አዋሽ ባንክ የ25 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዛ

0
817

አዋሽ ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ25 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ ፈጸመ። ቦንዱን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዛሬ አስረክቧል።

የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፀሐይ ሽፈራው በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ ብስራት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የቦንድ ግዥና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ተስፋ ሰጪና አስደሳች መሆኑንም ተናግረዋል።

”በዚህ ታሪካዊና አገራዊ ግድብ ላይ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ አሻራ ማሳረፍ ዕድለኝነት ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በአገሪቱ እየታየ ላለው ፈጣን ልማት ፕሮጀክቱ ያለው ሚና የጎላ ነው ብለዋል። በዚህም ባንኩ ደስታውንና አጋርነቱን ለመግለጽ ቦንዱን መግዛቱን አቶ ፀሐይ አስታውቀዋል። በቀጣይም ግድቡን ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ባንኩ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ባንኩ ያደረገው ድጋፍ ”ምሳሌ የሚሆንና የሚበረታታ ነው” ብለዋል።

ባንኮች ቦንድ መግዛት የቁጠባ ባህልን ከማዳበር አኳያ ያላቸው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ሌሎች ባንኮችም እያደረጉ ያለውን ድጋፍ በማስቀጠልና በማጠናከር አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ከተከናወነ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት በቅርቡ ኒያላ ኢንሹራንስ 12 ሚሊዮን ብር ቦንድ የገዛ ሲሆን፤የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአምስት ሚሊዮን ብር ስጦታ ማበርከታቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here