ግብረ ሰዶም???

0
3571

በርካታ አከራካሪ ነጥቦችን ከማስነሳት አልፎ ከፍ ሲል ውግዘትንም የሚያስከትል ጉዳይ ነው፤ የግብረ ሰዶማዊነት ጉዳይ። ከ192 አገራት ውስጥ በ28 አገራት ዘንድ በመብት ደረጃ የሚከበር ሲሆን በቀሪዎች የዓለም አገራት ዘንድ ደግሞ አሁንም ድረስ በሕግ እውቅና ያልተሰጠው እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። እስከ 1970 ድረስ በተለያዩ ሕክምና ማኅበራት ግብረሰዶማዊነት የአዕምሮ መዛባት በመባል እንደ በሽታ ይቆጠር እንደ ነበረም መዛግብት ያስረዳሉ።

በበርካታ አገራት እየተኮነነና እየተወገዘም ከሕግ እውቅና ውጪ እየተፈጸመ ይገኛል። በአንጻሩ በአሁኑ ወቅት ይህ ጉዳይ በአንዳንድ አገራት መደበኛ የኑሮ ዘዬ እየሆነ፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከተመሳሳይ ጾታም ጋር ቢደረግ ፍጹም ጤናማ ነው ወደሚል ድምዳሜ የተደረሰ ይመስላል። አብዛኞች አስተያየት ሰጪዎች ታድያ ይህ ጉዳይ እየበዛ ከመጣው የተመሳሳይ ጾታ ማኅበረሰብ ምክንያት በመሆን የተጽዕኖ ማሳደር እንቅስቃሴው አንዱ ተግባር ነው ይላሉ። የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በጉዳዩ ላይ ዓለም አቀፍ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማገላበጥና እና ባለሙያዎችን በማናገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ግብረ ሰዶም የተመሳሳይ ጾታ ጾታዊ ግንኙነት በኢትዮጵያ የሚጠራበት ሥሙ ነው። ግብረ ሰዶም የሰዶም ሥራ የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን፣ ሰዶም ይባል በነበረ ስፍራ የተመሳሳይ ጾታ ጾታዊ ግንኙነቶች በመኖራቸውና አምላክ በመቆጣቱ ሰዶምን ጨምሮ አምስት ከተሞች እንደጠፉ ይታመናል። ሰዶም የተባለችው ከተማም በዚህ ትታወቅ ነበር።

ኤልያን የአዲስ ማለዳ ባለታሪክ ነው። በ6 ዓመቱ በሚኖርበት በሐዋሳ ከተማ የተደፈረውና ለ32 ዓመታት በዚህ ሕይወት የቆየው ኤልያና፣ በዚሁ የብዕር ሥሙ ‹የሰዶም ነፍሳት› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ጽፎ ለአንባብያን አድርሷል። ወንደኛ አዳሪም ሆኖ እንደሠራ የሚያወሳው ኤልያና፣ ‹‹አሰቃቂ የወሲብ ሕይወት ውስጥ አሳልፈናል።›› ሲልም ያለፈ ሕይወቱን ያስታውሳል።

ከዛ ሕይወት ለመውጣትም ምን ያህል ከባድና በፈተና የተመላ እንደሆነ ለማስረዳት ‹ማግኔት ነው› ሲል ይናገራል። መሸፋፈኑንና ዝም መባሉንም አብዝቶ ይቃወማል። በአንጻሩ ግን ለመገናኛ ብዙኀን ክፍት ሆኖ አስተያየት ለመስጠት ፈተናው ከባድ ሳይሆንበት አልቀረም። እርሱም ሆነ ጓደኞቹ በግልጽ ከመናገር የተረፋቸው መገለልና ስድብ በመሆኑ፣ ለመገናኛ ብዙኀን ፊት ለፊት ወጥቶ መናገሩን ለጊዜው እንደገታም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ታድያ በወንደኛ አዳሪነት ሥራው እንደታዘበው ባለትዳር የሆኑ ወንዶችም ወደ እነርሱ ይሄዱ እንደነበር ነው። ‹‹በማኅበረሰብ ላለመገለል ወልደው በዚህ በኩል ግን እኛ ጋር እየመጡ ሕይወታቸውን በዚህ የሚያሳልፉ አሉ። በተለይ ተደፍረው ወደዚህ ሕይወት እንዲገቡ የተገደዱ ብዙ ናቸው።›› ሲል በቅርበት ሊታዘብ ከቻለው ይጠቅሳል።

