በአውሮፓ የ‘ቄሮ’ ኤምባሲ ወረራ

0
722

በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በየሳምንቱ የፖለቲካ ቱማታው ከፍና ዝቅ፣ ጠበቅና ላላ፣ ሞቅና ቀዝቀዝ በማለት ፈጣን ተለዋዋጭ ባህሪውን ለመከታተል ትዕግስትን ይፈትናል። ሰሞነኛ መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፥ ባህር ማዶ ተሸግሮ በአውሮፓ ኹለት ከተሞች ላይ በተለየ መልኩ የተገለጸው አንዱ ነው።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝ ንግሥት ኤልሳቤጥ መናገሻ፣ በዓለም የንግድ ማዕከሏና እምብርት ሎንደን በሰላሳዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ በርግጥ አንዳንዶች ቄሮ ይሏቸዋል፥ አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ላይ ድብደባ በመፈጸም የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ ኤምባሲውንም በመውረር ሕጋዊውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከሚውለበለብበት ዘንግ ላይ አውርደው በመጣል የኦነግን አርማ ዘቅዝቀው አውለብልበዋል፤ በኹከትንና ግርግርነ ምክንያት መዘቅዘቁን ልብ ያሉ ግን አይመስልም።

የሰልፈኞቹ ዓላማ ነፍጠኛ የሚሉትን የኢትዮጵያን መንግሥት መቃወም፤ በሚያራምዱት የፖለቲካ መስመር ሰበብ ታሰሩብን የሚሏቸውን ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሌሎች እስረኞችን ለማስፈታት ያለመ እንደሆነ ከዘገባዎች መረዳት ይቻላል። ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ፍጥጫና ግብግብ፣ ጥቃትና ሕገወጥ እንቅስቃሴ 12ቱ ለእስር ተዳርገዋል፤ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ታውቋል።

በማኅበራዊ ትስስርም ሆነ በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን ድርጊቱ ትኩረት መሳቡን ተከትሎ በርካቶች ግራ በመጋባት ምን እየተደረገ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፤ እቅጩን የሚነግራቸው ባያገኙም። አንዳንዶች ፖለቲካችን አገሩ ጠቦት፣ ብጥብጥና ኹከትና ግርግር በአውሮፓ ከተሞች ሊደገም ይሆን በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሌሎች ደግሞ “መሳለቂያ ተደረግን” በሚል ቁጭት ተብሰልስለዋል፤ ድርጊቱ መረን የለቀቀ እጅግ አሳፋሪ ነው ያሉም አሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የእንግሊዝ አቻውን ቸልተኛ ሲል ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂው ፖሊስ ነው በማለት ወቅሷል። የአገር ተቆርቋሪ ዜጎች ማንኛውም መንግሥት በአገሩ የሚገኙትን ዲፕሎማቶች ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት ሲሉ የ1949ኙን (እ.አ.አ) የጄኔቫ ስምምነትን ለክርክራቸው ማጣቀሻ አድርገውታል። በርግጥ አዲስ አበባ የሚገኙት የታላቋ ብሪታኒያ አምባሳደር በመንግሥታቸው ሥም ይቅርታ ይጠይቃል፤ ወንጀለኞችን ለሕግ እናቀርባለን ሲሉም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ታዋቂ ከሆኑት ፖለቲከኞች መካከል የኦሮሚያ ብልጽግና ቃል አቀባይ ታዬ ደንደአ፥ በፌስ ቡክ ገጻቸው “ኦነግና ባንዲራው: የባከኑ እሴቶች!” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሁፍ ድርጊቱን በጠንካራ ቃላት አውግዘዋል። የሕወሓት ረጅም የሴራ እጅ እንዳለበት በመጥቀስ “ሕወሓት በከንቱ ይለፋል! ውሃ የወሰደው አረፋ ይጨብጣል” ሲሉ ሸንቆጥ አድርገውታል።

ይህ የሎንደኑ ዜና ቋንጣ ሳይሆን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ በሌላዋኛዋ አውሮፓዊት አገር ሆላንድ የዲፕሎማሲ ከተማ ዘሔግ፥ ቁጥራቸው በኻያዎች የሚቆጠር የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች የኢትዮጵያ ኤምባሲ በር ላይ “የኢትዮጵያ መንግሥት አይወክለንም!” “ችግራችን ከነፍጠኛ ጋር ነው!” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋ።

ይሁንና ፈቃድ ያልተሰጠው ሕገ ወጥ ሰልፍ ነው በሚል በከተማው ከንቲባ የተላለፈ ነው በተባለ ትዕዛዝ ፖሊሶች ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን እንዲበተኑ ቢጠይቁም፥ የሰልፈኞቹን እሺታ ባለማግኘታቸው 19ኙ ለእስራት ተዳርገዋል። ሕግ በመተላለፍም እያንዳንዳቸው 600 ዩሮ እንዲከፍሉ ቅጣት እንደተጣለባቸው ተሰምቷል።

ዘግየት ብሎ በወጣ መረጃ፥ ብዙዎቹ የታሰሩት ሰልፈኞች የመኖሪያ ፈቃድ ማመልከቻቸውን ለማፋጠን ሲሉ በተቃውሞው ሰልፍ ላይ የመሳተፋቸውን ትክክለኛ ምክንያት መግለጻቸው ተዘግቧል። ይህንን የሰሙ አንዳንዶች በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ‘የጦስ ዶሮዎች’ ሲሉ ተሳልቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት ከፍለው ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ እስረኞቹ በከባድ ማስጠንቀቂያ ከአንድ ቀን የእስር ቤት አዳር በኋላ መፈታታቸው ታውቋል።
በርግጥ የሰሞኑ የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የአውሮፓ ከተሞች እንቅስቃሴ የብዙዎች ትኩረት የሳበ ከመሆኑም ባሻገር ለተለያዩ አስተያየቶች መንጸባረቅ ሰበብ ሆኗል። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የተካሄደውን እልቂትና ውድመት በአውሮፓ እንዳይደገም ሲሉ የምር ይሁን የቀልድ ስጋታተቸውን አንጸባርቀዋል። ሌሎች ደግሞ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ለማዳካም የዐቢይ መንግሥት የሄደበት ርቀት አፈናን በማንበሩ፥ ንዴትና ቁጭታቸውን እንዲሁም በአገር ፀጥ እንዲሉ ለተደረጉ የኦሮሞ ብሔርተኞች ድምጽ ለመሆን በዚህ መልክ መንቀሳቀሳቸው አላስገረማቸውም።

የሆነው ሆኖ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድንበር ሳያግደው አውሮፓና አሜሪካ ተሻግሮ በስደት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል ልክ በሕወሓት ዘመን እንደነበረው ዓይነት ጠንካራ ተቃውሞና ሥር የሰደደ መከፋፈል ለመቀጠሉ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here