ስኳር ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታ ሊዛወር ነው

0
1108

የጣና በለስ ቁጥር ኹለት ስኳር ፋብሪካን ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ድርድር መጀመሩን የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
ፋብሪካው በመንግሥት በመጀመሪያውና ኹለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሊገነቡ በዕቅድ ተይዘው ከነበሩት 10 የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ ነው።ውሳኔው ከስድስት ወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አስተዳደር ትላልቅ ፕሮጀክቶችንና የመንግሥት ኢንተርፕራይዞችን የማዘዋወር ዕቅድ አካል መሆኑ ተገልጿል።
በተለምዶ ሜቴክ ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የፋብሪካውን ግንባታ እንዲቋረጥ ከተወሰነ አንስቶ ምንም እንቅስቃሴ ያልነበረበት ጣና በለስ ቁጥር ኹለት፤ በአማራ ክልል በሚገኝ የመንግሥት ልማት ድርጅት ፋብሪካውን ሙሉ ለሙሉ ለመግዛት ጥያቄ ቀርቦ ግምገማ ላይ መሆኑ ታውቋል።
ወደ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የወጣበት ጣና በለስ ቁጥር ሁለት ግንባታው 23 በመቶ አካባቢ ሲሆን፤ ስኳር ፋብሪካው 12000 ቶን ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅም አለው።
የስኳር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ጋሻው አይችሉህም እንደገለጹት፤ የስኳር ፋብሪካውን ትክክለኛ ሀብትና አቅም ለማወቅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ሊገባ ነው። ይህ ከታወቀ በኋላ ዋጋ ላይ ድርድር እንጀምራለን፤ ይሁን እንጂ፤ ወደ ግል የማዛወሩ ጉዳይ ተወስኗል ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የተወሰነው ከዚህ ቀደም በሜቴክ የተያዙ ፕሮጅክቶችን ለማስቀጠል በአዲስ ኮንትራክተር ሥራውን ለማስጀመር ከተወሰነ ዓመት በኋላ ነው።
የቀድሞ መንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር የነበሩት ግርማ አመነቴ (ዶ/ር) ሚያዝያ 4/2010 የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ሲያቀርቡ ፣ የጣና በለስ ቁጥር ኹለት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ከሜቴክ ተነጥቆ በአዲስ ኮንትራክተር ሥራውን ለማስቀጠል እየተመከረ ነው ብለው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በተጨማሪም፤ በሜቴክ ተይዘው በግንባታ ላይ የነበሩት ኦሞ ኩራዝ አንድ እና ጣና በለስ አንድ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለኮርፖሬሽኑ የማስረከብ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጋሻው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኦሞ ኩራዝ አንድ ከሜቴክ እስከተቀማበት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሲሆን ለፕሮጀክቱ የተመበደበው በጀት ሙሉ ለሙሉ ቢወጣም መጠናቀቅ የቻለው 80 በመቶ ግንባታው ብቻ መሆኑ የኮርፖሬሽኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በተቃራኒው፤ የሜቴክ የቀድሞ ኃላፊዎች የፕሮጀክቱ 90 በመቶ ግንባታ ተጠናቋል ብለው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።
በሌላ በኩል፤ የቀድሞው ሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ክንፈ ዳኘው፤ በሙስና ተጠርጥረው ከመታሰራቸው በፊት ከናሁ ቴሌቭዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሮጀክቱ ለሥራ ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም። ሜቴክ የጣና በለስ አንድ ግንባታን 78 በመቶ ተጠናቋል ቢልም ኬኒያና የተባለው የስኳር ኮርፖሬሽን የውጭ አማካሪ 65 በመቶ ተጠናቋል ብሏል። ፕሮጀክቱ ባይጠናቀቀም፤ ሜቴክ ወደ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገደማ መውሰዱን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
ጋሻው ከሜቴክ የተነጠቁትን ኦሞ ኩራዝ አንድ እና ጣና በለስ አንድ ግንባታ ለማስቀጠል አዲስ ዋና ተቋራጭ መረጣ ላይ መሆናቸውን ገጸፀዋል። ወልቃይት ስኳር ፋብሪካን በመገንባት ላይ ያለው ካምፕስ፣ ኩራዝ ሦስትን የገነባው ኮምፕላንትና ጄጄ አይ ሲ ኩራዝ አምስትን የሚገነባው ድርጅት የፕሮጀከቶቹን ግንባታ ለማስቀጠል እየተወዳደሩ መሆናቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።
ስኳር ኮርፖሬሽን በዚህ በጀት ዓመት አሁን ሥራ ላይ ያሉትን ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን በመጠቀም 5.2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ለማምረት አቅዷል። በተጨማሪም በበጅት ዓመቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊውል የሚችል ከ21 ሚሊየን ሊትር በላይ ኢታኖል በመተሐራና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ለማምረት አቅዷል።
በሌላ በኩል ባለፈው በጀት ዓመት በስኳር ኢንዱስትሪ እና ተጓዳኝ ምርቶች ላይ ጥያቄ ካቀረቡ 25 ኩባንያዎች መካከል ከ17ቱ ጋር ውይይት መጀመሩን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል። ለአብነትም ያህል፤ በኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ኢታኖል ፋብሪካ ለማቋቋም የግብዓት አቅርቦት ውል ተፈራርሟል። በተጨማሪም ከአልጄሪያው ሲቪታል፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቱ ሉታህ እና ጂ ግሎባል የተባሉ ድርጅቶች በስኳር ኢንዱስትሪ እና ተጓዳኝ ምርቶች ለመሰማራት ጥናት እያደረጉ ሲሆን ከኮርፖሬሽኑ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here