አዲሱ የከተማ አስተዳደር – ተስፋና ስጋት

0
1407

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ምክትል ከንቲባ ከተሰየመ ቀናት ተቆጥረዋል። ይህንንም ተከትሎ ከዚህ ቀደም በከተማዋ አንዳንድ ክፍለ ከተሞች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ መሬት ወረራዎችና ሌሎች ተያያዥ ብልሹ አሠራሮችን በሚመለከት አዲስ ማለዳ ሰፊ ጽሑፍ ማዘጋጀቷ ይታወሳል። በዚህ ዕትም በቀጣይ በከተማዋ አዲስ ከተሾሙት አዳነች አቤቤ ዘንድ ነዋሪው ምን ይጠብቃል? ምንስ ሥጋት ይኖርበታል? የሚለውን እና ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ በአካል ተገኝታ ከታዘበቻቸው አካባቢዎች በመነሳት በአሁኑ ወቅት ያለውን የመሬት ወረራዎችን እና ነዋሪዎችን አስተያየት በማጠናቀር እንዲሁም ከሚመለከተው የመሬት ልማት ባንክ ኃላፈዎችንም ድምጽ በማካተት የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ከሰሞኑ በታየው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡ ዐስር ሹመቶች መኖራቸው በመገናኛ ብዙኀን ዘንድ በሰፊው ሲወራ መሰንበቱ የሚታወስ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ታዲያ በቅርቡ ከብልጽግና አባልነታቸው የታገዱትን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩትን ለማ መገርሳን እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የነበሩት ታከለ ዑማ ከኃላፊነት መነሳት እና በሌሎች መተካት በርካቶችን ያነጋገረ እና ሰፊ ትኩረትም የተሰጠው ጉዳይ ነበር።

ምንም እንኳን የለማ መገርሳ መነሳት ቀድሞውንም ተጠብቆ የነበረ ጉዳይ እንደነበር ቢታወቅም፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ‹ምነው ሰው አልረጋለት አለ?› በሚል የቦታውን የአመራሮችን እንሽርሽሪት በማንሳት ትችት ቢጤም ሲታከልበት ሰንብቷል። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ በዚህ ሳምንት በርካታ ውጥረቶች እና በነዋሪዎችም ዘንድ ክፉኛ መማረሮች፤ በተለይም ደግሞ ተዘዋውራ በሰበሰበቻቸው መረጃዎች ውስጥ በሕገ ወጥ መሬት ወረራዎች ዙሪያ የነዋሪዎችን ምሬት እና አዲሷን ምክትል ከንቲባን የኃላፊነት ብቃት ተስፋ በማድረግ የሚሰጡትን አስተያየት ጠይቃ ተረድታለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተሰናባቹ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ለመቆጣጠር እና ለማስቆም በሚል በከተማዋ መሬት ኦዲት እና ምዝገባ ሥራ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በበርካታ አካባቢዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ባዶ ቦታዎች በአንድ አዳር የፈረሱበት ሁኔታ ቢኖርም፤ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በቃኘችባቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ግን ከቀደመው ጊዜ በባሰ ፍጥነት እና ዐይን ባወጣ መንገድ ክፍት ቦታዎች እየተመረጡ ሲታጠሩ ሰንብተዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አካባቢ አዲስ ማለዳ በዐይን ለመታዘብ እንደቻለችው በሰውነት ተክለ ቁመናቸው ግዙፍ የሆኑ ወጣቶች በአካባቢው በመምጣት እና በጭነት መኪና አጣና እና ብዛት ያላቸው ወጣቶችን በማምጣት ክፍት ሆነው የቆዩ መሬቶችን ማለትም በማኅበር ለተገነቡ መኖሪያ መንደሮች አረንጓዴ ስፍራ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን በጉልበት ሲያጥሩ ታዝባለች። ይህም ሲከወን ደግሞ የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች በስፍራው መገኘታቸውን ለመመልከት ችላለች።
ወደ ወረዳው መሬት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ ወደሆኑትና እምሩ ወደሚባሉ ግለሰብ በመቅረብ ስለ ጉዳዩ ለማናገር ብትምክርም በግለሰቡ ፈቃደኛ አለመሆን ምክንያት ሙከራዋ ሳይሳካ ቀርቷል።

