የተከለከለው የኢዜማ መግላጫ

0
676

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ትናንት ነሐሴ 22/2012 በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሔዱ የመሬት ወረራዎችን እና ኢፍትሀዊ የሆነ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ክፍፍል በተመለከተ በራስ ሆቴል ሊሰጥ የነበረው መግለጫ በፖሊስ ተበትኗል።

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከቀናት በፊት ስለስብሰባው ለሰላም ሚኒስቴር በደብዳቤ ያሳወቁ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ሊሰጥ የነበረው መግለጫ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ስለመግለጫው መረጃ የለኝም በሚል ሳይካሄድ መቅረቱን አስታውቀዋል።

ናትናኤል ለአዲስ ማለዳ ጨምረው እንደገለጹት፤ ለሰላም ሚኒስቴር በተጻፈው ደብዳቤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰደ የሚገኘውን ፕሮቶኮል በተከተለ መልኩ ጋዜጣዊ መግለጫው እንደሚካሔድ ተገልጾ ደብዳቤ መጻፉን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የፓርቲው ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዋሲሁን ተስፋዮ እና ምክትል ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) መግለጫ ለመስጠት በዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ስለ መግለጫው መረጃ የለኝም በሚል እንዳይካሔድ የተከለከለው።

አዲስ ማለዳ ከፓርቲው ያገኘችው መረጃ እንደሚያመላክተው በአዲስ አበባ ከተማ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎችን እና ኢ-ፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ክፍፍልን በሚመለከት ፓርቲው ከስድስት ሳምንት በፊት ያለውን ችግር የሚያጠናና መረጃ የሚያጠናቅር ኮሚቴ አቋቁሞ መረጃዎችን ሲሰበስብ እንደቆየና ይህንኑ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መግለጫ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነበር።

ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት በጸጥታ አካላት በኩል ምንም አይነት እክል ፓርቲው ገጥሞት እንደማያውቅ እና ይህ የመጀመሪው እንደሆነ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ ጉዳይ በተደጋጋሚ መግለጫ ለመስጠት በእስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ለዕውነተኛ ድሞክራሲ በተደጋጋሚ መከልከሉ ይታወቃል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here