የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሰቲ እንደገና ሊቋቋም ነው

0
1178

መሰናዶ ያጠናቀቁ ተማሪዎችንም በምደባ መቀበል ይጀምራል

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲን እንደገና ለማቋቋም ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ ተገለጸ።ዩኒቨርስቲው ያዘጋጀው አዲስ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ በዩኒቨርስቲው ቦርድ ጸድቆ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መመራቱ የተጠቆመ ሲሆን፣ በቀጣም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ እንደሚጸድቅ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርስቲው ያዘጋጀው አዲስ ማቋቋሚያ ደንብ የኢትዮጵያ ሲቭል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ከዚህ በፊት የተቋቋመበትን ደንብ በማሻሻል የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መተዳደሪያ አዋጅን መሰረት ያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨረስቲ ፕሬዜዴንት ፍቅሬ ደሳለኝ(ፕ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።አንደ ፕሬዘዳንቱ ገለጻ አዲሱ ደንብ የተዘጋጀበት አላማ ከዚህ በፊት በዩኒቨርስቲው ሲታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረምና ከአቅም ግንባታ በዘለለ ብቃትም ለማረጋገጥ የሚፈቅድ አስራር ለመዘርጋት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ፍቅሬ አክለውም ደንቡ ከዚህ በፊት የነበረው ደንብና አላማ ያልተካተቱ አዳዲስ ተጨማሪ ተልዕኮዎችን የመጨመርና ቀድሞ የነበሩ ክፍተቶችን የመሙላት አላማን ያነገበ መሆኑን አመላክተዋል።በዚህም በዩኒቨርስቲው ከዚህ በፊት የነበሩ የአቅም ግንባታ አፈጻጸም ስራዎች ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፣ ከነበሩበት ክፍተቶች ውስጥ ዩኒቨርስቲው ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ለሁሉም ፕብሊክ ሰርቪሶች አገልግሎት እየሰጠ አልነበረም ብለዋል።ዩኒቨርስቲው ከዚህ በፊት በተወሰነ የፖለቲካ ወገንተኛ የሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ተቀብሎ ያስተምር እንደነበር ፕሬዘዳንቱ አስታውሰዋል።አዲስ የተዘጋጀው ደንብ ቀድሞ የነበረውን ክፍተት የሚፈታና ለሁሉም በአገር ደረጃ ለፌደራልም ሆነ ለክልሎች በእኩል እንዲያገለግል ተደርጎ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡

ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በአቅም ግንባታ ላይ አተኩሮ የሚሰራ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ፍቅሬ በአዲሱ ረቂቅ ደንብ አቅም ከመገንባት ባሻገር ብቃትን ማረጋገጥና መመዘን የሚስችል አስራር መካተቱን አመላክተዋል።በዚህም ዩኒቨርስቲው ያዘጋጀው አዲስ ደንብ ጸድቆ ህጋዊ መሰረት ካገኘ በኋላ በኢትዮጵያ እንዳሉ ፐብሊክ ዩኒቨርስቲዎች ሁሉ ከ12ኛ ክፍል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚችልበት እድል ክፍት እንደሚሆን ፕሮፌሰሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው ከዚህ በፊት ሲቋቋም የነበረው ደንብና አላማ እንደሌሎች የመንግስት(ፐብሊክ) ዩኒቨርስቲዎች መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚጋብዝ እንዳልነበር ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል።አዲሱ ደንብ እንደየ አስፈላጊነቱ ተብሎ እንደተቀመጠና መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማርን የሚፈቅድ ነው ተብሏል።ነገር ግን ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ እንደሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ሙሉ በሙሉ እንደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ከ12 ተቀብሎ ያስተምራል ማለት ሳይሆን በተጓዳኝ ግን መደበኛ ተመማሪዎችን የሚቀበልበት አግባብ እንደሚፈጠር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገለጻ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲን ከሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ትምህረት ተቋማት ልዩ የሚደርገው በተለያዩ ድረጃዎች በስራ ላይ ያሉ ክፍተት ያለባቸውን ሰራተኞች በመለየት ስፔሻላይዝድ የሆነ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት ማብቃት ሲሆን፣ በአንፃሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አላማ ሙሉ በሙሉ መደበኛ ተማሪዎችን በመቀበል የሰው ሀብት በማፍራት በላይ የተመሰረተ ነው።

ፐሮፌሰር ፍቅሬ ለአዲስ ማለዳ እንደጠቆሙት አዲስ የተዘጋጀው ደንብ በመጨረሻ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ ብኃላ ዝርዝር መመሪያዎችን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ክፍተቶችን የማስተካከያ አሰራር እንደሚኖር ጠቁመዋል።ዩኒቭርስቲው ከፍተቶችን በማጥናት መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለመስተማር ያቀደው እቅድ መቼ ተግባራዊ አንደሚሆን ደንቡ እስካልጸደቀ ድረስ መወሰን እንደማይቻል ተመላክቷል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር አስፈላጊውን መስፈርት ካሟላ ተማሪዎችን መመደብ እንደሚችል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደቻሳ ጉርሙ ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here