በዚሁ ወቅት አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም አሰሳ አድርጋ በነበረባቸው እና ሕገ ወጥ መሬት ወረራዎች በብዛት ተንሰራፍቶባቸዋል በተባሉ ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ዘንድ በመሔድ ከመመሪያው ወዲህ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ለመቃኘት ሞክራለች። ነዋሪዎችን፣ በማጠር ላይ የነበሩ ግለሰቦችን እንዲሁም ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችን አነጋግራለች።

በተለይም ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ለዓመታት ክፍት በተተወ መሬት ላይ በአንድ አዳር ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ እንደተከናወነ የታዘበችው አዲስ ማለዳ፣ ከዚህ ወረራ ጀርባ ማን እንዳለ ለማወቅ የተለያዩ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራዎችንም ስትሠራ ቆይታለች። በዚህም ረገድ መሬቶች በሚታጠሩበት ወቅት እና ከታጠሩ በኋላ በተደጋጋሚ እየተመላለሱ መሬቱ የአያቶቻቸው እንደነበር እና በቅርቡም የእርሻ ሥራ እንደሚጀምሩበት የሚናገሩ አርሶ አደር ቁመና ያላቸው ግሰለብ መሆናቸውን መረዳት ችላለች። ተጨማሪ ጥቆማዎች ግን በአርሶ አደር ነኝ ባዩ ሰው ተገን አድርጎ መሬቶቹ ከታጠሩበት አካባቢ እምብዛም ሳይርቅ የሚኖር ከበርቴ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በከንቲባ ጽሕፈት ቤት መመሪያው ከወጣ በኋላ መሬት ወረራው እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው ደግሞ በኦዲት እና ምዝገባ ሰበብ ቀድሞ የተያዙ መሬቶች ወደ ሕጋዊነት ይዘዋወራሉ የሚል መረጃዎች በሰፊው መሰራጨታቸው እንደሆነ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በሕገ ወጥ መንገድ ታጥረው የነበሩ እና በኋላ ላይ በተደረገ ዘመቻ ወደ መሬት ባንክ ተመልሰው የነበሩ መሬቶች እንደ አዲስ ወረራ እንደተደረገባቸው፤ ለዚህ ደግሞ የየወረዳዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊዎች በዋናነት ተዋናይ መሆናቸው አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8፣ 9 እና 10 የተባሉ አካባቢዎች የወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎች ሳይቀሩ በአካል በመገኘት ሰዎችን እንደሚያስፈራሩም ለመረዳት ተችሏል።

የመሬት ወረራውን ያስቀራል ተብሎ በመስተዳደሩ ይፋ የሆነው ይኸው መሬት ኦዲት እና ምዝገባ ታዲያ ጥሎት ባለፈው የሕገ ወጥ ወረራ ጉዳይን መሰረት ያደረጉ ተግባራት ከመታየታቸውም በላይ ለምን የአረንጓዴ ስፍራቸው እንደሚታጠር በጠየቁ ነዋሪዎች ላይም ዛቻ እና ማስፈራራት ‹‹ቤታችሁንም እንቀማችኋለን›› የሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ሰዎች መሰማቱም አቤት ሊባልበት የታጣበት ሁኔታ ሆኗል። ነዋሪዎች በመንግሥት ላይ አመኔታን እንዲያጡ የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በጎበኘችባቸው አካባቢዎች ያነጋገረቻቸው ሰዎች ታዲያ አሁንም በከፋ ሁኔታ የመሬት ወረራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው አጽንዖት ሰጥተው የሚናገሩት።

ከስምንት ዓመታት በላይ ክፍት መሬት እንደሆነ እና ቤትም እንዳልተሠራበት አዲስ ማለዳ የታዘበችው መሬት ላይ ከሰሞኑ በሰፊው ስለታጠሩት እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጦም እንዳያድሩ በተባሉ መሬቶች ዙሪያ ስለተፈጸሙ ሕገ ወጥ ወረራዎችም ነዋሪዎች ያስረዳሉ። በእርግጥ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ መመልከት እንደቻለችው ከባለ አንድ እስከ ባለ ሦስት ፎቅ ቤቶች በአካባቢው ተገንብተው ሰዎችም እንደሚኖሩበት ለማየት ይቻላል።

