ከኹለት ሳምንት በፊት በተደረገው የመንግሥት የንግድ ቤቶች ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ፤ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጭማሪ ባደረገባችው የንግድ ቤቶች ላይ የዋጋ ማስተካካያ ሊያደርግ እንደሆነ አስታወቀ።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙና በፌድራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደሩ የንግድ ሱቆችን የተከራዩ ነጋዴዎች ከመጠን ባለፈ ዋጋ ተጨምሮብናል በሚል ቅሬታቸውን ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ነው። እስከ አርባ አራት እጥፍ የሚድረስ ጭማሪ ተደርጎብናል በሚል ነጋዴዎቹ በተለያየ ጊዚያት ቅሬታቸውን በመያዝ በኮርፖሬሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ አቤቱታቸውንም አሰምተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የዋጋ ማስተካኪያ ሊያደርግ እንደሚችል የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፤ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን የኮርፖረሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ክብሮም ገብረመድህን በበኩላቸው የዋጋ ተመኑ የሚስተካከልባችው አሠራሮች መዘርጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ቤቶቹን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ እድሳት ያደረጉ፣ የዘርፍ ለውጥ ለማድረግ ያሰቡና ተመኑ በዝቶባችዋል ብለን በምንለያቸው ነጋዴዎች ላይ ቅናሽ ለማደረግ ጥናቶች ጀምረናል ብለዋል።
በሚቀርቡ ቅሬታዎች ሁሉም ነጋዴዎች አይስተናገዱም ያሉት ክብሮም አሠራሩ ሕግን ባማከለ መንገድ የሚከናወን ነው ብለዋል። አሁን ላይም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ሱቆች በእርጅና ብዛት ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑም ተገልጻል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ ባሳለፍነው ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 ችግሩን ለመፈታት ከነጋዴው ማኅበረሰብ የተወከሉ ከአርባ በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች አቤቱታቸውን ለኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ በፅሁፍ አስገብተዋል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች የተደረው ጭማሪ የወቅቱን ንግድ መቀዛቀዝ ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው ትላልቅ ሆቴሎችና የንግድ መዕከላት ይገኛሉ። አብዛኞቹ ሱቆችም የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ወሮ በነበረበት ወቅት የተሰሩ ናቸው።
የኮርፖሬሽኑ የኪራይ ቤቶች በአብዛኛው ለንግድ ምቹ በሆኑ አካባቢዎች ቢገኙም በካሬ ዝቅተኛ ክፍያ እየተከፈለባቸው ይገኛሉ ተብሏል።
አሁን ላይም፤ 972 የሚሆኑ የንግድ ቤቶች በካሬ ሜትር ከአንድ ብር በታች የሚከራዩ ሲሆን 2057 ቤቶች ደግሞ ከ 10 ብር በታች በካሬ ይከራያሉ። በዚህ የተነሳ፤ ኮርፖሬሽኑ የሚገባውን ያክል ገቢ እያገኘ አለመሆኑን ይገልጻል።
ከዛም ባለፈ፤ የወሰዱትን ቁልፍ ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው በሚሊዮን በሚቆጠር ብር የሚሸጡ ብዙዎች መሆናቸውን ከዚህ ቀደም የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ። ይህን ተከትሎ ሱቆቹ መታደስ እና ህጋዊነታቸውን ማረጋገጥ ስላለባችው በእያንዳንዱ ሱቆች ላይ ዋጋ መጨምር ማስፈለጉን ኮርፖሬሽኑ መግለጹ ይታወሳል።
በሌላ በኩል፤ ከኹለት ዐስርት ዓመታት በኋላ ግንባታ ላይ የተሰማራው ኮርፖሬሽኑ ካለበት የበጀት እጥረት አኳያ፤ ለ43 ዓመታት የዘነጋውን የኪራይ ዋጋ ማሰተካካያ ጉዳይ ድጋሚ ለማንሳት መገደዱን ምንጮች ይገልጻሉ።
በሚቀጥሉት ሳምንታትም ቅሬታ አቅራቢዎች ተለይተው ውሳኔ እንደሚሰጣቸውም ተገልጻል። የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን በስሩም 6635 የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን በአዲስ አበባ ያስተዳድራል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011