የፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት በእነ ጃዋር መሐመድ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ላይ ዐቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮችን አሰማ:: ችሎቱ ወደ ምስክር ሂደት ከመግባቱ በፊት ባለፈው ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ትእዛዝ አፈጻጸም ተመልክቷል። ጃዋር ከደህንነታቸው አንፃር ባላቸው ሁኔታ ከግል ሐኪማቸው ጋር ሊገናኙ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ከሕክምና ጋር በተገናኘ ጃዋር እኔ ከመረጥኩት ከግል ሐኪሜ በስተቀር በመንግሥት ሆስፒታል እንዲታከሙ ቢጠየቁ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ፖሊስ አስረድቷል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ከፖሊስ ጋር በመሆን ጃዋርን በማየት ሕመማቸው አጣዳፊ ከሆነ በግል ሐኪማቸው እንዲታዩ ቢባልም የግል ሐኪማቸው ስልክ ባለመገኘቱ ሊሆን እንዳልተቻለ አብራርቷል። ጃዋር በመንግሥት ሆስፒታል አልታከምም ማለታቸው ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ እንዳስገባው እና በዚህም ተጠርጣሪው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እንደ ማንኛውም ሰው በፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል መታከም እንደሚችሉ ፖሊስ አክሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጃዋር እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 9 ተጠርጣሪዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ችሎት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ምርመራ ማድረጋቸውንም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በሌላ በኩል በቀለ ገርባ እና ሀምዛ አዳነ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቢሮ ክፍል ካሜራ በመኖሩ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን አቤቱታ በማቅረባቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተመልክቷል።
ፖሊስ በበኩሉ ካሜራው የተቀመጠው ግቢው አዲስ በመሆኑ እና በተለይም በላይብረሪ ውድ የሆኑ መጻሕፍት በመገኘታቸው መሆኑን ጠቅሶ ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት ክፍል መመቻቸቱን ገልጿል።
ግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 መሠረት ተጠርጣሪዎች መብታቸው እና ጤናቸው መጠበቅ እንዳለበት ብሎም ከግል ሀኪሞቻቸው ጋር እንዲገናኙ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ከዚህ ባሻገር ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ምሥጢራቸውን መጠበቅ በሚያስችል መልኩ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ያድርግ ብሏል። ይህ ትእዛዙ የማይፈጸም ከሆነ በቀጣዩ ቀጠሮ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት የሁለት ምስክሮች ቃል የሰማ ሲሆን፣ በቀጣይ የሌሎች ምስክሮችን ቃል ለመስማት ለነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012