ጉታ በቀለ የተባሉ አርሶ አደር ለእርሻ በሚጠቀሙበት ስፍራ ግን እምብዛም ቤቶች አይታዩም። ይሁን እንጂ የሚታረሰው መሬት ለእርሻ የተከለለ መሬት ለመሆኑ ጥርጣሬን የሚያጭር ነው። እነዚህን ስፍራዎች በሚመለከት አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በነበሯት ዕትሞች መጥቀሷ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ስፍራዎች እርምጃ ተወስዶባቸው አካባቢውም ነዋሪዎች ደስታቸውን የገለጹባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በቅርቡ የተገላቢጦሽ እንደሆነ ማየት ተችሏል።

የደስታ ድምጻቸውን ያሰሙት የአካባቢው ነዋሪዎች ከሰሞኑ የከተማዋ አስተዳደር በመሬት ዙሪያ ላለው የኦዲት እና ምዝገባ ጋር በተገናኘ ባወጣው መመሪያ በመመርኮዝ በአንድ አዳር የመኪና መተላለፊያ ብቻ ሲቀር ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በገፍ እንደታጠረ እና ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የመሬት ኦዲት እና መምዝገባው በውስጥ ለውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙትን ስፍራዎች ሕጋዊ ለማድረግ ነው የሚል መረጃዎች መሰራጨታቸው እንደሆነ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ በስፍራው በሬ ጠምደው እርሻ ሲያርሱ የነበሩትን ጉታ በቀለን ከእርሻ መሬታቸው ቀጥሎ በእንጨት ታጥሮ የተከለለው ባዶ መሬት ተመልክታም ጥያቄ አቅርባ ነበር። ‹‹ምን እንደሆነ አላውቅም ግን ይህን መሬት እረስበት ተብዬ ሲሰጠኝ በማግስቱ የተወሰኑ ሰዎች መጥተው አጥረውት ሄዱ›› ሲሉ መልሰዋል።
አዲስ ማለዳ ቅኝቷን ከአርሶ አደሮች ወደ አካባቢው ነዋሪዎች መልሳ ጥያቄዎችን ስታቀርብ ቆይታለች። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ዜና ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደሚናገሩት፣ ስፍራው ከዓመታት በፊት ለቤት መሥሪያነት ለማኅበራት ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት ሠርተው ቀሪዎቹ ደግሞ መሥራት ባለመቻላቸው ክፍት እንደተተወ ይናገራሉ። ይህንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሦስት እና አራት ጊዜ በላይ ወጣት ልጆች በመምጣት አጥረውት እንደነበርና በተደጋጋሚ መንግሥትም እንደሚያስፈርሳቸው አስረድተዋል።

ነዋሪዋ አክለውም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በአካባቢው ቤት ሠርተው ሲገቡ እምብዛም ሰው ያልነበረበት አካባቢ ሲሆን፣ አርሶ አደሮች በርከት ብለው ይኖሩ እንደነበርና ካሳ ተከፍሏቸው መነሳታቸውን ግን መስማታቸውን ያስታውሳሉ። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ እንደተደረገም እንደሚያውቁ ተናግረው፣ ነገር ግን አብዛኞቹ እዛው አካባቢ የጭቃ ቤቶችን ሠርተው መኖር እንደመረጡ ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወረዳ አስተዳደሮች በተቀያየሩ ቁጥር ይህን ስፍራ በተደጋጋሚ እንዲታጠር እንደሚያደርጉ እና ብዙም ሳይቆዩ በተለይም ደግሞ ምክትል ከንቲባው በመሬት ወረራ ዙሪያ በተናገሩ ወቅት እንዲፈርስ ተደርጎ ነበር›› ሲሉ ያስረዳሉ። በሕጋዊ መንገድ ሰዎች ለመኖሪያ ቤት መገንቢያ የተሰጣቸውን ቦታ ነው እየታረሰ የሚገኘው የሚሉት ነዋሪዋ፣ ጥብቅ ክትትል ከመንግሥት በኩል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዘንድሮው የምርት እና የእርሻ ዘመን በአገር ዐቀፍ ደረጃ ምንም አይነት ጾሙን የሚያድር መሬት እንደማይኖር አስታውቀው፤ በባለሀብቶች ተወስደው ወደ ሥራ ባልገቡ መሬቶችም ላይ፣ መሬቶቹ የሚገኙበት ክልል መንግሥት እንዲያርሰው እና ይህም ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ ምርት ዕጥረት መቋቋም የሚቻልበት መንገድ አንዱ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በከተማ አስተዳደሩ ዘንድ በሚነገሩ መረጃዎች መሰረት ከፍተኛ የመሬት ቅርምት እንዳለ እና ይህንም ተከትሎ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣው መመሪያ ቅርምቱን ወደ ሌላ ደረጃ እንዳያሸጋግረው ተፈርቶ ነበር። በወቅቱ አዲስ ማለዳ የታዘበቻቸው የመሬት ቅርምቶች ቢኖሩም እና በተወሰኑት ላይ መንግሥት እርምጃ ቢወስድም፣ ነገር ግን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዙት መሬቶች በእጅጉ መብዛት እንደጀመሩ መታዘብ ችላለች።

