ቢያንስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአጠቃላይ ሕወሓት ይቅርታ መጠየቅ አለበት

0
787

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ነቀምት ከተማ ገና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያሉ፤ ከ41 ዓመታት ገደማ በፊት ነበር የተቀላቀሉት፤ ቀጀላ መርዳሳ።
ያኔ የነበረው ትግሉ ወደ ሜዳ ሳይወርድ እና እንቅስቃሴው ከተማ ውስጥ በነበርበት ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች መማክርት ጸሐፊ የነበረው ሥመ ጥሩው አቡማ ምትኩ ስር ይመራ በነበረው ምድብ ፖለቲካዊ ፕሮግራም ካስጠኑ በኋላ፣ በጽሑፍ ቃለ መሀላ ፈፅመው ድርጅቱን ተቀላቅለዋል።

በወቅቱ ቃለ መሃላው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተፅፎ ነበር የቀረበው በማለት የሚያስታውሱት ቀጀላ መርዳሳ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከፍተኛ አመራር አባል ናቸው። በአሁኑ ወቅትም የግንባሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ከሰሞኑ ሥሙ ደጋግሞ የሚነሳው ግንባሩ፣ አየር ላይ ተንጠልጥለው ያሉና ያልተቋጩ አጀንዳ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉበት።
ቀጀላ መርዳሳ ይህንን በሚመለከትና የተለያዩ ተያያዝ ጉዳዮችን በሚመለከት ከአዲስ ማለዳው ዳዊት አስታጥቄ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ወደኋላ መለስ ብለን እንጀምር፤ ድርጅቱን እንዴት ተቀላቀሉ? ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባትስ ሲወስኑ ምን ዓይነት ሁኔታ ገጠሞት?
የትግል ሜዳውን ምዕራብ ግንባር በመቀላቀል ነበር የጀመርኩት። በዚያ የኦቦ ሌንጮ ለታ ወንድም አብርሃም ለታ፣ የዛሬውን ሊቀመንበር ኦቦ ዳውድ ኢብሳ እንዲሁም ሌሎች ነቀምት እንተዋወቅ የነበሩ እና በአመራር ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች ስለነበሩ ለእኔ ሁኔታውን ቀላል አድርጎልኝ ነበር። እንደ አዲስ አልሆነብኝም።

እንዲያውም ወደ ዋናው ማዘዣ (head quarter) ተላኩኝ። ከዚያም በካድሬ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤትም እንዲሁ በአሠልጣኝነት ቆይቻለሁ።
ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ወደ ካርቱም በመሄድ ዲፕሎማቲክ ዴስክ ላይ ተመድቤ ሠርቻለሁ። በእርግጥ ከዛ በፊት በድርጅቱ በነበረኝ እንቅስቃሴ ምክንያት በወቅቱ የነበረው ስርዓት ለአራት ዓመት እስር ወርውሮኝ ነበር።

ከዚያ በፊት የትምህርትዎ ሁኔታ ምን ሆነ? ከፖለቲካ ትግል ሜዳ ውጭ በሥራ ዓለምስ በምን ሙያ ሠርተዋል?
በ1974 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በታሪክ ትምህርት መጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ የተወሰነ ጊዜ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግያለሁ። ከዚያ ውጪ በትግል ሜዳ ነው እድሜዬን ያሳለፍኩትና አሁንም እያሳለፍኩ ያለሁት።

እንዴት እና መቼ ነበር ወደ ኃላፊነት ቦታ የመጡት?
በትግል ሜዳ ሆኖ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ አመቺ ሁኔታ አልነበረም። ኹለተኛው ጉባኤ ሞቃድሾ ነበር የተካሄደው። በወቅቱ ምዕራብ ካርቱም ስለነበርኩ መድረስ አልቻልኩም ነበር።
ሦስተኛው ጉባኤ ግን በአባላትም ብዛት እና ተሳትፎ የተሻለ ነበር። እኔም በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ በአመራርነት የተመረጥኩት በ2004 እ.ኤ.አ በዚሁ ሦስተኛው ጉባኤ ላይ ነው።

