖች ኢትዮጵያዊ ባህል እና ትውፊትን ይዞ ከሚከናወነው ከቡሄ ወይንም ደብረታቦር በዓል ጋር በተገናኘ የሚከወኑ ስርአቶች ናቸው። ምስጢራዊ ትርጉሙ የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ተከትሎ የመጣ ቢሆንም አፈፃፀሙ ግን ኢትዮጵያዊ ስርዓትን የተከተለ በዓል ነው።›› ብለዋል።
ነገር ግን እስከ አሁን በዓሉ በዚህ ጊዜ ነው መከበር የተጀመረው የሚል ጥናታዊ መረጃ እንዳላገኙ ነው መጋቢ ሐዲስ የጠቀሱት። ‹‹ነገር ግን የደብረ ታቦር በዓል እንደ በዓል የእረኞች በዓል ነው። እንደ ሀይማኖት ደግሞ የተማሪዎች በዓል ነው።›› ሲሉ ያስረዳሉ።
እንዲህ ነው፤ የቆሎ ተማሪዎች የደብረታቦር በዓልን ከምዕመናን ለምነው የሚያገኙትን በማሰባሰብ እና ንፍሮ በመቀቀል፣ ዳቦ በመጋገርና ጠላ በመጥመቅ ነው የሚያከብሩት። በዓሉም በደብረታቦር ተራራ ላይ የክርስቶስ በብርሃነ መለኮትነት መገለጥ፤ በወቅቱ ከክርስቶስ ጋር አብረው የነበሩት ሦስቱን ደቀመዛሙርት (ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ እና ያዕቆብ) እንዲሁም የሙሴን እና የኤልያስን እንደተጠሪ ማኅበርተኛነት መገኘትን ለማስታወስ የሚከበር በዓል በመሆኑ ደግሞ የተማሪዎች በዓል ተብሎ ይጠራል።
በሌላ በኩል ደግሞ በባህል ደረጃ እናቶች በተለይም በሰሜኑ አካባቢ የክርስትና አባቶች እና የክርስትና እናቶች ሙልሙል ዳቦ እየጋገሩ ለልጆቻቸው የሚያደርሱበት ቀን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረታቦር ተራራ አምላክነቱን በገለጠበት ወቅት ከደብረታቦር አልፎ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ በብርሀን ተጥለቅልቆ ነበር። እረኞችም በብርሃኑ በመገረም እና በመደነቃቸው ምክንያት በጊዜ ወደ የቤታቸው ባለመመለሳቸው የእረኞቹን መዘግየት ያሳሰባቸው ቤተሰቦች ‹ልጆቻችን የት ቀሩ› በማለት ቂጣ በማዘጋጀት እንዲሁም ለብርሀን የሚሆን ችቦን በማብራት እነርሱን ፍለጋ መውጣታቸውን ለማስታወስ ሙልሙል ተዘጋጅቶ ችቦ የማብራቱ ሥነስርአት ይከናወናል።
በደብረታቦር በዓል ወቅት በሕጻናት ተዘጋጅቶ የሚጮኸው ጅራፍ ደግሞ እረኞቹ በዛን ወቅት ይዘዉት የነበረውን ጅራፍ የሚወክል ሲሆን፣ የጅራፉ ድምፅም በደብረታቦር ተራራ ላይ የተሰማውን የእግዚአብሔር አብ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚለውን መልእክት ለማስታወስ የሚደረግ መሆኑን መጋቢ ሐዲስ ያስረዳሉ።
‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቃውንት በጣም ከሚደነቁባቸው አካሄዶች መካከል›› ይላሉ መጋቢ ሀዲስ አክለውም ‹‹ምስጢር መተርጎማቸው፣ ንባብን ማቃናታቸው እና ትርጓሜን ማቅናታቸው እንዳለ ሆኖ በቀጥታ ከሌላ አገር በዓሉን ሲያመጡ ኢትዮጵያዊ ወዝ እና ቅርጽን ስለሚያስይዙት ነው። አከባበራቸውም ዓለማቀፍ ቅርፁን ሳይለቅ ኢትዮጵያዊ ወዝ እንዲኖረው ስለሚያደርጉት በየትኛውም የዓለም ክፍል በዓሉ ቢከበር እንኳን ኢትዮጵያዊ ወዝ እና ኢትዮጵያዊ ትውፊት ተሰጥቶት የሚከበረው በእኛ አገር ብቻ ነው።››
ቡሄ ለማኅበረሰብ ትስስር?