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክ ልማት ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ እና ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፤ በመንግሥት ደረጃ ተግባራዊ የሆኑ እና ከዚህ ቀደም በወረራ ተይዘው ነገር ግን በተደረገ ዘመቻ ወደ መሬት ባንክ የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ በጥቅም ትስስር አሁንም ቁጥራቸው የበዙ መሬቶች መሰብሰብ አልተቻለም።

በተለይም ደግሞ በቅርቡ በጠቅላይ ሚነስትሩ በኩል የተላለፈው እና በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ መሬቶችን የማረስ እና ምርት የማምረት እርምጃ ይህን ነገር ለማባባስ ትልቅ አቅም እንደሚኖረው እና ይህ ወቅት ሲያከትም እና መልካሙ ጊዜ ሲመጣ መንግሥት ተጨማሪ ዙር ካሳ ከፍሎ ሊያስነሳቸው እንደሚችል አልሸሸጉም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበጎ እሳቤ በመነሳት ይህን እንቅስቃሴ እንዲጀመር እንዳደረጉት የሚናገሩት የሥራ ኃላፊው፣ ነገር ግን ሊያስከትል በሚችለው ተጽዕኖ ላይ ግን ይህን ያህል ትኩረት የሰጡበት ጉዳይ እንዳልነበር መረዳት ይቻላል ሲሉም ይናገራሉ። አያይዘውም በመንግሥት በኩል በዘመቻ መልክ ሕገ ወጥ መሬቶችን ይዞታ የማስመለስ እና ወደ መሬት ባንክ የማስገባት እንቅስቃሴ ውጤታማነቱ እንደሚያጠራጥራቸው እና በዘመቻ የሚሠራ ሥራ እንዳልሆነም ያስገነዝባሉ።

እንደምክንያት የሚገልጹት ደግሞ ወረራው እጅግ ፈጣን እና በውስብስብ ግንኙነት የሚሠራ በመሆኑ ዘመቻው የአንድ ሰሞን ማስፈራራት እና የማስደንገጥ እንጂ ዘላቂ ለሆነ መፍትሔ የሚጠቀምበት እንዳልሆነም ያስረዳሉ። የሥራ ኃላፊው በቅርቡ በተሰናባቹ ምክትል ከንቲባ ተግባራዊ እንዲሆን የታሰበው የመሬት ኦዲት እና ምዝገባ ጉዳይም ውጤታም እንደማይሆን፣ ይህም መሬት ባለመርገጡ እና ተቋማዊ መዋቅር ውስጥ ባለመግባቱ እንደሆነ በምክንያት አስደግፈው ይናገራሉ።