በተመሳሳይ ሕይወት ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ የቆየው ሌላው ባለታሪክ አጠለል ይባላል። ‹ሴት› ሆኖ ስምንት ጊዜ አግብቶ እንደፈታም ያወሳል። የ8 ዓመት ልጅ ሆኖ በቅርብ ቤተሰብ መደፈሩን አንስቶ፣ ያም ወደዚህ ሕይወት እንዳስገባው ይገልጻል። ‹‹በመንግሥት ደረጃ ፈቃድ አላገኘም እንጂ እንቅስቃሴው ግን አለ›› ሲልም በተመሳሳይ ሕይወት ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይጠቅሳል።

እርሱም በበኩሉ ተሸፋፍኖ መደባበቁ ጭራሽ እንዲስፋፋ አድርጓል ባይ ነው። ‹‹ማግለልና መስደብ ተገቢ አይደለም። ዛሬ ሲሰደቡ ነገ የሚበቀሉ አሉ። በቀላቸው የከፋ ነውና የሚሆነው ትምህርት አዘል በሆነ መንገድ ማስረዳት ተገቢ ነው።›› ሲልም ከኖረበት በመነሳት ሐሳቡን አካፍሏል።

ጥቅምት 15 የወጣው የአዲስ ማለዳ 51ኛ እትም ላይ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ቆጬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የደረሰን አንድ አስገድዶ መድፈር በሚመለከት መዘገቧ ይታወሳል። ጥቃቱን ያደረሰው ፖሊስ ሲሆን እድሜው 15 ዓመት የሚጠጋ የጎዳና ተዳዳሪን ከእንቅልፉ ቀስቅሶ ‹‹እስረኛ ነህ፣ ላስርህ ነው›› በማለት ቢሮው ወስዶ በገጀራ በማስፈራራት አስገድዶ የደረፈ ሲሆን፣ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንደተቀጣ የክስ መዝገቡ ያስረዳል።

መጋቢት 3 ቀን 2011 ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ድርጊቱ የተፈጸመ ሲሆን፣ ጥቃቱ የደረሰበት ልጅ ለፍርድ ቤት በሰጠው ቃል መሠረት፣ ልብሱን እንዲያወልቅና የሚታሰረውም እርቃኑን እንደሆነ ገልጾ በገጀራ ጭምር እንዳስፈራራውም ተናግሯል። የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 13 ቀን 2012 በዋለው ችሎት፤ ተከሳሽ በፈጸመው ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን፤ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ቸላለች፤ ጉዳዩንም ዘግባለች።

ታድያ እንዲህ ያለ ወንጀል በየጊዜው ሲፈጸም መሰማቱና መፈጸሙ አንድም መረጃው በስፋት ካለመናገር የመጣ እንደሆነ ነው ብዙዎች የሚናገሩት። አልፎም በዚህ መልክ ጥቃት ለደረሰባቸው ልጆችና ወጣቶች የሥነልቦና ምክር መስጠት ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ ያንን ለማድረግ ትኩረት አለመሰጠቱም ሆነ አቅም አለመኖሩ፣ በተመሳሰይ ተግባር ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችን አሃዝ ከፍ ያደርጋል።

ሰዎች ምን ይላሉ?
በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው እና አሁንም ቢሆን የጋራ መግባባት ላይ ያልተደረሰበት እንዲሁም አንድ ሳይንሳዊ መፍትሔ ያልተበጀለት ማኅበራዊ ጉዳይ ነው ይሉታል፣ በርካቶች ስለ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወይም ግብረሰዶማዊነት አስተያየታቸውን ሲሰጡ። ይህ ጉዳይ ታዲያ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ ዘመናትን ተሻግሮ ያለንበት ዘመን ላይ ደርሷል። ይህ በአንድ ድምጽ መግባባት ላይ መድረስ ያልተቻለበት ጉዳይን በሚመለከትም ለሚጠየቁ ጥያቄዎች የተለያዩ እና ጽንፍ ረግጠው የቆሙ ምላሾች ሲሰነዘሩም ይስተዋላል።