ሕጻናትና ልጆች ዱላቸውን ይዘው ‹መጣና በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ!› ብለው በየደጁ ሲያንኳኩ፣ ‹ይሄ የእገሌ ቤት ያ የእገሌ› ብለው ለይተው አይደለም። በራቸው የተንኳኳ ሰዎችም መርቀው ከተቻለም ሙልሙል ሸልመው ሲሸኙ፣ ‹የእነ እገሌ ልጆች› ብለው ለይተው አልያም ሃይማኖታችን አይደለም በማለት ገፍተው አይደለም። ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ ገጽታው ባለፈ በማኅበረሰብ ውስጥ እንደ እሴት የተያዘ መሆኑንም ከዚህ ማየት ይቻላል።
የበዓል መሰረታዊ ዓላማ ኹለት ነው ይላሉ፤ መጋቢ ሐዲስ። አንደኛው ፍጡርን ከፈጣሪው ጋር ማገናኘት ሲሆን፤ ‹በሽተኛውን የሰው ልጅ ከመድኃኒቱ ፈጣሪው ጋር፣ የተራበው የሰው ልጅ ከምግቡ ፈጣሪው ጋር፣ የተጠማውን የሰው ልጅ ከሕይወት ውሀ ምንጭ ከሆነው ፈጣሪው ጋር ማገናኘት ነው።› ኹለተኛው ደግሞ ሰዎችን ከሰዎች ማገናኘት፤ ማኅበራዊ ትስስራቸውን ማጠንከር።
በዓላት ሲመጡ የሰዎች አመጋገብ እንዲሁም አለባበስ ይቀየራል። አነጋገር ሳይቀር ይቀየራል። በቡሄ በዓል ቀን አዋቂ የተባሉ በእድሜ ከፍ ያሉ ሰዎችም ይሁን ሕጻናቱ ይሰበሰባሉ። የሆያ ሆዬ ዜማን በጋራ ይጫወታሉ። ችቦ ይበራል፣ ጅራፍ ይጮኻል፣ ባህላዊ ልምዱም ሆነ ማኅበረሰባዊ ትስስር እና ቁርኝቱ እየጠነከረ ይሄዳል።
‹‹ባህል እንደቀላል ነገር የሚታይ አይደለም›› ይላሉ መጋቢ ሐዲስ ሲቀጥሉ ‹‹ብዙውን ጊዜ ባህላቸው ያጡ አገራት ናቸው የተለያየ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ቀውስ ውስጥ የሚገቡት። ስለዚህ የበዓል ሌላኛው ዓላማ ደግሞ ሰዎችን ከብቸኝነት እና ከግለኝነት አውጥቶ ማኅበራዊ ማድረግ ነው።
በቋንቋ፣ በሀይማኖት በአስተሳሰብ የሚለያየውን ማኅበረሰብ የሚያገናኘው እና አንድ የሚያደርገው ሀይማኖት ነው የሚሉት መጋቢ ሐዲስ እሸቱ፣ ስለዚህ ሀይማኖት ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ዝናና የእውቀት ደረጃ የፈጠሯቸውን ግንቦች አፈራርሶ ሰዎችን የማገናኘት ሥራ ይሠራል በማለት ያክላሉ።
ሀይማኖት ውስጥ ደግሞ ባህል እና ስርዓት አለ። ሰላምታው፣ ‹እንኳን አደረሳችሁ› መባባሉ ሁሉ ለማኅበራዊ ኑሮና ለኅብረተሰብ ግንኙነት እጅጉን ጠቀሜታ አላቸው ብዬ አስባለሁ ሲሉም ዕይታቸውን አካፍለዋል።
የቡሄ አከባበር- በዘመናት መካከል
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በቡሄ በዓል አከባበር ዙሪያ ነባሩንና ወቅታዊውን ጉዳይ በማነጻጸር ሐሳባቸውን አካፍለዋል። ‹‹እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት የቡሄ በዓል ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ባህሎች እና ትውፊቶቻችን የምዕራቡ ዓለም ጫና ውስጥ ገብተዋል።
