አምስት ድርጅቶች ከመድረክ ጋር ለመሥራት ተስማሙ

0
495

“ትብብር ለህብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ፌደራሊዝም(ትብብር) ምስረታ በሒደት ላይ ነው

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በውስጡ ከያዛቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት ሌሎች ተጨማሪ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የሚመሰርቱት ግንባር ትብብር ለመመስረት በመስማማት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ለማግኘት የስምምነት ሰነድ ማስገባታቸው ተገለጸ።

ትብብሩን ለመመስረት የተስማሙት ፓርቲዎች የመድረክ ግንባር አባል ድርጅቶች በመድረክ ስም እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ)፣ የአገው ብሔራዊ ሽንጎ፣ የኦጋደን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር(ኦብነግ)፣ የከፋ አረንጓዴ ፓርቲና ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሆናቸውን የመድረክ ፀሐፊ ደስታ ዲንካ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በመድረክ ውስጥ ታቅፈው ከሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ)፣ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲያዊ እና ሉዓላዊነት(ዓረና)፣ የአፋር ህዝብ ድሞክራሲያዊ ፍትህ ፓርቲ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢሶዴፓ) ሲሆኑ አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ዕትሟ ኢሶዴፓ ከኦፌኮ ጋር በመድረክ ውስጥ መቀጠል እንደሚቸገር መዘገቧ ይታወሳል።

ጸሐፊው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ኢሶዴፓ በአዲስ ትብብር ውስጥ ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም የሚለው ጥያቄ ውሳኔው በመድረክ ስም የሚወሰን ስለሆነ የኣባል ድርጅቶች ግላዊ ውሳኔ የለውም ብለዋል፡፡

መድረክና ከላይ የተዘረዘሩ ሌሎች አመስት ፓርቲዎች ለመመስረት ለምርጫ ቦርድ ያስገቡት ምስረታ ሰነድ ላይ የትብብሩ ስያሜ “ትብብር ለህብረ ብሔራዊ ድሞክራሲ ፌደራሊዝም(ትብብር) የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የመድረክ ጸሐፊ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።ፀሐፊው አክለውም መድረክ እንደ ግንባር እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በምስረታ ላይ የሚገኘው የትብብር ድረጅት ለምርጫ ቦርድ ባስገባው ሰነድ ላይ የድርጅቱን አመራሮች ሰይሞ መላኩን ደስታ ጠቁመዋል።የትብብሩ አባል ድርጅቶች በተስማሙበት መሰረት የትብብሩ ሊቀመንበር የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ሊቀመንበር የሆኑትን ዳውድ ኢብሳን ሊቀመንበር፣ አብድራህማን ሽህ መሐዲ ምክትል ሊቀመንበር አንዲሁም አላምረው ይርዳው የትብብሩ ፀሐፊ አድረጎ መሾሙን ደስታ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል፡፡

አንደ ደስታ ገለጻ አዲስ ትብብር ለመመስረት ስምምነት ላይ ሲደረስ መድረክን ለማፍረስ ምክንያት አይሆንም የሚል ጥያቄ መነሳቱን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።ነገር ግን አዲሱ ትብብር ለመድረክ መፍረስ በምንም መስፈርት ምክንያት ሊሆን እንደማይችልና መድረክ በምንም አይነት አይፈርስም ብዙ የተደከመበት ድርጅት ነው ሲሉ ደስታ አክለው ገልጸዋል፡፡

ትብብሩን ለመመስረት የመድረክ ሊቀመንበር መራራ ጉዲና(ፕ/ር)ና የሌሎች አባል ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቀድሞ የጋራ ውይይትና መግባቢያ መድረክ በመፍጠር በአንድ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተመላክቷል።የትብብሩ አባል ድርጅቶች የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ስምምነት ተፈራርመው ለምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና እንዲኖረው ማስገባታቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት መራራ ጉዲና(ፕ/ር) ትብብሩ ከስብስብ አንፃር ትልቅ ድርጅት ሆኖ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

አዲስ ማለዳ በባለፈው ሳምንት እትሟ የኢሶዴፓን በመድረክ ውስጥ የመቀጠል እድል ኦፌኮ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በሚደርገው ትብብርና ፊርማ አለመስማማቱ መሆኑን ዘግባ ነበር።በዚሁ ጉዳይ የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ኢሶዴፓ ከመድረክ ጋር ወደፊት ላለመቀጠል የፈለገበት ምክንያት መድረክ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር ለመፍጠር በመንቀሳቀሱ እና የትብብር ስራ በመስራቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።እንደ ፕሮፌሰር መራራ ጥቆማ የልዩነቱ ዋና ምክንያት መድረክ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር መፍጠሩ ቢሆንም ሌሎች የልዩነት ነጥቦችን መናገር አልፈልግም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

አዲስ ማለዳ ስለ ትብብሩ ህጋዊ እውቅና እንድሰጠው ለምርጫ ቦርድ ማቅረቡን ለማረጋገጥና ምርጫ ቦርድ የወሰነውን ውሳኔ ለመስማት በተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም የሚመለከታቸው አካላትን ማግኘት ባለመቻሏ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here