በሦስት ክልሎች 760 ሺሕ ሔክታር መጤ አረም ያለባቸው ቦታዎች ተለዩ

0
713

በስነ- ምህዳር፣ በሰብል ምርት እና ምርታማነት ላይ ችግር እያደረሱ የሚገኙትን የመጤ አረሞችን ለመለከላከል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የግብርና ሚስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

መጤ አረሞቹ በአሁን ወቅት በአማራ፣ኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ክልሎች ላይ የተከሰቱ ሲሆን አረሞቹ በመንገድ ዳር፣ በግጦሽ መሬት፣ በማሳ ውስጥ እና በውሃ ኣካላት ላይ ተብለው መለየታቸውንም የሚኒስቴሩ የእጸዋት ጥበቃ ተወካይ ዳይሬክተር ታምሩ ከበደ ገልጸዋል።

በዚህም በሦስቱ ክልሎች ላይ ብቻ ሰባት መቶ60 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ መጤ አረሞች መገኘታቸው እንዲሁም መለየታቸውን የገለጹት ታምሩ፤በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት 35 ዓይነት የሚሆኑ መጤ አረሞች ከፍተኛ ስጋት የደቀኑ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ 28ቱ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ጉዳት የሚያደርሱ እንደሆኑም በጥናት ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

ለአብነት ያህልም በርጊሃራ የሚባል አረም የቁጥቋጦ ዛፎችን እያወደመ መሆኑን የአካበቢውን ሥነምህዳር እያበላሸ መሆኑን የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህም ባለፈ ሌሎችም ሰፊ ሥራ ይጠብቀናል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም እነዚህ አረሞች የአካባቢውን ስነ ምህዳር እና ተጠቃሚ የሚባሉ እጸዋቶችን ጭምር ከማጥፋት በተጨማሪም የውሃ ጥራት በማጓደል፣የአሳ ምርት መቀነስ፣የመስኖ አውታር በመዝጋትም ጭምር ጉዳት እያስከተሉ በመሆናቸው የግብርና ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ለመስራት የሚያስችለውን መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ታምሩ ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል።

ታምሩ እንደገለጹት ከሆነም መጤ አረም ለመከላከል በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙት ተቋማት ጉዳቱን በመረዳት የግንዛቤ ሥራ ከመስራት ባለፈ በመመሪያ የተደገፈ ሥራ በማስፈለጉ መመሪያዎቹን መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

በጋራ የሚሰሩት ተቋማትም የግብርና ሚኒስቴር የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ ደን ምርምር ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ የሚያስችል መመሪያ እንደሚሆንም ታምሩ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

መመሪያው እስካሁን ድረስ መዘጋጀት እንደነበረበት እና መዘግየት እንዳልነበረበት የሚያምኑት ታምሩ፣ለዚህም ዋነኛው እና ተጠቃሹ ምክንያት ፊታችንን ወደ አንበጣ መከላከሉ ሥራ ላይ በማተኮራችን መጤ አረሞችን ለመከላከል የሚጠበቅብንን ያህል አልሰራንም ብለዋል።

መሬትን በአግባቡ አለመያዝ በራሱ አንድ ችግር መሆኑ የሚያነሱት ታምሩ መመሪያው ተጠናቆ ሲጸድቅና ወደ ሥራ ሲገባ አርሶ አደር እና አርብቶ አደሩ መሬቱን በሚገባ እንዲይዝ ግንዛቤ ከመስጠት ባሻገር መሬቱን በአግባቡ ባለመያዙ የሚጠየቅበት መንገድ እንደሚኖርም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተለይም የግጦሽ መሬት በአረም ከተወረረ እንስሳት ምግባቸውን ለማግኘት ሲሉ ወደ ቆላማ ቦታዎች እንደሚሄዱ እና አረሞቹ ወራሪ በመሆናቸው አካባቢውን በሰፊው በመውረር ጉዳት እንደሚያደርሱ ተጠቁሟል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአረሙን ስርጭት ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ ከመሔዳቸውም ጋር ተያይዞ የሚቆጣጠረው ስለማይኖር ከወዲሁ ግንዛቤ መፍጠር ስራ እንደሚሰራም አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) እንደሚሉት መጤ እና ተዛማች አረሞችን በሚመለከት በተቋማት እየተሰራ አለመሆኑን በተለይም ይህን ሥራ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት በሚገባ መስራት እንዳለበት በመጠቆም ከኢኮኖሚው ባሻገርም የሚጎዳው የስነ ምህዳር ስለሆነ ጉዳዩ ባለቤትንት መግፋት ሳይሆን ሥራን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ውስጥ ከ32 በላይ መጤ አረሞች ሊኖሩ እንደሚችል የገለጸ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ግን ከ32 በላይ መጤ አረም ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ይላሉ አደፍርስ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ መጤ አረሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የተደራጀ ሥራ ካልተሰራ አስጊ እንደሚሆን ነው ያስታወቁት።

ቁመቱም ከአንድ ሜትር እስከ ኹለት ድረስ ማደግ የሚችው ላንታና ካማራ ወይም የወፍ ቆሎ የሚባለው የአረም ዓይነት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከ80 እስከ 100 ዓመት እንደሚገመት የሚገልጹት ባለሙያው፤ ይህ አረም ሰፋፊ የሚባሉ የእርሻ ቦታዎችን በመውረር እጸዋቶች የጸሃይ ብርሃን እንዳያገኙ በማድረግ ጉዳት እያደረሰ መሆንም ገልጸዋል።

አሁን ላይ መጤ አረሞቹ በአየር ንብረት ለውጡ እና በአፈር መሸርሸር ምክንያት ምቾት ያገኙ በመሆናቸው ወደ ምስራቅ ሃረርጌ እና ወደ ወሎ አካባቢ የእርሻ መሬቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆን አስታውቀዋል።

ሌላው ከ40 ዓመት በፊት በረሃማነትን ለመከላከል ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የሚነገረው ፕሮሶፒስ ጁሊ ፍሎራ (የወያኔ ዛፍ) ተብሎ የሚጠራው አረም በአሁኑ ወቅት ግን በአፋር ብቻ አንድ ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ሸፍኖ የአፋር አርብቶ አደርን እያስለቀሰ እንደሚገኙ ያነሳሉ አደፍርስ።

ባለሙያው አደፍርስ መጤ አረም የኢትዮጵያ ስጋት ብቻ ሳይሆን የአለም ስጋት በመሆኑ አንዳንድ አገሮች አረሙን ወደ ጥቅም እያዋሉት እንደሆነ በመጠቆም በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተተከሉ እንዳሉት ችግኞች ትኩረት በመስጠት የሚመጣው ጉዳት ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ መሰራት አለበት ብለዋል።

እንዲሁም ለምርምር ተብለው ወደ ኢትየጰያ የሚገቡ ምርቶች ላይ በጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here