የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ አቋርጦት የነበረውን አገልግሎት ጀመረ

0
1386

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ አቋርጦት የነበረውን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በሽያጭም ሆነ በስጦታ የማስተላለፍ ውሎችን የማረጋገጥ እና የመመዝገብ አገልግሎት ከሀሙስ ነሐሴ 7/2012 ጀምሮ መጀመሩን የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር ሙሉቀን አማረ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ የኮቪድ 19 ወረርሺን መስፋፋትን ተከትሎ በ15ቱም ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ከሰኔ 17/ 2012 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ማስታወቁ ይታወሳል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃም አገልግሎቱ ተቋርጦ የነበረው በተለይ ሰኔ ወር ላይ የንግድ ፍቃድ ከማደስ ጋር ተያይዞ የኪራይ ውል፣ የአክሲዎን ማህበራት ቃለ ጉባዬዎች እና መሰል አገልግሎቶችን የሚፈልጉ በርካታ ተገልጋዮች በመኖራቸው እና ኤጀንሲው ካለው የማገልገል አቅም በላይ ተጠቃሚዎች የበዙበት ወቅት በመሆኑ ይህም የኮቪድ 19 ስርጭትን ሊያባብስ እንደሚችል በመሰጋቱ ነው። በዚህም ምክንያት የዚህ አገልግሎት ፈላጊዎች በኦን ላይን ተመዝግበው ሰልፍ እንዲይዙ ተደርጎ ኤጀንሲው ለጊዜው አገልግሎት መስጠቱን አቋርጦ እንደነበር ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰአት ግን በአንድ በኩል ከንግድ ፍቃድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚፈልጉ ባለጉዳዮች በመቀነሳቸው፤ እንዲሁም በኦን ላይን በመመዝገብ ሰልፍ የሚይዙ የአገልግሎት ፈላጊ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን በመረዳት ኤጀንሲው ከሌሎች አመታት የስራ አፈፃፀም ጋር በማነፃፀር ባደረገው ጥናት መሰረት በተለይ በነሃሴ፣ በመስከረም እና በጥቅምት ወራት ላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር የሚቀንስበት እንደሆነ በመገንዘብ ኤጀንሲው ያቋረጠውን አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ተደርጓል።

በዛን ወቅት ይህን የማንቀሳቀስ ንብረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም ያቆምንበት ምክንያት የንብረት ሽያጭ ውል ላይ ሻጭ፣ ገዢ ምስክሮችን ጨምሮ ለአንድ ጉዳይ ብዙ ሰዎች የሚመጡበት አገልግሎት ስለሆነ ይሄን እርምጃ ባንወስድ ኖሮ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከማስፋፋት አንፃር ከፍተኛ የሆነ አደጋ ይፈጠር ነበር ሲሉም ዋና ዳሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ይሄ ወረርሽኝ መቼ እንደሚቆም ባለመታወቁ፤ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን እኛም ዝም ብለን አገልግሎት ዘግተን መቀጠል የለብንም ያሉት ሙሉቀን በተጨማሪም ከዚህ በላይ ሰልፍ የሚያዙ ሰዎች መብዛት ስለሌለባቸው፣ ወረፋ የያዙትንም አገልግሎት መስጠት ስለሚገባ ከዚህ እንዲሁም ህዳር እና ታህሳስ ወር ላይ ከንግዱ ጋር የሚገናኙ የኪራይ ውል እና መሰል ወቅታዊ ጉዳዮችን ተከትሎ ሊበዛ የሚችለውን የስራ ጫና ታሳቢ በማድረግ ይሄ ያለንበትን ወቅት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የስራ ጫናን ለማቅለል ሲባል በአሁን ሰእት አገልግሎቱን የመክፈት ውሳኔ ላይ መደረሱን ሙሉቀን ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰአት በኦን ላይን ተመዝግበው ሰልፍ ለያዙ 1 ሺህ 200 ለሚሆኑ ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎቱ መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን ወረፋቸውን ሲጠባበቁ ለነበሩ ተገልጋዮችን ቅድሚያ በመሰጠቱ ከሐሙስ ነሐሴ 07 ቀን 2012 ጀምሮ ባሉት 6 ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ በወረፋቸው ቁጥር መሠረት በተመቻቸው የኤጀንሲው ሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በመገኘት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ታውቋል። ከቀጣዩ ሳምንት ሀሙስ ጀምሮም ምንም አይነት ሰልፍ መያዝ ሳያስፈልግ ማንኛውም ሰው የኦን ላይን መተግበሪያውን በመሙላት በቀረበው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተገኝቶ መስተናገድ እንደሚችልም ሙሉቀን ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ የተቋቋመበት ዋንኛው አላማ ገቢ መሰብሰብ ሳይሆን አገልግሎት መስጠት ነው። ዋንኛው ትኩረታችን ገቢ ባለመሆኑ በዚህ አገልግሎት በተቋረጠበት ወቅት ይሄን ያህል ገቢ ቀነሰብን ይሄን ያህል አጣን ብለን በጥናታችን አላመላከትነውም ያሉት ዋና ዳሬክተሩ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን ኤጀንሲው በ2012 520 ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 530 ሚሊየን ብር ማግኘት መቻሉን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here