ሉላዊነት በማለት ፈረንጆች የክርስትና ሥም ያወጡለት አስተሳሰብ ከላይ ከላይ ሲታይ አቃፊና አቀራራቢ ቢመስልም ቅሉ አሁን ያለንበት ሁኔታ እንደሚያመለክተው ደሀ እና አዳጊ አገራት የምዕራባዊያኑ አስተሳሰብ እና ሸቀጥ መድፊያ ነው እየሆኑ ያሉት። ከፍተኛ የሚባል የባህል ወረራ ነው እየተከናወነ የሚገኘው።›› በማለት ይገልጻሉ።
በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ደሃ እና አዳጊ አገራት የኔ የሚሉት ባህል እና አስተሳሰብ እንዳይኖራቸው፣ በምዕራባዊያኑ የአመለካከት ፀበል እንዲጠመቁ፣ አለባበሳቸው፣ አመጋገባቸው፣ አነጋገራቸው ፖለካዊ ዕሳቤያቸው ሁሉ ሳይቀር የእነሱ የሆነው ሁሉ ትክክል ነው ብለው እንዲያምኑ የአዕምሮ አጠባ እየተከናወነባቸው መሆኑን ይጠቁማሉ።
‹‹እንግዲህ እኛም ዓለም ውስጥ ነው ያለነው። ከኢንተርኔቱ፣ ከፊልሙ እንዲሁም ከሌሎች የሉላዊነት ቱሩፋቶች ከሚባሉት ማምለጥ አልቻልንም። በዚህም ምክንያት በዓሉ እለት ተእለት እየተረሳና እየተዘነጋ ግጥሞቹ እና በግጥሞቹ ውስጥ ይተላለፉ የነበሩ መልዕክቶችም እየተረሱ ሄደዋል። ነገር ግን ጎጂ የሆኑትን እያረሙ እና እያስተካከሉ በተለይም ግጥሞቹን ስለ ሥነጽሑፍ ቀደምት ታሪክ የሚያጠኑ ምሁራንም ይሁኑ በፊልሙ፣ በሙዚቃውና በሌሎችም የኪነጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ጥናት እና ምርምርን በማድረግ በዘመናዊ መንገድ ማቅረብ ይገባቸዋል።›› የመጋቢ ሐዲስ እሸቱ ገለጻ ነው።
አክለውም እንዲህ በምሳሌ ያስረዳሉ፤ ‹‹እንጀራውን ሳይሆን ማቅረቢያውን መቀየር ነው። ድሮ በሰፌድ ይበላ የነበረው እንጀራ አሁን በትሪ እየተበላ ነው። በቅል ይጠጣ የነበረው ጠላ አሁን በብርጭቆ እየቀረበ ነው። መጠጡን ሳይቀየር መጠጫውን መቀየር ይቻላል። በዓሉ ባይቀየር አቀራረቡን ግን መቀየር ማስተካከል ይቻላል።›› ይላሉ።
ምክረ ሐሳባቸውን ሲያቀርቡም ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ እንደሆነና በተለይ የሥነጽሑፍና የኪነጥበብ ሰዎች ለእነሱም አዲስ ውበት እና ግኝትን ስለሚፈጥርላቸው የተባለ ነገርን አስሬ ከመደጋገም እነዚህ ግጥሞች ላይ ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ ጥሩ ነው ብለዋል። በዚህም ባህል እና ትውፊትን ያቆያሉ። የእኔ የሚለው ማንነት፣ ባህል፣ ወግና ስርዓት ያለውን ትውልድ መቅረፅ ይችላሉ። በተጨማሪም ለእነሱም ቢሆን በአዲስ መልክ የሚመጡበትና ገበያን የሚፈጥሩበትን እድልን ይፈጥርላቸዋል።
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ እና ቡሄ?
