ባለፉት ሶስት ወራት ከ130 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተፈናቅለዋል

0
769

ባለፉት ሶስት የክረምት ወራት ብቻ ከ130 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የመፈናቀል አደጋ እንደደረሰባቸው የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ ነሀሴ ወር አጋማሽ ባለው ወቅት በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ከ130 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት መፈናቀላቸውን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አልማዝ ደምሴ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በእነዚህም ጊዜያት በአጠቃላይ በ15 ሰዎች ላይ እና በ410 እንስሳት ላይ የሞት አደጋ መከሰቱም የተገለፀ ሲሆን አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ለሚገኙ ሰዎችም አፋጣኝ የሆነ ድጋፍ በኮሚሽኑ እየተደረገ መሆኑንም አልማዝ ገልፀዋል።

በእነዚህ የጎርፍ አደጋዎች ምክንያት በሰኔ ወር በ6 ክልሎች ላይ በሚገኙ በ16 ወረዳዎች በተከሰተው አደጋ የ7 ሰዎች እና የ28 እንስሳት ሞት ተመዝግቧል፣ 536.1 ሄክታር የሚሆን ማሳ ወድሟል፣ 65 የሚሆኑ ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፣ እንዲሁም 1 ሺህ 24 የሚሆኑ አባወራዎችም የአደጋው ተጠቂ ሲሆኑ 54 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

በሀምሌ ወርም በተመሳሳይ በ6 ክልሎችና 30 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ በደረሰው አደጋ 6 ሰዎች እንዲሁም 327 እንስሳቶች ሞተዋል፣ 20 ሺህ 781.5 ሄክታር ማሳ ተጎድቷል፣ 33 ቤቶችና 2 ሱቆች ፈርሰዋል፣ 2 ሺህ 780 አባወራዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ በተጨማሪም 1 ሺህ 967 ሰዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

በነሀሴ ወርም በ5 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 9 ወረዳዎች የ2 ሰዎች እና የ55 እንስሳቶች ሞት የተመዘገበ ሲሆን 11 ሺህ 889 አባወራዎች በአደጋው ተጎድተዋል፣ 1 ሺህ 851 የሚሆኑ ሰዎችም ከቤት እና አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፣ 18 ሺህ 476 ሄክታር የሚሆን ማሳም በጎርፍ አደጋው ሳቢያ ተጎድቷል።

በአፋር ክልልም የተጎጂዎች ቁጥር ለብቻው የተሰራ ሲሆን በሰኔ ወር ብቻ 49 ሺህ 55 የሚሆኑ አባወራዎች የተጠቁና 19 ሺህ 626 ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በአጠቃላይም እስከ ነሀሴ ወር አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 69 ሺህ 885 ሰዎች አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን 41 ሺህ 731 ሰዎችም ተፈናቅለዋል ሲሉ ዳይሬክተሯ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ይህም የተፈናቃይ ቁጥር ባሳለፍነው ሳምንት በመታሀራ ወንጂ፣ አዋሽ ፈንታሌ፣ አሜባራ፣ ዱለቻ እና ገዋኔ አካባቢዎች ላይ የተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን የማያካትት ሲሆን የመፈናቀሉም ይሁን የአደጋው ሁኔታ በየጊዜው የሚቀያየር መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም መሰረት የጎርፍ አደጋው እስከ ነሀሴ አጋማሽ ባለው ወቅት ውስጥ በአፋር ክልል በሚገኙ በሁሉም ዞኖች፣ በአማራ ክልል በደቡብ እና በማእከላዊ ጎንደር እንዲሁም በኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በደቡብ ወሎ እና በሰሜን ሸዋ፤ ከጋንቤላ ክልል በአኟክ እና ኑዌር ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልልም በምስራቅ ሸዋ፣ በደቡብ ምእራብ ሸዋ፣ በምእራብ ሸዋ፣ በአሩሲ፣ በምእራብ ጉጂ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ ወረዳዎች ተከስቷል።

እንዲሁም በሱማሌ ክልል በፋሰን፣ በሸበሌ እና ጅጅጋ አካባቢዎች ላይ፤ በተጨማሪም የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ላይ በጉራጌ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ፣ በስልጤ፣ በከፋ እና በዳውሮ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማና በአዲስ አበባ ዙሪያ እንደዚሁ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋዎች መከሰታቸውም ተገልጿል።