የጥያቄዎችም መሰረት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በኢትዮጵያ እንደ አብዛኛው የሕብረተሰብ አጠራር ግብረሰዶማዊነት በእርግጥ በተፈጥሮ የሚፈጠር ጉዳይ ነው ወይስ ደግሞ ሰዎች በምርጫቸው የሚገቡበት? በተለይም በራሳቸው ውሳኔ የሚገቡበት ሕይወት ነው ከሚለው አንጻር በአብዛኛው የሰው ልጅ ዘንድ የሚታየውና በተፈጥሮም ነው ተብሎ ከሚታመነው የሴት እና የወንድ ግንኙነት በተቃራኒ ወንድ እና ወንድ ወይም ሴት እና ሴት ግንኙነትን መርጠው ነው ወይ የሚለውን ያመላክታል። በእርግጥ በዚህ ዕትም አዲስ ማለዳ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ጉዳይ ለአብነት አነሳች እንጂ የጾታ መቀየርን እና ባለ ኹለት ጾታዎችን በሚመለከትም ሰፋ ያለ ዳሰሳ ማድረግ ይቻል ነበር።

ለመሆኑ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንዴት ይተረጎማል በሚለው ጉዳይ አዲስ ማለዳ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ለማወቅ ጥረት አድርጋለች። በዛም ማወቅ እንደተቻለው ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ማለት ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ብዙኀኑ ከተቀበለው እና በተለያዩ ኃይማኖቶችም ዘንድ እንዳለው አስተምህሮ ተባእት ጾታ ያለው ወደ እንስት ጾታ፣ እንስት ወደ ተባዕት ተሳስበው እንደሚኖራቸው ሁሉ፣ በተቃራኒው ተባዕት እንዲሁ ከተባዕት እና እንስትም ከእንስት ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚደረገው መስተጋበር እንደሆነ ጥናቶች ያትታሉ።

በእርግጥ ይህ መስተጋብር ከላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው ከፍጥረት ጀምሮ የነበረ እና ከብዙኀኑ መሳ ለመሳ አብሮ የተፈጠረ ጉዳይ ነው ወይ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተም ጥናቶች ምላሻቸው እኩል በኩል በሚባል ደረጃ አመክንዮ በማንሳት ይሞግታሉ። ‹አሜሪካን ሳይንቲፊክ› የተሰኘ አንድ ድረ ገጽ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚያስቀምጠው ‹‹ለሚነሱት ጥያቄዎች ኹለት የተለያዩ ምላሾች ይሰነዘሩበታል›› ሲል ያነሳል።

አንዳንዶች ይህ መስተጋብር እና ግንኙነት ከፍጥረት ጀምሮ የነበረ እና በሥነ ሕይወት የተደገፈ ፍጹም ተፈጥሮአዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተው ይከራከራሉ። እንደ ማጣቀሻም ራሳቸውን ሳይቀር ሲያቀርቡ፤ በተቃራኒው ደግሞ ‹የለም! ይህ ጉዳይ በምርቻ የሚመጣ ነው።› የሚሉ ወገኖችም ደግሞ ቁጥራቸው የበዛ ነው።

በኢትዮጵያ ካርድ የተሰኘ የሲቪል ሶሳይቲ ዳይሬክተር እና መሥራች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት በፍቃዱ ኃይሉ በእርግጥ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በተመለከተ ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ለመሆኑ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል በሚል ከአዲስ ማለዳ ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ እንደሚከተለው ይመልሳሉ።

‹‹ይህ ጥያቄ ለባለሙያዎች ቢቀርብ ጥሩ ነበር። ሆኖም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ምሁራዊ ሐቀኝነት ችግር ይስተዋልበታል። በርዕሰ ጉዳዩ የሚጽፉ ምሁራን ቀድመው የያዙትን አቋም የሚደግፍ ‹ጥናታዊ መደምደሚያ› ያቀርባሉ እንጂ እምብዛም ወገንተኝነት የማይስተዋልበት ጥናት አያቀርቡም›› ሲሉ ጀምረው፤ ቀጥለውም ‹‹የሆነ ሆኖ፣ ጥያቄው ‹ማረጋገጥ ይቻላል› ሳይሆን ‹ተፈጥሯዊ ነው ወይስ አይደለም?› ቢሆን ይሻላል›› ሲሉም ለጥያቄው ማስተካከያም ያስቀምጣሉ።

በፍቃዱ ይቀጥላሉ ‹‹ለጥያቄው አጭር መልስ ከታች አስቀምጣለሁ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ወቅት አነጋጋሪው ነገር ‘የወሲብ ምርጫቸው’ ተቃራኒ ፆታ ያልሆኑ ኹለት አዋቂ ሰዎች፣ ተዋደው እና ተፈቃቅደው የሚፈፅሙት ግንኙነት በሕግ ሊያስከስሳቸው ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ነው። የሰው ልጆች በነጻነት የመምረጥ መብት ያላቸው ተፈጥሯዊ የሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ አይደለም። እንደ ጋብቻ፣ ቤተሰብ የመሳሰሉት ነገሮች እንኳን ሳይቀሩ ተፈጥሯዊ ሳይሆኑ ሰው ሠራሽ ጉዳዮች ናቸው።

