“የጸጥታ ኃይሉ የመምረጥ መብቴን የሚያደናቅፍ ኃይል ከመጣ የሕይወት መስዋዕትነት እከፍላለሁ የሚል መልዕክት አስተላፏል” ጌታቸው ረዳ

0
517

የትግራይ ክልል በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ የራሱን ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ እየሰራ ነው፡፡ ክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ያስቀመጠው ቀነ ቀጠሮ መዳረሱን ተከትሎ የፌደሬሽን ምክር ቤት ትግራይ ክልል በክልል ደረጃ ምርጫ አደርጋለሁ የሚለውን አቋሙን እንዲቀይርና ካልሆነ እርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁን ተከትሎ በማዕከላዊ መንግስቱና በትግራይ ክልል ገዥ ሕወሓት መካከል የቃላት ጦረትነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

አዲስ ማለዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገረቻቸው የሕወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል ጌታቸው ረዳ “ምርጫ እናካሂዳለን ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የጸጥታ ኃይሉ የመምረጥ መብቴን የሚያደናቅፍ ኃይል ከመጣ የሕይወት መስዋዕትነት እከፍላለሁ የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፈው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በፌደራል መንግስት በኩል የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው በመጥቀስ ምርጫ ማካሄዱን ካላቆመ እርምጃ እወስዳለው ያለውን ውሳኔ ማስተካከል ካለበት ማስተካከል ያለበት የፌደራል መንግስቱ እንጅ የትግራይ ክልል አይደለም ሲሉ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የሕወሓት ስራ አስፈጻሚ አባሉ ጌታቸው አክለውም “ትግራይ ምርጫ ያካሂዳል፣ ትግራይ ምርጫ እንደሚያካሂድ የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ድሮም የትግራይን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስከበር የታገሉ ናቸው፣ አሁንም የታገልነትን ነፃነት ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ነው ያሉት፡፡”ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ክልል የተደረገው ወታደራዊ ትዕይንት የመምረጥ መብታችንን የሚያደናቅፍ ኃይል ለመመከት እንጅ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ግጠሙኝ የሚል መልዕክት የለውም ብለዋል፡፡

“በትግራይ በኩል ጦርነት የማድረግ ፍላጎት የለም፡፡ ይሄ ሁሉ ጥረት የተደረገው ጦርነትን ለማስቀረት ነው፡፡ ከጦርነት ስለሽሸህ ግን ጦርነት አይጠፋም፡፡ በተቻለ መጠን ግን ጦርነትን ለማስቀረት ሁላችንም ጥረት ማደረግ አለብን፡፡” ሲሉ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ ችግር ከሕወሓትና ከብልጽግና በላይ ነው ያሉት ጌታቸው “ሕወሓትና ብልጽግና ከአቅማቸው በላይ የሆነን የአገር ችግር እኛ የፈጠርነው ነው ብለው ቢታረቁ የስልጣን እርቅ ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡ ጌታቸው አክለውም “ሕወሓትና ብልጽግና ቢታረቁም አትንካኝ አልንካህም ነው የሚሆነው እንጅ በምንም መልኩ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር አይፈታም፣ ምናልባት የተወሰንን ሰዎችን የስልጣን ተጋሪ ሊያደርገን የሚችል ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር በዘላቂነት አይፈታም” ሲሉ አብራርዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሕወሓትንና የብልጽግናን ልዩነት ለመፍታት ወደ ትግራይ ክልል ያቀኑ የአገር ሽማግሌዎች የተመለሱበትን ምክንያት ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ ሽማግሌዎቹ የመቀራረቢያ ሀሳብ ከሕወሓትና ከብልጽግና በላይ ሌሎች የአገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያካተተ እና ብሔራዊ ውይይት መሆን አለበት የሚል እምነት በሕወሓት በኩል በመኖሩ እና ያን ማድረግ በወቅቱ ባለመቻሉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ሕወሓት ወደፊትም ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ብቻውን የሚወያይበትና የሚደራደርበት ጉዳይ እንደማይኖር ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡ እንደ ጌታቸው ገለጻ በሕወሓት በኩል ብሔራዊ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች ያካተተ ውይይት ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑን ለአገር ሽማግሌዎች አስረድቷል ብለዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ከብልጽግና በኩል ምላሽ ለማግኘትና የብልጽግናን ሀሳብ ለማካተት ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች እስከ መጨረሻው ስዓት በተደጋጋሚ ብትሞክርም ምላሻቸውን ማግኘት አልቻለችም፡፡

6ኛው ዙር የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫ ለማካሄድ ውሳኔ አሳልፎ ክልላዊ ምርጫ ኮሚሽን በማቋቋምና አዲስ የምርጫ ህግ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የምርጫ ስርዓት አብላጫ ድምጽ ያገኘ ድርጅት መንበረ ስልጣኑን የሚረከብ ሲሆን፡፡ ትግራይ በቀጣይ በምታካሂደው ክልላዊ ምርጫ አዲስ ቅይጥ የምርጫ ስርዓት ለማካሄድ ተወስኗል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here