ታኅሣሥ 16 በውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የእርቀ ሠላም ኮሚሽን በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል። ‹‹የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና በኢትዮጵያ በሕዝቦች መካከል የሚታየውን ቅራኔ ለመፍታት በሚል የተቋቋመ ኮሚሽን ነው ሲሉ›› የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ተስፋዬ ዳባ ገልፀዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው ሰብሳቢው ሲገልፁ የእርቅና የሠላም ዓላማን ያነገበ፣ ለግጭትና ቁርሾ ምክንያት የሆኑትን ዝንፈቶች የስፋት መጠን አጣርቶ እውነታን በማውጣት ተመልሰው እንዳይከሰቱ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አቅጣጫ ጠቋሚ ገለልተኛ ኮሚሽን ነው ብለዋል።
በጣት የሚቆጠሩ የሕወሓት አባላት የተገኙበት ጉባኤው በቀረበለት የኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ማፀደቂያ ላይ በርካታ አስተያየቶችን አስነስቷል። የምክር ቤት አባሉ ሻምበል ነጋሳ ጥያቄያቸውን ሲያነሱ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን እንደአስፈላጊነቱ ያካትታል ተብሎ የተቀመጠው አካሄድ ስህተት ነው። ምክንያቱም በአዲስ አበባም ሆነ በድሬዳዋ በርካታ አለመግባባቶች ተስተውሎባቸዋል ስለዚህ እንዳስፈላጊነቱ የሚለው ቢቀር መልካም ነው ብለዋል። ሌላው የምክር ቤት አባል ደግሞ በዳይ እና ተበዳይ ሲባል በምን ደረጃ ነው ? ኮሚሽኑስ የሚያመጣው ለውጥ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? ካሉ በኃላ ኮሚሽኑ ምንም አይነት የፖለቲካ ንክኪ እንዳይኖርበት አሳስበዋል።
ሌላው የምክር ቤት አባል ካሳ ጉግሳ ያነሱት ሐሳብም ኮሚሽኑ ካጋጠመው ተቃውሞዎች አንዱ ነው። ‹‹ኮሚሽኑ ማንን ከማን ነው የሚያስታርቀው?›› ሲሉ የጀመሩት የምክር ቤት አባሉ ‹‹ሕዝብ ከሕዝብ አልተጣላም፤ ተጣልቶም አያውቅም። እንዲያውም በአሁኑ ወቅት ድርጅቶች ናቸው አለመግባባት ውስጥ ያሉት ስለዚህ ኮሚሽኑ ድርጅቶችን ቢያስታርቅ ነው የሚሻለው። ስያሜውም ‘የድርጅቶች ግጭት የሰላም ኮሚሽን” ቢባል ይሻላል›› የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ካሳ አክለውም ‹‹ዲላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎችን ሰብስበን ስናወያይ የተረዳነው ችግሩ ከውጭ እንደሚመጣ እንጂ በተማሪዎች መካከል ምንም ችግር የለም። የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በድርጅቶች መካከል ነው እርቅ የሚያስፈልገው ስለዚህ የኮሚሽኑን መቋቋም በግሌ አልቀበለውም›› በማለት ሐሳባቸውን አቅርበዋል።
የኮሚሽኑን ነፃና ገለልተኛነት በተመለከተ ሌላው የምክር ቤት አባል ብርሃኑ መኩየ ኮሚሽኑ ለአስፈፃሚ አካል ተጠሪ ሆኖ እንዴት ነፃ እና ገለልተኛ ይባላል በሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ላዋይሽ ተወልደ ‹‹እርቅ የሚጀምረው ከዚሁ ምክር ቤት ነው። ለአንድ አገር እየሠራን ሕዝብን ወክለን የተቀመጥን ሰዎች ፍፁም የማይታረቅ ሐሳብ ልናራምድ አይገባም›› ሲሉ ይናገራሉ። በመሐመድ አህመድ የተነሳው አስተያየት ደግሞ ‹‹27 ዓመት ሲዘራ የነበረው ጥላቻ ፍሬ አፍርቶ ህዝብ እየተጫረሰ ነው። እርቅ እና ሰላም ከሌለ ወደ ከፋ ነገር ነው የምንገባው፤ የአገሪቱን ሀብት ዘርፈው አሁንም ህዝቦችን የሚያጋጩ አሉ ይሄንንም ሕግ ሊይዘው ይገባል›› ብለዋል። ይሄን ሀሳብ የሚጋሩት ሌላው የምክር ቤት አባል ደግሞ ‹‹እኛ እናውቅልሀለን ማለት ይብቃ ፣ ሕዝብ እኛ እያወቅን ለምን ያልቃል? በእርግጥ 20 ዐመታት ተንኮል ያስተማርነው ሕዝብ በአጭር ጊዜ ሊለወጥ አይችልም ግን ደግሞ ከመሞከር መስነፍ የለብንም መጨራረስ ለውጥ አያመጣም። ሕዝባችን ሠላም ይፈልጋል ነገር ግን ግጭትን እየፈጠሩ ያሉ ቡድኖች ባሉበት ሁኔታ እና ተገቢው እርምጃ ሳይወሰድባቸው ሠላምን፣ እርቅን መናፈቅ አይታሰብም›› ብለዋል።