እርስዎ እና መሰሎችዎ ከወጣትነት ጀምሮ የታገሉበት ድርጅት አሁን ያለበትን ደረጃ ሲያዩ ምን ይሰማዎታል?
ድርጅቱ ከተመሠረተ ሦስት ዓመት በኋላ ነበር የተቀላቀልኩት። አብሬ ነው የተወለድኩት ማለት እችላለሁ። ድርጅቱ ሲመሠረት የኦሮሞ ሕዝብ ንቃተ ህሊና በጣም ዝቅተኛ ነበር። ስለዚህ የግንባሩ ዋና ሥራ በኃይለሥላሴ ጊዜ ጠፍቶ የነበረውን የኦሮሞ ማንነት ማስመለስ ላይ ነበር።

ትኩረት ያደረግነው የኦሮሞን ማንነት በማስመለስ ላይ ነው። ኦሮሞ በሌላ (derogatory) በሆነ ወይም የኦሮሞን ሕዝብ ባልሆነ ሥም ነበር የሚጠራው። ከንጉሡ ስርዓት መውደቅ በኋላ የደርግ መንግሥት ሲመጣ ነው ኦሮሞ በሥሙ መጠራት እንኳ የቻለው።

ይህንን የጠፋውን ማንነቱን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን ለማስመለስ ትልቅ ትግል አድርገናል። በወቅቱ ሱዳን አገር ኦሮሞ የሚባል ማንነት እና ኦሮምኛ ቋንቋ አይታወቅም ነበር። ይልቁንም ብዙዎች ከሰላ [ሱዳን የሚገኝ ስፍራ] አካባቢ ‹ኦረማ› የሚባል ቦታ ይመስላቸው ነበር። ትግርኛ እና አማርኛ ተናጋሪዎች ግን ይታወቁ ነበር።

በእርግጥ በብዛት ወደ ሱዳን ይሄዱ የነበሩት ከኤርትራ እና ከሌሎች አካባቢ ስለነበር እና የኦሮሞ ልጆች ከአገር በብዛት አይወጡም ስለነበር ይሆናል። ግን የኦሮሞ ማንነት የማጥፋት ሥራ በመሠራቱ የመጣ ውጤት ነበር። የኦሮሞ ብሔርተኝነት ለማምጣት፣ የኦሮሞን ማንነት ለመገንባት እንዲሁም የኦሮሞን ሕዝብ አንድነት ለማረጋገጥ እና ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ያለ ኦሮሞ አንድ እንደሆነ ለማስተማር እና ለማገናኘት ረጅም ርቀት ሄደናል።

ያለፉት ስርዓቶች የኦሮሞን ማንነት ለማጥፋት ብዙ ሠርተዋል። ኦሮሞን በአካባቢ፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በመከፋፈል አንድነት እንዳይኖረው እና እንዲበታተን አድርግዋል። ይህንንም ኦነግ ሲታገል ኖሯል። ለዚህ ነው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የኦሮሞ ብሔርተኝነት ምልክት (አርማ) ነው የምንለው።

የኦነግ የተቀባይነቱ መሠረትም ይሄን በመሥራቱ የመጣ እንጂ በጦር ሜዳ ውጊያዎች ወይም በፖለቲካው መስክ ያሳካነው ውጤት አይደለም።
በእርግጥ ኦነግ በትጥቅ ትግልም በምዕራብ ሆነ በምሥራቅ በኩል ትግል አድርጓል። ወደ ትጥቅ ትግል ሲገባም የደርግ መንግሥት ከሶማልያ ተስፋፊ ጦር ጋር ጦርነት ውስጥ የገባበት ወቅት ነበር። ታላቋን ሶማሌ እንመሠርታለን፣ ወሰናችን እስከ አዋሽ ድረስ ነው በሚል።