ከዚያ ውጪ ያለውን ለማሳየት በርካታ ዓለም ዐቀፍ ምርምሮች እየተደረጉ ነው። ቬሮኒክ ሞቲዬር የተባለች ተመራማሪ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ‘A Very Short Introduction’ በተሰኘው የመጽሐፍት ስብስቡ ውስጥ ያሳተመላት ‘Sexuality’ (‘የወሲብ ምርጫ’ ብለን እንተርጉመው) የተባለ መጽሐፍ ላይ ‹የወሲብ ምርጫ ተፈጥሯዊም፣ ባዮሎጂካልም፣ ዓለም ዐቀፋዊም አይደለም› (“sexuality is not a natural, biological, universal experience”) ትላለች።

እንደምሁሯ የወሲብ ምርጫ ልክ እንደ ‘ወንዳወንድነት’ ወይም ‘ሴታሴትነት’ የምንላቸው ጽንሰ ሐሳቦች ነው መታየት ያለበት። ‘ወንዳወንድ’ የሆኑ ሴቶች፣ ‘ሴታሴት’ የሆኑ ወንዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ የብዙ ሁኔታዎች ውጤት ነው። በነገራችን ላይ ‘የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት’ በብዙ አገሮች እና በዓለም የጤና ድርጅት ሳይቀር የሥነ ልቦና ችግር ነው ተብሎ ታምኖ በሳይካትሪ ይታከም ነበር። የዓለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1992፣ እንግሊዝ በ1994፣ የራሺያ ፌዴሬሽን በ1999 እና የቻይና የሳይካትሪ ማኅበር በ2001 ችግሩ የሰዎቹ የሥነ ልቦና ሳይሆን ‘ሆሞፎቢያ ነው’ (በፆታ ምርጫቸው ምክንያት ሰዎችን መጥላት ነው) በሚል ነው በሕክምና ለማዳን መሞከራቸውን የተዉት›› ሲሉ ምላሻቸውን ይሰጣሉ።

ከዚሁ በተቃራኒው ደግሞ ከውልደቱ ጀምሮ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ፍላጎት እንዳልነበረው እና ‹‹እኔ ስወለድ ወደ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወይም ግብረሰዶማዊ አልነበረኩም›› ይላል፣ ለቢቢሲ ፊውቸር አስተያየቱን የሚሰጠው አንድ ባለታሪክ። ከክርስቲያናዊ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደተማረ እና በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መስመር ወንድ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች የፍቅር ጓደኛ እንደነበረው ያወሳል።

ለኹለት ዓመታት የዘለቀው የኹለቱ ተባዕቶች የፍቅር ግንኙነት ታዲያ የባለታሪኩ ወንድ የፍቅር ጓደኛው ወደ ተቃራኒ ጾታ በመሔድ ሴት አግብቶ እስኪለየው ድረስ ዘልቋል። ‹‹በእርግጥ ኹለታችንም ጎን ለጎን ሴቶች ጋርም ግንኙነት ነበረን›› ሲልም ያስታውሳል። ለቢቢሲ ፊውቸር የግሉን ታሪክ በራሱ ከትቦ እንዲታተም የፈቀደው ይኸው ባለታሪክ፣ ከአገረ አሜሪካ እንደሆነ እና በግብረሰዶማዊነት ዘንድ ያለውንም አስተያየት በጥቂቱ ያስቀምጣል።

በዚህም መሰረት በፈረንጆች 1977 አካባቢ በአገረ አሜሪካ ግብረሰዶማዊነት አብሮ የሚፈጠር ጉዳይ እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር ከ10 በመቶ የሚሻገር አልነበረም ሲል ይናገራል። ይሁን እንጂ እንደ ባለታሪኩ አነጋገር ጽሑፉ በተዘጋጀበት የፈረንጆች 2016 ላይ ግን ግብረሰዶማዊነት የተፈጥሮ ጉዳይ እንደሆነ የሚያምኑት ሰዎች ቁጥር በተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት እና መጠይቅ መሰረት ከ42 በመቶ እስከ 50 በመቶ መድረሱን ያመላክታል።