‹‹በዓል በህሊና ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅርፁ ይቀያየራል።›› ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም ‹‹ለምሳሌ በሕጻንነታችን በዓል ሲመጣ የምናየው እና የምናስበው የሚበላውን፣ የሚጠጣውን ግርግሩን ነው። ከዛም ደግሞ እድሜ እየጨመረ፣ መጽሐፍትን እያገላበጥን፣ ሊቃውንትን እየጠየቅን፣ የሀይማኖቱን ንባብ አልፈን ምስጢራቱንአልፈን ኃይለ ቃላቱን መረዳት ስንጀምር ለካ በየዋህነት እና ቅንነት ነው ስናከብረው የኖርው። ይሄን ያህል የጠለቀ፣ የረቀቀ፣ የመጠቀም ምስጢር አለው በማለት እንደነቃለን።›› ብለዋል።
እርሳቸውም ታድያ በበኩላቸው በዓሉ ያስደንቃቸውና ያስገርማቸው እንደነበር ያወሳሉ። አሁን አሁን ደግሞ በበዓሉ ውስጥ ተጠቅልሎ ያለውን ቁም ነገር፣ በበዓሉ ውስጥ የታጨቀውን ምስጢር እየተረዱ ሲመጡ የበለጠ ከአድናቆት ወደ አድናቆት፣ ከመደመም ወደ መደመም እንደመጡ ነው የሚያነሱት።
‹‹ስለዚህ በጣም ነው በዓል የምወደው። አይደለም የሀይማኖት ስርአት እና ወግ ጠብቆ የሚከበር በዓል ይቅርና የሌሎች በሌላ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩ በዓላትን አደንቃለሁ። ምዕመኑም ስርዓቱን ጠብቆና ባህሉን አውቆ እንዲያከብረውም እመክራለሁ።›› ብለዋልም።
‹‹ዓለማዊ ጉዳዮች ልዩነትን እያሰፉ እንጂ እያጠበቡ መምጣት አይችሉም። ዓለማችን ጠባብና አንድ መንደር ሆናለች የሚል ፕሮፖጋንዳ ብንሰማም ይሄም ከዚህ አሜሪካ ደውለን ሰው ማግኘት መቻላችንን ነው። ከዚህ አሜሪካ ደውሎ የምያገኘውን መረጃ እየሰማ፣ ነገር ግን አብሯት ከሚተኛው ሚስቱና በእርሱ መካከል ፌስ ቡክ እና መሰል ማህበራዊ ሚዲያዎች እየፈጠሩት ያለውን ግድግዳ ማየት ይቻላል። ይሄ ሉላዊነት በማቀራረብ ስም የማራራቅ ሥራን እየሠራ ነው።›› ሲሉ በንግግራቸው ያሉ እውነታዎችን አንስተዋል።
በአንጻሩ ይህን ክፍተት ደግሞ መሙላት የሚችሉት ሀይማኖት፣ ባህል እና ትውፊት ናቸው ባይ ናቸው። እናም እነዚህ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
‹‹ሀይማኖት እርማት አያስፈልገውም።›› ያሉት መጋቢ ሐዲስ፣‹‹እንድናምነው እንጂ እንድናርመው፤ ነብሳችንን እንድናስምርበት እንጂ አዕምሮአችንን እንድናመራምርበት አልተፈቀደልንም። ነገር ግን ባህል እና ትውፊት የምንላቸው እንደዘመኑ ጠቃሚነት እና ጎጂነታቸው እየታየ ሊቀነሱ፣ ሊጨመሩ፣ ሊጠቡም ሊሰፉም የሚችሉ ናቸው። ጎጂና አክሳሪ ባህል እና አስተሳሰብ ካለ እየታረመና እየተስተካከለ ሊሄድ ይገባዋል።በእውቀት የተደገፈ እምነት ከእርካሽ እና ጎጂ ባህሎች ነፃ ያወጣል።›› ብለዋል።
በ2012 የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የሰዎች መሰባሰብ የቫይረሱ ስርጭት እንደሚጨምር በመታወቁ ብዙ ኹነቶች ታጉለዋል። የቡሄ በዓልም የወትሮው ድምቀትና የብዙ ሰዎች ሱታፌ የሚቀንስበት ቢሆን እንኳ፣ ተሰባስበው የሚያከብሩ ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና እንቅስቃሴያቸውም በማስተዋል እንዲሆን ይጠበቃል።
ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012