መንግሥትን ለአላስፈላጊ ወጪ ከሚዳርጉት እና የመንግሥትን ዋነኛ ሀብት ከማሟጠጥ ባለፈ ካዝናን ባዶ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች እንደሚሆኑም ኃላፊው ጠቁመዋል። ‹‹መሬት በዋናነት የመንግሥት ትልቁ ሀብት ነው። ይህን ሀብት መንግሥት በአግባቡ የማይጠቀምበት ከሆነ ትልቅ አገራዊ ቀውስ ውስጥ ነው የሚገባው። ምክንያቱም መንግሥት ትልቁ ገቢው ከመሬት የሚገኘው እንደመሆኑ መጠን ያን ገቢውን በአንድም በሌላም ያጣዋል ማለት ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ያነጋገረቻቸው በቦሌ ለሚ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪ ይህንን ሐሳብ በሚገባ ይጋሩታል። መንግሥት በሌላ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጉዳይ ላይ በተጠመደበት ወቅት ይህን የመሬት ወረራ እየተፈጸመ እና እርሻ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ፣ ቦታውን እንዲለቁ በሚደረግበት ወቅት ድጋሚ ካሳ የሚጠይቁ እና የሚከፈላቸው ከሆነ ብልሹ አሰራሮችን አሁንም መቀረፍ አለመቻላቸው ምልክት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የመሬት ባንክ ልማት ኃላፊው እንደሚሉት፣ በሕጋዊ መንገድ ተይዘው ነገር ግን ረጅም ዓመታት ምንም አይነት ሥራ ሳይሠራባቸው ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ወደ መሬት ባንክ የማስገባት ሂደቱ ባለፈው ዓመት ጀምሮ ሲካሔድ ነበር።

አዲስ ማለዳም በ23ኛ እትሟ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ማውጣቷ ይታወሳል። ለሪል እስቴት ቤት ልማት ተሰጥተው በቤት ፈንታ ዳዋ ሲውጣቸው የኖሩ የከተማዋን ቦታዎች ከ29 የሪል እስቴት አልሚ ኩባንያዎች ለመንጠቅ መወሰኑን ተከትሎ፣ ወደ መሬት ባንክ የገቡት ቦታዎች መጠን ከዚህም እንደሚልቅ እሙን ነው።

ታዲያ በያኔው የለውጡ የለጋነት ዘመን በተደረጉ ግምገማዎች ምክትል ከንቲባው ሲናገሩ አይደፈሩም የተባሉ ቦታዎችን አስተዳደራቸው ሲነጥቅ ከሚኒስትሮችም ጭምር ‹ተው ይቅርባችሁ!› ሲባሉ ነበር። በዚህም የቦታ መንጠቅ ሂደቱ በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች የነበሩበት እንጂ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር በመጠቆም አስተዳደራቸው ይህን በድፍረት በማድረጉ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ይህም በቀደሙት የአስተዳደሩ የበላዮች ያልተሞከረ በመሆኑ ለአዲሱ አስተዳደር አንዱ የጥንካሬ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ከነዋሪዎች በኩልም በርቱ ሊባሉ እንደሚገባ ያምናሉ።

ዳንኤል ሌሬቦ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ዲን ናቸው። ዳንኤል እንደሚሉት ያልለሙ ቦታዎችን ነጠቃው እጅግ የዘገየ ቢሆንም አዲሱ አስተዳደር የወሰደው እርምጃና ቁርጠኝነት ግን ሊደነቅ ይገባዋል። ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት የአንድ ክፍለ ከተማ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ዳንኤል፣ ለልማት ተብለው ከተሰጡ ቦታዎች መካከል ለ20 ዓመታት ያለጠያቂ ታጥረው የነበሩ ቦታዎች በቅርቡ በተወሰደው እርምጃ መነጠቃቸውን በመጥቀስ፣ ትልቅ እምርታ ነው ይላሉ። ግን ደግሞ እርምጃው የዘመቻና የአንድ ወቅት ሥራ ሆኖ እንዳይቀር ይሰጋሉ።

በእርግጥ አስተዳደሩ ሲባክኑ የነበሩ ቦታዎችን ወደ መሬት ባንክ ማስገባቱ ቢደነቅለትም ምንድነው ሊሠራባቸው ያቀደው፣ አሁንስ ምን ላይ ናቸው የሚለው ጥያቄ መልሶ እየተነሳበት ነው። አስተዳደሩ ቦታዎቹን ለምን ለምን ዓይነት ልማት አቅዷቸዋል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የጠየቅናቸው በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ጥላሁን፣ ጥያቄውን በበርካታ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች በየቀኑ እየተጠየቁ ስለመሆኑ በመግለፅ የተለየ ዕቅድ እንደሌለ ተናግረዋል።