በተመሳሳይ በዛኑ ዓመት ግብረሰዶማዊነት ከቤተሰብ ወይም ከአካባቢ ሊወረስ የሚችል በአጠቃላይ ከአስተዳደግ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር እና ይህንንም የሚያምኑ ሰዎች በአገረ አሜሪካ በተሠራ ጥናት 60 በመቶ ይሆኑ እንደነበር ነው። እናም እስከ የዛሬ አራት ዓመት በፊትም ወደ 37 በመቶ ዝቅ ማለቱንም ይኸው ፀሐፊ ግለ ታሪኩን ባስነበበበት መጣጥፉ ላይ አስፍሯል።

ግብረሰዶማዊነትን በሚመለከት በአገራችን ኢትዮጵያ ጎልተው ወጥተው የመብት ጉዳይን ማቀንቀን ባይቻልም ቅሉ ውስጥ ውስጡን ለመኖራቸው እና በተለይም ደግሞ በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ኢትየጵያዊያንም በግብረሰዶማዊነታቸው በግልጽ እስከ መታወቅ ደርሰዋል። ይህ ጉዳይ ታዲያ ከላይ ካነሳነው አሜሪካዊው ባለታሪክን በመመርኮዝ በርግጥ ግብረሰዶማዊነቴ በተፈጥሮ አብሮኝ የተወለደ ጉዳይ እንጂ መርጬ የገባሁበት ወይም ተገድጄ እንድሆን የተደረገበት ሁኔታ አይደለም የሚል ግለሰብ ይኖራል ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

በዚህም ረገድ በፍቃዱ ኃይሉ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ እንኳን አሁን ድሮም ነበሩ›› ሲሉ ማጣቀሻ መጽሐፍትን መቼታቸውን ወደ 17 እና 18ኛ ክፍለ ዘመን ያደረጉ ጽሑፎችን በማጣቀስ ይናገራሉ። ‹‹ሕግ፣ ሃይማኖት እና ባሕሉ ስለሚጠየፋቸው እና ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ ስለሚጥል ራሳቸውን ሸሽገው ነው የሚኖሩት። አንዳንዶቹ ከአገር ከወጡ በኋላ ስለ መብታቸው እየተሟገቱ ነው። ‘ጉራማይሌ ኢትዮጵያ’ የሚባለው የፌስቡክ ገጽ ለዚህ ማሳያ ነው።

ድሮም አለ ያልኩትን በማስረጃ ለማስደገፍ ደግሞ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‹አንዳፍታ ላውጋችሁ› የተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ በዐፄ ተክለሃይማኖት ዘመን (1762-1769) የተከሰተ ድርጊት በገጽ 177 እና 178 ላይ ይተርካሉ። ታሪኩ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ የነበሩ ኹለት ሴቶችን የሚያሳትፍ ሲሆን፣ አንዷ በማርገዟ ሌላኛዋ ክስ መሥርታባት እስከ ንጉሡ ድረስ ለፍርድ የቀረቡበት እና ዳኝነት ያገኙበትን ሁኔታ ነው የሚተርከው።

ንጉሡም ጉዳዩን በብልሐት መርምረው አንደኛዋ ሴት (ያላረገዘችው) ከሴት ጓደኛዋ ጋር ከመተኛትዋ በፊት ከሌላ ወንድ ጋር ተኝታ ኖሮ፣ ‹ዘሩን ከዚህ ወንድ ተቀብላ ለዚህች ሴት አቀብላታለች› ብለው፣ ወንዱ የቀለብና ማሳደጊያ እንዲቆርጥ እንደፈረዱበት በዜና መዋዕላቸው ላይ እንደተጻፈ ጠቅሰዋል። ታሪኩ የተነገረበት ሁኔታ የአሁኑን ዓይነት ጥዩፍነት በዘመኑ እንዳልነበረ ፍንጭ ይሰጣል›› ሲሉ ከዘመናት በፊት ይህ ጉዳይ በነገሥታት ደረጃ ይታወቅ እንደነበር እና ነገሥታቱም ፍርድ ይሰጡበት የነበረ ወደ ፊት የወጣ እና ከአሁኑ ዘመን በበለጠ ባለፉት ዘመናት ለጉዳዩ የሚሰጠው አሉታዊ አመለካከት እንዳልነበር ይነግሩናል።

