ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ይገነባል የተባለው የመኖርያ ቤት አልተገነባም

0
682

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላቶች አራት ቢሊዮን ብር የሚፈጅ የመኖርያ ቤት ሊገነባ መሆኑ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉ ተገለጸ።

የከተማው ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለኮንዶሚኒየሙ ግምባታ የቤት ዲዛይን እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች እንደተጠናቀቁ ባለፈው ዓመት በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው የሚታወስ ቢሆንም፤ እስከ አሁን ድረስ ግን ምንም አይነት ግንባታ እየተከናወነ እንዳልሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከዛም በተጨማሪም መኖርያ ቤቶቹ በሰባት የተለያዩ ቦታዎች የሚገነቡ ሲሆን ከአምስት አስከ አስር ፎቅ እንደሚሆኑ ተገልፆ ነበር፤ ጌቱ አርጋው እንደተናገሩት ከሆነ የከተማው አስተዳድር ለግምባታው የሚሆን በጀት እንደመደበ እና ግምባታው ከሶስት አመት በላይ እንደሚፈጅ አንስተው ነበር። ከዛም በተጨማሪ እንዳነሱት ከሆነ ‹‹እንዲህ ያለ ስራ ፖሊስ በተረጋጋ መልኩ ስራውን እንዲሰራ ያግዘዋል›› ሲሉም ኮሚሽነር ጌቱ መናገራቸው ይታወሳል።

በተያዘም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ በወቅቱ ከ19 ሺህ 300 በላይ አባላቶች መኖራቸውን ገልጸው የነበሩት ጌቱ ከመኖርያ ቤቶች በተጨማሪ የከተማው አስተዳደር ዘመናዊ እና ብቁ የሆኑ ፓሊስ ለማሰልጠን የሚረዳ ለአዲስ አበባ ከተማ የፖሊስ ኮሌጅ ይገነባል ብለው አንስተው ነበር።

ይህን ጉዳይ በሚመለከትም ከአንድ አመት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት ጌቱ አረርጋው በሰጡት መግለጫ ላይ ለአዲስ አበባ ፖሊስ አአባላ የመኖርያ ቤት ይገነባል ማለታቸውን ተከትሎ፤ አስከሁን ምንም አይነት ቤት እንዳልተጀመረ እና መረጃውም እንደሌለው የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

እስካሁን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊሶች የሚገነባ ቤት እንዳለ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ እና እንቅስቃሴም አለመኖሩን የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ተናግሯል። ምናልባት ተገልፆ ቢሆን ኖሮ በእቅዳችን ይካተት ነበር በማለት የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙኘት ክብሮም ለአዲስ ማለዳ አንስተዋል።
በተጨማሪነት ተቋሙ ይሄን ለማስፈጸም ተብሎ የተቋቋመ ሳይሆን ፤ ህጉን ተከትሎ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍልን እኩል በህጉ መሰረት ለማገልገል የተቋቋመ ነው ሲሉ የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም የኤጀንሲው ዋና ስራ ከማቋቋሚያ አዋጁ ተጨማሪ መንግስት የሚሰጠውን ስራ ይሰራል ማለት ይሆናል እንጂ ፤ ይሄ በዋናነት እኛን አይመለከትም ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል። የሕግ ስርአቱን ተከትልን ከተለያዩ ክልሎች የህዝብ ተወካዮች ይመጣሉ ፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለ ስልጣናትም ይመጣሉ ፤ ስለዚህም ለእነርሱ መቀመጫ የሚሆኑ የተስተካከሉ መንግስት የኪራይ ቤቶችን ማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የነበሩትን ነባር ቤቶቻችንንም (ማስተዳደር) መቆጣጠር ነው እየሰራን ያለነው ብለዋል።

የህዝብ ግንኙነቱ እንደሚሉት ቅርብ ጊዜ ወደ ኮርፖሬሽንነት እንደ መሸጋገራችን(3 ዓመት) የአቅም ማዳብር ከተደረገ በኋላ ለመንግስት ሰራተኞች የሚከራይ ቤቶችን ለማቅረብ በዕቅድ መያዛቸውን ጨምረው ተናግረዋል።ለሌላው ህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ህንጻዎች ሲገነቡ ከታች ያሉ ህንፃዎች ለንግድ ተቋማት ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ መታሰቡንም ጠቁመዋል። በማለት የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ኢኒስፔክተር ማርቆስ እንዳነሱት ከሆነ ለፖሊስ አባላቶች መኖርያ ቤቶች መገንባት እና የፖሊስ ማስልጠኛ ይገነባል ስለመባሉ እንደማያውቁ እና ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንደማያውቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here