ይህም ማለት አስተዳደሩ ቦታዎቹን የነጠቀው አቅዶ አይደለም ማለት ነው። ቦታዎቹን ወደ መሬት ባንክ ከማስገባት ባሻገር ምን ይሠራባቸዋል የሚለውን እስከ አሁን የወጣ ዕቅድ የለም ወይ ለሚለው ጥያቄም ተስፋዬ ‹‹አዎን›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። እንዴትና በምን ምክንያት ነው አስተዳደሩ ረጅም ዓመታትን ያለ ጥቅም የቆዩ ቦታዎችን ወደ ልማትና ጥቅም ለመመለስ ዕቅድ የማያወጣው የሚለውን ጥያቄ ብናስከትልም፣ ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በላይ ምላሽ ሊሰጡ አልፈቀዱም።

የአዲስ አበባ የቀድሞ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ወደ መሬት ባንክ ከገቡ ከዓመት በላይ ስለሆናቸው ቦታዎች ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ አስተደደሩ ከመንጠቅ ባለፈ ቦታዎቹን አሁንም ወደ ምጣኔ ሀብት ማስገባት አለመቻሉን ገልጸዋል። ይህ ታዲያ በኹሉም ሥራ ኃላፊዎች ዘንድ የሚነሳ ቅሬታ ነው። አዲስ ማለዳ ይህን ጽሑፍ በምታዘጋጅበት ወቅት ያናገረቻቸው በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንኑ ይጋራሉ።

የከተማ ልማትና ምህንድስና ምሁሩ ዳንኤል ‹‹የከተማ ሀብት እጅግ ውስን የሆነው መሬት ነው›› ካሉ በኋላ፣ ይህን ውስን ሀብት በጠንካራ ሕግና ቁጥጥር ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። ከዚህ ቀደም አንድም ለቦታዎች ረጅም ጊዜ ታጥሮ መቆየት ምክንያቱ የመሬት ዘርፍ ባለሙያዎች ከባለሀብቶች ጋር የሚኖራቸው አላስፈላጊ (የጥቅም) ግንኙነት ነውም ይላሉ።

ዋናው ግን በከተማዋ ከማእከል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ፍፁም መናበብ አለመኖር ነው። ለልማት የሚተላለፉ ቦታዎችን ውል መነሻ በማድረግ ‹መቼ ይለማሉ? እስከመቼስ ተጠናቅቀው ለተፈለገው አገልግሎት ይውላሉ?› የሚለውን የተግባር ዕቅድ (action plan) አውጥቶ ከከንቲባ እስከ ወረዳ አመራር በጥብቅ መናበብ ከመከታተል ይልቅ ውልን መደርደሪያ (ሼልፍ) ላይ ሰቅሎ ነገር ዓለሙን የመርሳት አባዜ ቦታዎቹን ለረጅም ዓመት ከልማት ውጭ ስለማድረጉ በማንሳትም ይህ ልማድ ሊታረም እንደሚገባው ዳንኤል አፅንዖት ይሰጣሉ።

በመሬት በኩልስ ቢሆን የመንግሥት ወሳኝ እና ትልቁ ሀብቱ እንደመሆኑ መጠን በዝምድናም ሆነ በትውውቅ የሚደረጉ ሸፍጦች የኋላ ኋላ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ እንደ አገር እንደሚያስከፍል የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪው ሙሉቀን ሀብቱ ይናገራሉ። አገር እኩል የገቢ ክፍፍል እንዲኖራት ማድረግ የሕዝብን ሰላም እና በመንግሥት ላይ የሚኖረውን አመኔታ እንደሚጨምር የሚናገሩት ሙሉቀን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የሕገ ወጥ መሬት ወረራ ጉዳይ ግን አሁንም ቢሆን ሳይረፍድ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ሲሉ ይናገራሉ።

