በምዕራብ አርሲ እና ምስራቅ ሸዋ ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎች 27 ሚሊየን 500ሺሕ ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

0
639

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ እና ምስራቅ ሸዋ ዞን ተፈናቃዮች ከ27 ሚሊየን 500ሺሕ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።
የቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገው በባቱ እና በሻሸመኔ ከተሞች እንዲሁም ከሁለቱ ዞኖች ለተመረጡ ወረዳዎች ነው።
የድጋፉ አላማ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት ቤትና ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች ነው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና አባል የሆኑት አበባ ዮሴፍ እንደገለጹት ለተፈናቃዮች የተደረገው የምግብ ነክ እና የአልባሳት ድጋፍ በጥሬ ገንዘብ ሲተመን ከ27 ሚሊየን 500 ሺሕ ብር በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሽታዬ ምናለ የአርትስቱን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዜጎች ላይ የተፈጸመው የዘርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልጸው መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሽታዬ አክለውም ኢትዮጵያ ከአደጉ አለም አገራት ተርታ እንዳትሰለፍ ሕዝቡ በዘር ጥላቻና በሀሰት ትርክት ወደ ግጭት እንዲገባ የሚፈልጉ የጥፋት ሃይሎች እንዳሉ ጠቁመው ለእነዚህ የጥፋት ኃይሎች በር ሳንከፍት ችግሮቻችንን በዴሞክራሲያዊ እና በሰለጠነ መንገድ በመፍታት አገሪቷን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይጠበቅብናል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የዞንና የወረዳ አመራሮች ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ያስረዱት ምክትል አፈ-ጉባዔዋ የክልሉ ሕዝብ ተደጋግፎና አብሮ የመኖር እሴቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡

የምዕራብ አርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ከድር ኤሌሞ በበኩላቸው ድርጊቱ የኦሮሞን ህዝብ የማይወክልና ከህዝቡ ባህልና እሴትም ጋር የሚቃረን መሆኑን ጠቁመው የተፈናቀሉትን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው የደረሰባቸውን ግፍና በደል በዝርዝር የገለጹ ሲሆን አሁንም ስጋት እንዳለባቸው እና መንግስት የህግ የበላይነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እና የጀመረውን የመልሶ ማቋቋም ስራ በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቁመው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ የሴቶች ኮከስ አባላት ከመንግስት ተቋማት እና ከግል ድርጅቶች የተገኘው ነው ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here