ዳሬክተሯ እንዳሉት በሰኔ ወር የጎርፍ መጠባበቂያ እቅድ ላይ በተሰራው አጠቃላይ ግምት መሰረት ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በማሳቸው፣ በከብቶቻቸው፣ በቤትና ንብረታቸው ላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል፤ እንደዚሁም ከእነዚህ ሰዎች ውስጥም ወደ 434 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሎ ቅድመ ግምት ተቀምጦ እንደነበር አስረድተዋል።

ይህም የጎርፍ አደጋ ሊቀጥል የሚችል መሆኑን የጠቆሙት አልማዝ ክረምቱ ካለማለቁ ጋር ተያይዞ በቀጣይም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ፣ ነጎድጓዳማና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ዘንቦ ረባዳማና ቆላማ ቦታዎች ላይ በጎርፍነት መልክ በመከሰት ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም አስታውቀዋል።

የዘንድሮው የጎርፍ አደጋ በሌሎች ጊዜያት ከተከሰቱት የጎርፍ አደጋዎች ሁሉ የከፋ ጉዳት ያስከተለ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ የዝናቡም ሁኔታ በጣም ተከታታይና የጀመረውም ደግሞ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ መሆኑ ለአደጋው መጨመር ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል። በጎርፍ መጠባበቂያ እቅዱ መሰረት የሚመለከታቸው ሰዎች ስራዎችን ከሰሩ ከዚህ በላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር መቀነስ ይቻላልም ብለዋል።

ለአደጋ መከላከሉ ስራ ከተበጀተው አጠቃላይ በጀት ውስጥ ምግብ ነክ ላልሆነ ድጋፍ 277 ሚሊዮን 678 ሺህ 500 ብር እንደሚያስፈልግ የገለፁት አልማዝ በግብርናም 231 ሚሊዮን ብር፣ ለምግብ 1 ቢሊዮን 385 ሚሊዮን 341 ሺህ 475 ብር፣ ለተመጣጠነ ምግብ፣ 304 ሚሊዮን 871 ብር እያለ በአጠቃላይ ወደ 3 ቢሊዮን 409 ሚሊዮን 375 ሺህ 38 ብር እንደሚያስፈልግ ተገምቶ መቀመጡን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ይህም የክረምት ወቅት ሲያልፍ ምን ያህል አጠቃላይ ጉዳት ተከሰተ የሚለው ተጠንቶ ይፋ ይደረጋል ያሉት ዳይሬክተሯ አሁን በመስራት ላይ የምንገኘው ስራ አደጋው በሚደርስበት ጊዜ በፍጥነት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በሚያስፈልጉበት አካባቢዎች ላይ ማድረስ ነው ብለዋል።

እነዚህም ድጋፎች ከምግብ ነክ እንደ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሩዝ፣ አልሚ ምግብና ወተት በነብስ ወከፍ የሚሰጠው ስሌት አለ፤ በዛ ስሌት መሰረት ተሰልቶ ለተጎጂዎቹ የሚሰጣቸው ሲሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ምንጣፍ፣ ሸራ፣ ብርድ ልብስ፣ ብረት ድስት፣ ሰሀን፣ ጆግ፣ የሻይ ኩባያ፣ ዛንዚራ እና መሰል ቁሳቁሶች እንደዚሁ ይታደላሉ ሲሉም ገልፀዋል።

እስካሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ በሁለት አይነት መንገድ እየተደረገ ነው ያለው የሚሉት አልማዝ ይህም በመደበኛ በጀት እርዳታ ማለትም በየስድስት ወሩ የሚጠና ጥናትን መሰረት አድርጎ እያንዳንዱ ክልል በዛ መሰረት የሚያስፈልገው ድጋፍ ተሰልቶ በሚደረግለት ድጋፍና ሁለተኛው ደግሞ በተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ማለትም ጎርፍ፣ እሳት አደጋ፣ በአንበጣ፣ በግጭቶችና የመሳሰሉት ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ የሚሰጥ ድጋፍ ነው ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here