የተመሳሳይ ጾታን ጉዳይ በተመለከተ አዲስ ማለዳ ጥያቄዎችን ታነሳለች። ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ከሆነ የተፈጥሮን ኡደትንስ አይጋፋም ወይ? ምክንያቱ ደግሞ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ዘርን ከማስቀጠል እና ከመተካት በአጠቃላይ ልጆችን ከመውለድ አንጻር እንዴት አይነት መንገድን ይከተላል? በተራዘመ ጊዜ ሰሌዳስ ሕዝብን ቁጥር ለመቀነስ እና የሰውን ልጅ ቁጥር ሊቀንሰው እንደሚችል ደግሞ የተለያዩ ጥናቶች ለዚህ ሐሳብ ማጎልበቻ አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እና ጸሐፊው በፍቃዱ ኃይሉ ለዚህም ምላሽ አላቸው። በተለይም ደግሞ ይህ እንቅስቃሴ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ዘር ከመተካት ከሚለው ተፈጥረአዊ ሕግ ጋር ስለሚቃረን እንዴት ያዩታል ለሚለው ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ሰዎች ሁሉ ዘራቸውን መተካት ይፈልጋሉ ማለት አይደለም፤ የማይፈልጉ ሰዎች አሉ›› ብለው ጀምረው፣ ‹‹የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ተፈጥሯዊ ሆነ አልሆነ የአዋቂ ሰዎች ምርጫ ነው መሆን ያለበት በሚለው መወሰን አለበት››። ሲሉም ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ በዚህ ጉዳይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ብታገላብጥም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የራሳቸውን ልጆች ወልደው አቅፈው ለመሳም የሚኖራቸውን ዕድል በግልጽ የሚያስቀምጥ አንድም ጥናት ማግኘት አልቻለችም። ይሁን እንጂ የተመሳሳይ ጾታ ተጋቢዎች ወይም በአንድ ጣሪያ ስር የሚኖሩ ጥንዶች ልጆችን በማደጎ በመውሰድ የእጓለ ማውታ ስርዐኣትን መከተል የሚችሉበትን መንገዶች ግን በስፋት የሚጠቁሙ ሐሳቦች ለመኖራቸው መታዘብ ተችሏል።

ግብረሰዶማዊነት በኢትዮጵያ
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በፍቃዱ ኃይሉም እንዳስቀመጡት በኢትዮጵያ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ግብረሰዶማዊነት እንደነበር እና አሁንም ለመዝለቁ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከዚህም ጋር በተያያዘ ታዲያ ግብረሰዶማዊነት በተባዕት ለተባዕት ጾታ ግንኙነት ብቻም ሳይሆን እንስት ለእንስት ተመሳሳይ ጾታም ግንኙነት ተመሳሳይ ስያሜ አለው።

ይሁን እንጂ ዳንኤል ኢዶ ባልቻ በፈረንጆች 2009 የኹለተኛ ዲግሪያቸውን መመረቂያ ‹‹ግብረሰዶማዊነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መመረቂያ ጽሑፍ ላይ፣ በሴቶች መካከል የሚደረገው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ገልጸዋል። በአንጻሩ ደግሞ በተባዕት ጾታ መካከል የሚደረገው ግንኙነት ግን ወንጀል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እስከ ሦስት ዓመት እስር ድረስ የሚያስቀጣ እንደሆነም አስቀምጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል በጽሑፋቸው ሲገልጹ የመገናኛ ብዙኀን፣ የተማሩ ሰዎች እንዲሁም ቤተ እምነቶች የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በሚመለከት በአሉታዊ ጎን እንደሚቀሰቅሱ ይገልጻሉ። አያይዘውም ከቤተ ዕምነቶች ቅስቀሳ በተጨማሪም ግብሰዶማዊነት ጉዳይ በኢትዮጵያ በሴቶች የስርዓተ ጾታ ተሟጋችነት (ፌሚኒዝም) አለመኖር አንደኛው ጉዳይ መሆኑ ያስረዳል።

ሴት ስርኣተ ጾታ ተሟጋቾች (ፌሚኒስቶች) በዚህ በኩል እንዴት ተለይተው ግብረሰዶማዊያን መብት ተሟጋች ሊሆኑ ቻሉ? ግንኙነትስ አለው ወይ? በሚልም አዲስ ማለዳ ጥያቄዎችን ያቀረበችላቸው በፍቃዱ ምላሻቸውን ሲሰጡ ‹‹በርካታ ‘ሴክሶሎጂስቶች’ (የወሲብ ሳይንስ አጥኚዎች) የወሲብ ግንኙነት በተመሳሳይ ፆታም ሆነ በተቃራኒ ፆታ ወንዳወንድነት (‘ማስኩሊኒቲ’) እና ሴታሴትነት (‘ፌሚኒኒቲ’) ከማኅበራዊ ሥሪት ግንኙነቶች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይከራከራሉ።