አዲሲቷ ከንቲባ ተስፋ ወይስ ስጋት?
በአንጻራዊነት ረጅም ጊዜያት በአንድ የኃላፊነት ስፍራ ላይ የቆዩት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ዑማ ከሰሞኑ መነሳታቸው ይታወሳል። እርሳቸውንም መነሳት ተከትሎ ከለውጡ በፊት በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ከንቲባ በመሆን ያገለገሉ፤ በኋላ ከለውጡ መምጣት ጋር ተያይዞም ወደ ፌደራል ቢሮዎች በመምጣት የገቢዎች ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉ እንዲሁም ለአጭር ጊዜያትም ቢሆን ብርሀኑ ጸጋዬን በመተካት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን የሠሩት ብርቱ ሴት ናቸው የሚባልላቸው አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ለመምራት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

አዳነች አቤቤ በአዳማ ከተማ ከንቲባነት ዘመናቸው እጅግ በርካታ ታሪካዊ ሥራዎችን በመሥራት እና የሕግ በላይነትንም በማስከበር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። ከዚህም በተጓዳኝ ደግሞ አዳማ ከተማን በ20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሶደሬ መዝናኛ ማዕከል ጋር በማገናኘት ሰፊ እና አስደናቂ ሥራ ለመሥራትም በሒደት ላይ እንደነበሩም ምንጮች ይናገራሉ።

ወደ ፌዴራል ከመጡ በኋላም ቢሆን ውጥንቅጡ ወጣውን የግብር አሰባሰብ በማስተካከል እና ሰፊ ሥራዎችን በመሥራት የሚመሰገን የግብር መጠን እንዲሰበሰብ መቻሉም የሚታወስ እና ኅብረተሰቡም በግልጽ ያየው ጉዳይ እንደሆነ የሚታወስ ነው።

አዳነች አቤቤ ይህን ያህል ቆይተውበታል ባይባል እንኳን በጠቅላይ አቃቤ ሕግነት በቆዩበት ጊዜያት በአገሪቱ የሕግ ስርኣት ላይ የማይናቅ ሥራን እንደሠሩም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች ይናገራሉ። አያይዘውም አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት ከፍተኛ የሆሥ ውጤታማ ሥራን በመሥራት የሚስተካከላቸው እንደሌለ እና ከዓላማ ጽናታቸው ጋር ተዳምሮ የሥራ ባህላቸው የሚያስቀና ትጉህ እንደነበሩም በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ውስጥ የሚሠሩ ባልደረቦቻቸው ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።
አዲስ ማለዳ ምልከታ ባደረገችባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ግለሰቦች በአዲሷ ከንቲባ ዙሪያ የተለያየ ስሜት እንዳላቸው ይናገራሉ።

‹‹አዲሷ ከንቲባ ካላቸው ልምድ እና ከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም የተነሳ አዲስ አበባን በሚገባ ያስተዳድራሉ የሚል ግምት አለኝ›› ሲሉ ይጀምራሉ። አያይዘውም በተሰናባቹ ከንቲባ አስተዳደር ዘመን የተፈጠሩ አስቸጋሪ ጉዳዮችን ለማጥራት ከፍተኛ የሆነ ሥራ ቢጠበቅባቸውም አቅም ያንሳቸዋል የሚል ጥርጣሬ እንደማይገባቸውም ይናገራሉ።

‹‹በዋናት ግን በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን እንደሚያስቆሙልን ከፍተኛ የሆነ ተስፋ አለኝ›› የሚሉት ዜና፣ በተለይ ደግሞ በተደጋጋሚ እየፈረሰ በድጋሚ ለሚታጠረው የመኖሪያ መንደሮች አረንጓዴ ስፍራዎች መላ የሚበጅለት ጊዜ እንደሚሆንም ባለ ሙሉ ተስፋ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። በገቢዎች ሚኒስቴር ውስጥ የነበራቸውን ከፍተኛ ሥራ አፈጻጸም በአንክሮ ይከታተሉ የነበሩት ዜና፣ በአዳማ ከተማም የነበራቸውን የሥራ ተነሳሽነት በዝና መስማታቸው ለዚህ ለሞላው ተስፋቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰላ ትችት በአዲስ አበባ አዲሷ ከንቲባ ላይ የሚሰነዝሩት አስተያየት ሰጪ፤ ‹‹በአዳነች የሥራ ችሎታ ምንም አልጠራጠርም፤ የሚመጡ ለውጦችም መኖራቸው አይቀሬ ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም ነገር ግን አዲስ አበባ ጉዳይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያሻው እና ከባድ አገራዊ ትኩረትን የሚስብ ውስብስብ ችግሮች ባለቤት የሆነች ከተማ በመሆኗ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንደማይመጣ ከወዲሁ ሊታወቅ እንደሚገባ ይናገራሉ።