ጊዜው ለኦነግ አስቸጋሪ የሚባል ነበር። በአንድ በኩል ከደርግ መንግሥት ጋር በሌላ በኩል ደግሞ ከዚያድባሬ የሶማልያ ወራሪ ጦር ጋር። ዚያድባሬ በበኩሉ ሶማሌ ‹አቦ› ብሎ በምሥራቅ አካባቢ የነበሩ እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የነበሩ ኦሮሞዎችን ገንጥሎ ለመውሰድ የነበረውን ጥረት ለማክሸፍ፣ በሌላ በኩል በደርግ መንግሥት ይደገፉ ከነበሩት የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ጦር ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ነበርን።

እና የጆን ጋራንግ ጦር መቀመጫም በዚሁ በምዕራብ አቅጣጫ ስለነበር በዚያ በኩል የነበረውን የትጥቅ ትግል በሦስት አቅጣጫ አስቸጋሪ አድርጎብን ነበር። ያም ሆኖ እስከ ደርግ መንግሥት ውድቀት ድረስ ብዙ ፈተና አልፈን የሽግግር መንግሥት ምሥረታው ጋር ደረስን።

በሽግግር መንግሥት ምስረታው ወቅት ደግሞ ወያኔ መራሹ መንግሥት ባለ በሌለ ኃይሉ ድርጅታችንን ማሳደድ ተያያዘው። የዓለማቀፍ ሁኔታም አንድ ኃይል ብቻ የሚያስተዳድርበትን ስርዓት ስለተፈጠረ የትጥቅ ትግሉን የበለጠ አስቸጋሪ አደረገብን።

ወደ ሱዳን፣ ኬንያም ሆነ ወደ ጅቡቲ መሄድ አንችልም። ሶማልያም እንደ አገር የለችም። ዓለማቀፋዊ ምክንያት ጂኦ -ፓለቲካዊ ዳራው አስቸጋሪነት እና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የኦነግን የትጥቅ ትግል ስኬት አስቸጋሪ አድርጎብናል።

ግማሽ ክፍለ ዘመን ለተጠጋ የግንባሩ ጉዞ ብዙ የኦሮሞ ወጣቶች በሥመ ኦነግ የተገረፉ፣ የሞቱ እና ደብዛቸው የጠፋ ግለሰቦች አሉ። እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ድርጅት የግለሰቦቹን ማንነት በሰነድ መያዝ ችላችኋል?
የኦሮሞ ወጣቶች፣ የኦሮሞ ምሁራን፣ የኦሮሞ ነጋዴዎች ሆን ተብሎ በፖሊሲ ደረጃ ተሠርቶብናል፤ በተለይ በሕወሓት። ሕወሓት በባህሪው ነፃ የሆኑ ፓርቲዎች እንዲኖሩ አይፈልግም። በተለይ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፓርቲዎችን ለማየት አይፈልግም ነበር። ወደ ህወሓት የሚለጠፉትን ብቻ ነበር የሚያስጠጋው።

ከዚያም አልፎ የኦሮሞ ባለሀብቶችንም በገንዘብ ሊረዱ ይችላሉ በሚል እያሳደደ ሲገድል ነው የከረመው። እንደእነ ደራራ ከፈኒ ያሉ የኦሮሞ ባለሀብት በጠራራ ፀሐይ ነው የገደላችው። ብዙ ደብዛቸው የጠፋ ወይም ሆን ተብሎ ከንግድ ዓለም እንዲወጡ እና እንዲደኸዩ ለማድረግ ተሠርቷል። በዚህም የኦሮሞ ብሔርተኝነት መሰረት እንዳይዝ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል። የነቁ የኦሮሞ ምሁራን እና ወጣቶች ምንም ውስጥ ሳይኖሩ በስመ ኦሮሞነት ብቻ እየታደኑ ተገድለዋል።

