የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተያዘው የ2013 በጀት አመት ከአገራዊ ወጪ ንግድ 3.91 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት በእቅድ መያዙንና ከዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍና ክትትል ከሚያደርግባቸው የግብርና 2.918 ቢሊዮን እና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶች 587.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚጠበቅ አስታወቀ፡፡
ከምርት አቅርቦት እስከ ወጪ ንግድ ባለው የግብይት ሰንሰለት በየደረጃው ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ተግዳሮቶችን በቅንጅት በመፍታት ከዘርፉ የወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሳደግ የሚለውን ዓላማ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው መነሻ እቅድ የአምስት ዓመታት የግብርና ምርቶች የምርት እና ምርታማነት ትንተና የእቅዱ ነው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የአምስት ዓመታት የወጪ ንግድ የዕቅድ አፈፃፀም ትንተና፣ የ2012/13 ምርት ዘመን የግብርና ምርቶች አቅርቦት ትንበያ ግምት፣ የግብርና ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ያላቸው ፍላጎት፣ የአለም ገበያ የግብርና ምርቶች ዋጋ ትንበያ፣ ከ2012 በጀት ዓመት የዞረ የወጪ ንግድ ምርቶች ክምችት ትንተና፣ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የግብርና ምርቶች ጥሬ ግብዓት ፍላጎት ትንተና፣ የወጪ ግብርና ምርቶች የብጣሪ/ሪጀክት መጠን ትንተና እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለግብርና ምርቶች ያለው አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅእኖ የሚሉትን ነጥቦች ለእቅዱ ዝግጅት በመነሻነት ከታዩ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል ተብሏል፡፡
እቅዱ በታሳቢነት ያስቀመጣቸው አመላካቾች አዎንታዊነትን ተከትሎ እቅዱን ለማሳካት የምርት አቅርቦትንና ጥራትን ማሳደግ፣ የአሰራር ስርዓቶችን ማሻሻል፣ የህግ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻል የህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መቆጣጠር እና የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚተገበሩ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012



