ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ባለሥልጣናት ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሊተላለፉ ነው

0
580

የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተደጋጋሚ በሰጠው ጊዜ ገደብ እንዲያስመዘግቡ ተጠይቀው ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ አሳልፎ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

አብዛኛዎቹ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ማለትም ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታዎች ኮሚሽኑ ባስቀመጠው ጊዜ ገደብ ሀብታቸውን፣ ማለትም እስከ ሐምሌ 30/2012 ድረስ ቢያስመዘግቡም በአንፃሩ በጣት የሚቆጠሩ ሚኒስቴርና ሚኒስተር ዴኤታዎች በተደጋጋሚ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ህግን የማስከበር ሥራ ለመሥራት ኮሚሽኑ አስፈላጊ አባሪ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ እንዲሁም በግልባጭ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትና ለጠቅላይ አቃቢ ህግ ለማስገባት መወሰኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ኃላፊነቱን ለመወጣት በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በስልክ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በአካልና በሚቀርቧቸው የሥራ ባልደረቦች ጭምር ቢጠየቁም ፈቃደኛ አይደሉም ሲል አስታውቋል። በኮሚሽኑ በኩል ከሚጠበቅበት በላይ እስከመለመን ድረስ ቢደርስም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ማረጋገጡን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጧል። ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ባለስልጣናት ከሚመሩት መስሪያ ቤትና ተቋም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑንና የግለሰብ ጉዳይ መሆኑን አስታውቋል። በመሆኑም ጉዳያቸው የሚታየው በግለሰብ ደረጃ ነው ተብሏል።

ባለስልጣናቱን ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ያደረገው የልመና ጥሪ ጭምር ባለመቀበላቸው ኮሚሽኑ ህግን የማስከበር ግደታ ስላለበት ግደታውን ለመወጣት በሀብት ምዝገባ አዋጅ መሰረት እንደሚሰራ የተጠቆመ ሲሆን፣ በአዋጁ መሰረት በህግ አግባብ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ አካላት ላይ በኹለት መንገድ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል። በአዋጁ ከተቀመጡ አስራሮች ውስጥ አንደኛው አስተዳደራዊ እርምጃ ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ወንጀልን የሚስከትል እርምጃ መሆኑን የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአዋጁ መሰረት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው የተሰጣቸው ጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ አስፈላጊው እርምጃ ተወስዶ አንድ ሺህ(1000) ብር ተቀጥተው ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚደረግበት የህግ አግባብ መኖሩን አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ የባለስልጣናቱን አስፈላጊ መረጃ የማጠናከር ስራ በማደራጀት ስርዓት የመገንባት ስራውን እንደሰራ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፍትሕ ተቋማት ህግ እንዲከበር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። አብዛኛዎቹ የመንግስት ባለስልጣናት በተለይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለስልጣናት ሀብታቸውን በተገቢው ጊዜ ማስመዘገባቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ለምርመራ አካል የሚላከው መረጃ የባለስልጣናቱን ስም ዝርዝር ለሚዲያና ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተመላክቷል።

የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቀደም ሲል ባወጣው የ2012 በጀት ዓመት የመንግስት ባለስልጣናት የሀብት ምዝገባ ቀነ ገድብ 90 በመቶ የሚሆኑ የፌደራል ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት ባለስልጣናት በተሰጠው ቀነ ገደብ ማስመዝገባቸውን ኮሚሽኑ መግለጹን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

በሌላ በኩል የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የባለስልጣናትን ሀብት በኦንላይን በይፋ የሚያሳይ ስርዓት ማዘጋጀቱን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ስርዓት ዘመናዊ እንደሆነና ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን መረጃ አስመርጦ ሚሰጥ ነው ተብሏል።

ይህን ስርዓት ተግባራዊ ለመድረግ የሚስችል የቀደመውን አዋጅ በማሻሻል ኮሚሽኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅ ማቅረቡን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። የማሻሻያው ዋና አላማ የመንግስት ባለስልጣናትን ሀብት ለማወቅ የሚፈልግ ሰው በፅሑፍ ጥያቄ ማቅረብ አለበት የሚለውን አዋጅ በማሻሻል ማንኛውም ሰው ወደ ኮሚሽኑ መምጣት ሳይጠበቅበት የሚፈልገውን መረጃ ባለበት መግኘት ለማስቻል መሆኑን መስፍን ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here