ስለዚህ በተለያየ መልክ ጉዳት የደረሰባቸው እንዲሁም የሞቱ የኦሮሞ ተወላጆችን በታሪክ ማህደር ሰንዶ ለመያዝ ግንባሩ ጥረት እያደረገ ነው። ተገቢ እንደሆነም እናምናለን። የምናውቃቸው ዝርዝሮች ይኖሩናል። የማናውቃቸውን ብዙዎቹን ደግሞ በጥናት ለማጠናቀር እንሠራለን።

የኦሮሞ ብሔርተኝነት መፍጠር ትልቁ የኦነግ ስኬት ነው ብለዋል። የኦሮሞ ብሔርተኝነት የቤት ሥራ ተጠናቋል ብለው ያስባሉ?
በጣም አሳክተነዋል። በኃይለሥላሴ እና በደርግ ጊዜ በምሥራቅ እና በምዕራብ አካባቢዎች ተለያይተው የሚገኙ የኦሮሞ ሕዝቦችን ለማስተሳሰር እና ለማገናኘት ችለናል። በተለይ በ1983/4 ከወሎ ከሚሴ ጀምሮ እስከ ሞያሌ እና ወንበራ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የኦሮሞ ሕዝቦች እዚህ ፊንፊኔ ጉለሌ የሚገኘው ጽሕፈት ቤት መጥተው የነበሩበት አጋጣሚ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን መፍጠር መቻላችን ማሳያ ነው።

ሃይማኖት የየግል ነው፣ ኦሮሞነት ግን የጋራችን ነው የሚል አቋም ወስደዋል። አሁን በሃይማኖት የሚለያይ ብዙም ኦሮሞ የለም። ሾልኮ የሚገባ ወይም ከውጪ ተልዕኮ ይዞ የሚመጣ ካልሆነ በቀር። እንደ አንድ ሕዝብ ነው ኦሮሞ እየተንቀሳቀሰ ያለው።

ሌላ ምሳሌ ልስጥህ፤ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ሲቃወሙ የነበሩት ሰዎች ወለጋ እና ሐረር ጫፍ የነበሩ የኦሮሞ ሕዝቦች ናቸው። ሲጮኹ የነበሩት ፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ የኦሮሞ ልጆች ተፈናቀሉ ብለው ነው። ይህ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ለመፍጠር ሌላው ማሳያ ነው።

ወደ አገር ቤት ከተመለሳችሁ ወዲህ ትልቅ ተሃድሶ ማድረጋችሁ ይታወቃል። በተሃድው ምን ምን ጉዳዮች ተነሱ?
እንዳልኩህ በተሃድሶው እንደ ትልቅ ስኬት የወሰድነው የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ማሳካታችንን ነው። ብሔርተኝነት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው ማንነትን መገንባት ነው። የዚህ ብሔር አባል ነኝ ብሎ ራስን ማዛመድ መቻል እና የዛን ብሔር ወግ፣ ባሕል መጠበቅ እና አብሮ መጓዝ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ወደ መንግሥት ምሥረታ (State hood) ነው የሚያድገው።
ከ1983 በኋላም በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚባለው ነገር አለ። ይሄ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከዴሞክራሲ ጥያቄ መካከል አንዱ ነው። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ደግሞ ከታች ጀምሮ ሕዝቡ የሚያስተዳድረውን አካል መምረጥ መቻሉ ነው።

በሌላ አነጋገር ኦሮሞም ሆነ ሌላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመረጡት መሪ ተዳድረው አያውቁም። እንደ ኦነግ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መሪ ተመርጦ አያውቅም። ይሄ ትልቅ የሚቀር ጉዳይ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መመለስ እና የዴሞከራሲ መስፈን ለሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው እና እንደሚተርፍ አናምናለን።

የኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ የዴሞከራሲ እሴት ያለው ሕዝብ አንደመሆኑ ያንን ለማምጣት ብዙ ርቀት ይቀራል። ሕዝቡ በመረጠው እና በፈለግው መንገድ ዴሞክራሲያዊ ባህላችን ዛሬም ድረስ ሊቀየር አልቻለም።