የስርዓተ ፆታ መድልዖዎች የሚረዱና የማይቀበሉ ሰዎች፣ የፆታ ምርጫን መሠረት ያደረጉ መድልዖዎችን በቀላሉ ይረዷቸዋልም፣ ይቃወሟቸዋልም›› ሲሉ ያስቀምጣሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በቅርቡ በተለያዩ መንገዶች የሥነ ጾታ ትምህርት በስርዓተ ትምህርት ሊካተት እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ መሆኑን ተከትሎም አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ስለመጀመሩ ከአሉባልታ ውጪ የሰማሁት ነገር የለም።

ነገር ግን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ጉዳይ ተነጥሎ ሳይሆን የወሲብ ትምህርት በጥቅሉ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ መካተት አለበት ብዬ አምናለሁ። ይኸውም የሕፃናትና ሴቶች የወሲብ ጥቃትን ለመከላከል እና ምርጫን የሚያከብር ትውልድ ለመፍጠር ጠቃሚ ነው›› ብለው እንደሚያምኑም በመናገር ሐሳባቸውን ይደመድማሉ።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ጾታ በአመዛኙ ወንዶች ብቻ ተገናኝተው የፍቅር ግንኙነት የሚያደርጉበት መተግበሪያ መኖሩንም ለማወቅ ተችሏል። ይኸው መተግበሪያ በመዲናችን አዲስ አበባ በሚኖር በአንድ ኢትዮጵያዊ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውስጥ ባለ አንድ ወጣት እንደተሠራም ለማወቅ ተችሏል። ወደ አገር ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በአብዛኛው በጉብኝት የሚመጡ ውጭ አገር ዜጎችን በዋናነት ታሳቢ አድርጎ የተመሳሳይ ጾታ ሰዎችንም ለጎብኚዎች በማቅረብ እንደሚሠራም ለማወቅ ተችሏል።

ይኸው ወጣት ካለበት ሕይወትም ለመውጣት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው እና በ13 ዓመቱ የመደፈር ጥቃት ደርሶበትም ወደዚህ ሕይወት እንደገባም አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ለማወቅ ችላለች። ይህ ወጣት በኢትዮጵያ በየትኛውም ጥግ በዘረጋው መረብ ለጎብኚዎች ተመሳሳይ ጾታ ሰዎችን በአመዛኙ ወንዶችን እንደሚያገናኝም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። በዋናነት ደግሞ ጎብኚዎች መዳረሻ የሆኑ ከተሞች የደንበኞቹ ዐይን ማረፊያ ሲሆኑ እርሱም ደግሞ ጠንክሮ የእንግዶቹን ፍላጎት ተመሳሳይ ጾታዎችን በማቅረብ ያሟላል ማለት ነው።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከዓመታት በፊት ከግብረ ሰዶም ጋር በተያያዘ አሁን በሥራ ላይ በሌላ አንድ ምሽት መዝናኛ ቤተወ ውስጥ ስለተደፈረ ግለሰብም በግልጽ የሚያውቀው እና ምሽት ክበቡ ስነ ስርዓት አስከባሪም ከደፋሪዎች ጋር በመመሳጠር በቤቱ ውስጥ ይዝናና የነበውን ግለሰብ እንዲደፈር አድርጓል ተብሎ ሕጋዊ ቅጣት ተጥሎበት እንደነበርም የሚያስታውሰው ጉዳይ ነው።
በዚህ ጉዳይ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ የመጣው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ምናልባትም ከጊዜያት በኋላ የመብት ጥያቄው ወደ አደባባይ በመምጣት ሊያስተጋባ የሚችልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሴት ስርዓተ ጾታ አቀንቃኞች እንደሚሉት የግብረ ሰዶማዊያን ጉዳይ ከስርዓተ ጾታዊነት ጋር የሚገናኝ ሳይሆን ከሰብዓዊነት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ስርዓተ ጾታ አራማጆች በእርግጥ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የተመሳሳይ ጾታን መብት እንዲከበር ወይም በአደባባይ መተግበር እንዲችል እየተንቀሳቀሰ ያለ አካል አለመኖሩንም ይናገራሉ።