‹‹አዲስ አበባ የመሬት ቅርምት በዋናነት የሚነሳ እና ሊነሱ ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ትንሹ ነው። ምክንያቱም ቀላል እርምጃ የሚወሰድበት እና ቁርጠኝነት ካለ ሊፈታ የሚችል የአስተዳደራዊ እና ሕጋዊ ጉዳዮች ጥምረት የሚፈታው ችግር ነው። አንድ ሰው መሬት ያለ አግባብ ከያዘ ሕጋዊ አይደለህም ተብሎ እርምጃ ሊወሰድበት ከፍ ሲልም በሕግ ሊጠየቅበት የሚችል ጉዳይ ነው›› ይላሉ።

በዋናነት ግን አዲስ አበባ ውክልና ጉዳይን እና ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት እና የጥቅማ ጥቅም ክፍፍልን በሚመለከት ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ሊፈቱ የማይችሉ አዳጋች ሐሳቦች ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ስለሚኖሩ አዳነች አቤቤ ምንም እንኳን ጥንካሬያቸው ቢታወቅም ቅሉ፣ እነዚህን መፍታት ግን እንዲህ በቀላል ይሆንላቸዋል የሚባል እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በታዘበችው አካባቢዎች በተለይም ከሹመቱ ማግስት ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ በኹለት አቅጣጫ ሲካሔድም ነበር። በዚህም መሰረት የመሬት ወረራው በአስቸኳይ ይቁም የሚል ትዕዛዝ የተሰጠ በሚመስል አኳኋን በረጃጅም እንጨቶች ታጥረተው የነበሩ የመንደር ውስጥ ክፍት ቦታዎች በአንድ አዳር ሲፈራርሱ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ታጥረው የማያውቁ መሬቶች ከእንጨትም በተጨማሪ በቆርቆሮዎች እንዲታጠሩ ሲደረጉም ለማየት ተችሏል።

አሁንም አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የተስፋ እና ስጋት ሁኔታ ለመታዘብ የቻለች ቢሆንም ፍርዱን ለጊዜ ትተዋለች። በእርግጥ ከፊት ለፊት የሚመጣው አዲሱ ዓመት በከተማዋ እና በነዋሪዎቿ ላይ ከፍተኛ ሆነ መነቃቃት እንዲሁም ሕዝብ እና መንግሥት በቅርበት ተነጋግረው እና ተማምነው የሚኖሩበት ይሆን ወይስ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ጥቂቶች ብቻ በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ እየመዘበሩ ሌሎች የበይ ተመልካች የሚሆኑባት አዲስ አበባ ትሆን? የሚለው ጉዳይ ጊዜ ፈራጅ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ተደራጅተው ከመንግሥት ብድር በመውሰድ ብረታ ብረት ሥራ የሚያከናውኑ የወዳጅነት ለሥራ ማኅበር አባላት ለአዲስ ማለዳ ስለ አዲሷ ከንቲባ ሲናገሩ፤ ‹‹እኛ ተጠቃሚ ሆነናል። አሁንም ሕግ በሚፈቅድልን መልኩ እየተመራን ከመንግሥት በሚሰጠን ድጋፍ ለማደግ እንሠራለን። ከዚህ በፊት እኛ ተጠቃሚዎች ብንሆንም በርካታ ተስፋ የሚያስቆርጡ ጉዳዮች ነበሩብን።

ነገር ግን ይህ ከከንቲባው ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አልነበረም። ምክንያቱም ከንቲባው በእያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ እየገባ እንዲያገለግል መጠበቅ የለብንም። ነገር ግን በየወረዳው የተቀመጡት ሥራ ኃላፊዎች ወገንተኝነታቸው በግልጽ የሚታይ ነበር። አሁንም ይህ ጉዳይን በሚመለከት ከአዳነች አቤቤ ዘንድ መሻሻልን እንጠብቃለን›› ሲሉ ይናገራሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here