የተበደለ ሕዝብ መካስ አለበት፤ እርስ በእርሱ መታረቅ አለበት የሚል ሐሳብም በምክር ቤት አባላት ተነስቷል፡፡ ‹‹የተበደሉ የሚባሉት የተደበደቡት፣ የተገደሉት፣ የተፈናቀሉት ናቸው›› የሚሉት አባላት በዳይን ደግሞ ኮሚሽኑ አጣርቶ ከሚያመጣው ውጤት ማየት እንደሚቻልም ያነሳሉ። አያይዘውም በአረጀ እና በአፈጀ መንገድ ኢትዮጵያን አሁንም ለመምራት የሚጣጣሩት አገር አፍራሾችን ወደ ጎን መተው ይገባል ሲሉ ሐሳባቸውን ሰነዝራሉ።
ከምክር ቤቱ ለተነሱት በርካታ ጥያቄ እና አስተያየቶች የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተስፋዬ ዳባ ምላሽ ሰጥተዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የኮሚሽኑ አባላት የሚሄዱበትን አካባቢ ወግ እና ባሕል ቢያውቁ መልካም ነው ያሉ ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የየአካባቢውን የአገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎችን ያካትታል ብለዋል። በዳይ ተበዳይ ስለሚለውም ሲያብራሩ በኮሚሽኑ 20ዎቹም አንቀጾች ውስጥ ይኼ ቃል የለም ነገር ግን ተበድያለሁ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል የለም ብለን መነሳት የለብንም ብለዋል፡፡ የዚህ ኮሚሽን ዓላማም ተበድያለሁ የሚል አካል ካለ መፍትሔ ለማምጣት እንደሆነ አንስተዋል። ግጭት ያለው በድርጅቶች መካከል ነው ለተባለውመ አስተያየት ምላሽ ሲሰጡም ‹‹የፖሊቲከኞችን ጉዳይ ለራሳቸው ለፖለቲከኞች እንተወው ምክንያቱም የራሳቸው የውይይት መድረክ ስላላቸው ይፈቱታል›› ብለዋል።
ሕገ መንግሥቱ ምሕረት የማይደረግላቸው በሚል ያሰፈራቸውን ወንጀሎች ላይ ኮሚሽኑ ምንም ዓይነት ሥራ አይሰራም፣ የወንጀል ምርመራ ተግባርንም አያከናውንም ነገር ግን የችግሮቹነ ምንነት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ መሆናቸውን አጣርቶ ያቀርባል።
የእርቀ ሠላም ኮሚሽኑን መቋቋም በተመለከተ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምሁራን እንደተናገሩት ከማንነትና አስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ይልቅ መጽደቅ ያለበት የእርቀ ሠላም ኮሚሽን ነው።
ለዚህም እንደምክንያት ያስቀመጡት የእውነት እርቁ እና ሠላሙ ካለ ሕዝብ በፈለገበት ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመስራት እና ደኅንነቱ የመጠበቅ እድልን ያገኛል የሚል ነው። ይህ ደግሞ ወሰን፣ ድንበር፣ ማንነት፣ ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች ኢትዮጵያ ወደሚል እሳቤ ከፍ ይሉና አገራዊ አንድነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያግዛልም ይላሉ።
ከክርክርና መልስ በኋላ ለምክር ቤቱ የቀረበው የእርቀ ሠላም ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 5/2011 በአንድ ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጽ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል። በእለቱ የሕወሓት አባላት ከሆኑት የሕዝብ እንደራሴዎቹ መካካል ከግማሽ የሚልቁት የምክር ቤቱ አባላት አልተገኙም።
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011