ግብረሰዶማዊነት በሳይንስ ዕይታ
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው እና መርጠው እና ፈቅደው ወደ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መሳባቸውን የሚናገሩ የአሜሪካዊውን ግለ ታሪክ ለማስቀመጥ ሞክረናል። እንዲሁም በመግቢያችን ላይ ለማሳየት በሞከርነው የባለታሪካችን መደፈር እና በዚህ ግንኙነት ውስጥ መገኘት ከተፈጥሮአዊነቱ ይልቅ የምርጫ ጉዳይ ነው ለሚሉት ወገኖች ሰፊ መከራከሪያ የሚያስነሳ ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል።
በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ የሥነ አዕምሮ ማኅበር ደግሞ ከአምስት ዓመታት በፊት በ2015 በፈረንጆች አቆጣጠር ባወጣው ‹‹ግብረሰዶማዊነት እና ሳይንሳዊ ማመሳከሪያዎቹ›› በሚል ጽሑፍ፤ ግብረሰዶማዊነት እስከ ቅርብ ጊዜ የአዕምሮ መዛባት እንደሆነ እና ግብረሰዶም መሆን ማለት አዕምሮን እንደመሳት እና እንደ በሽታም ይቆጠር እንደነበር ይናገራል።

ጽሑፉ ቀጥሎም ከ1970 በፈረንጆች ጀምሮ ግን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሰዎች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ከሚኖራቸው ግንኙነት አቻ እንደሆነ መታመን መቻሉንም ያስቀምጣል። የዓለም የጤና ድርጀትም በዚህ በኩል ባወጣው አጭር ማብራሪያ ግብረሰዶማዊነት የአዕምሮ ጤንነት መዛባት ሳይሆን በግብረሰዶማዊነት የሚገፉ ሰዎች ወደ አዕምሮ ሕመምተኛነት ሊዳረጉ ይችላሉ በሚልም ያስረግጣል።

አያይዞም በሴት እና በወንድ ጾታ ተመሳሳይ የጾታ ግንኙነት፣ ኹለቱንም ማስኬድ የሚችሉ፣ ጾታቸውን የቀየሩ እና ሌሎችም በዓለም ጤና ድርጅት ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት ያላቸው እና ጤናማ እንደሆነም ይነሳል።

ይሁን እንጂ ይኸው ጽሑፍ በውስጡ ተመራማሪዎች ግብረሰዶማነትን በሚመለከት ባዘጋጁት ጽሑፍ ውስጥ ግብረሰዶማዊነት ጤናማ የሆነ ድርጊት ነው ተብሎ የሚታመነውን አካሔድ የሚደግፍ ሳይሆን በግብታዊነት ጤናማ ነው ብቻ በሚል የሚያልፈው ጉዳይ እንደሆነ ያስቀምጣል።

ከዚሁ በተጓዳኝም ግብረሰዶማዊነት መነሾ ተብለው የሚታመኑ በሚል በቀረበው እና ለማጣቀሻነት በሚመች መልኩ እንደተሰነደው፤ ግብረሰዶማዊነት በእርግጥም በኹለት መንገድ ይከሰታል በሚል ክርክር እንዳለ እና ይህም ራሱን የቻለ ሰፊ ጉዳዮችን የሚይዝ እንደሆነ እንዲሁም በተፈጥሮ የሚመጣ ጉዳይ ነው ወይም የምርጫ ጉዳይ ነው በሚልም የተከፈለ ጎራ ለመሆኑ ጽሑፉ ያስቀምጣል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በተፈጥሮ የሚመጣ ጉዳይ መሆኑን የሚያምኑ በግብረሰዶማዊነት ላይ የተለሳለሰ አቋም እንዳላቸው እና እምብዛም የማይረበሹ ሰዎች ሲሆን፤ የግብረሰዶማዊነት ጉዳይ በምርጫ የሚመጣ እና ሰዎች በፍቃዳቸው የሚጀምሩት የሕይወት ዘየ ነው ብለው የሚያምኑ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ አናሳ መቻል እና ታግሶ የማሳለፍ አዝማሚያ እንዳላቸው ይናገራል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎች በተፈጥሮ የሚመጣ ጉዳይ ነው በሚል ሐሳባቸውን እየሰነዘሩ እንዲገኙም ጥናቱ በቁጥር የተደገፈ ዘገባም ሲሠራ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ ነው የሚያስብል ድምዳሜ ላይ መድረስ አልተቻለም።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ማለዳ ከተለያዩ የእምንት ተቋማት የተወጣጡ የእምነት መሪዎችን እና የኃይማኖት አባቶችን ባነጋገረችበት ወቀት በአንድ ድምጽ ማግኘት የተቻለው ነገር ቢኖር ግብረሰዶማዊነት ፍጹም ኃጢአት መሆኑን ነው።

አዲስ ማለዳም በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾቿ ላይ ለሰዓታት ባዋለችው መጠይቅ መሰረት፣ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ድምጽ ሰጪ ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሮአዊ ጉዳይ እንዳልሆነ ያምናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here