የመሬት ጥያቄ አልተመለሰም። እንደ ኦነግ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ ነው። ከአፄ ምኒልክ በኋላ የመጣው የገባር ስርዓት መሬት ሕዝቡ መሬት አልባ እንዲሆን አድርጎታል።

የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አልተመለሰም የሚል አቋም አላችሁ? ‹መሬት ላራሹ› በሚል በደርግ መንግሥት የተወሰደውን እርምጃስ እንዴት ታዩታላችሁ?
መጀመርያ ጥያቄውን የመለስው ይመስል ነበር። በኋላ ግን በተለያየ መልክ መልሶ ሕዝቡን ገባር አድርጎታል። በመዋጮ መልክ ከምርቱ ላይ እንዲሰጥ ይደረግ ነበር።
በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን መሬት የመንግሥት እና የሕዝብ ነው በሚል እንደፈለገ ሕዝቡን ከመሬቱ ሲያፈናቅል፣ ሲነጥቅ ነው የከረመው። ለማደናበር የሕዝብ ይላል እንጂ የሕዝብ ሆኖ አያውቅም። የፈለጉትን መሬት እንደፈለጉ ሲነጥቁ ነው የከረሙት። በፍጹም መሬት የመንግሥት መሆን የለበትም። የሕዝብ ብቻ ነው መሆን ያለበት።

ወደ አገር ቤት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስናችሁ ስትገቡ ከመንግሥት ጋር የተስማምታችሁባቸው ግን እስከ አሁን ያልተፈፀሙ ጉዳዮች ካሉ ቢነግሩን?
ስምምነቱን ለመፈፀም ብዙ ጊዜ አልወሰድንም። ምናልባትም ግማሽ ቀን እንኳን አልፈጀንም። አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው ኤርትራ የመጡት።
ኹለት አበይት ጉዳዮች ነበሩ የተወያየንባቸው። አንዱ ትጥቅ ትግሉን አቋርጠን በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብተን ለመታገል ሲሆን ሌላኛው በነፃነት ተንቀሳቅሶ የማደራጀት፣ የመቀስቀስ እንዲሁም የተወረሱ ንብረቶቻችን እንዲመለሱልን የሚሉ ነጥቦች ነበሩ።

ከ1984 ቻርተር ተገፍተን ስንወጣ ብዙ ንብረቶች ተወርሰውብናል፣ ቢሮዎችም እንዲሁ። በርካታ መኪናዎች እና ገንዝብም ጭምር ነበር የተወረሰብን። ከመንግሥት ጋር ያለንም ግንኙነት እንደ ጠላት ከመተያየት አልፎ አብሮ ለመሥራት በሚል ተስማምተን ነበር።

በእኛ በኩል ምንም ጥያቄ የለውም፤ በሰላማዊ መንገድ እየታገልን ነው። በተለይ በኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር የአሁኑን ኦዲፒ- ብልፅግናን ጨምሮ በጋራ ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰን ነበር።

እንደ ገባን የመጀመርያዎቹ ኹለት እና ሦስት ወራት ጥሩ ነበር። በኋላ ግንኙነቶቹ እየተባላሹ መጡ። መጠራጠር ሰፈነ። በተለይ ሜዳ የነበሩ ሠራዊትን በመመለስ ሂደት ውስጥ ችግሮች ነበሩ። በዓለማቀፍ ደረጃ በተለመደው መልክ ማቀናጀት አልተቻለም። መንግሥት ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችም ይሄ ነገር ተግባራዊ እንዳይሆን ሲሠሩ ነበር።

ይኸውም ከለውጡ በፊት ምንም ሰራዊት ሳይኖራቸው ዝም ብለው ጠብመንጃን ከውጭ አስገብተው በሕገ ወጥ መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው የሚሉ ከመንግሥት ሰዎች ነበሩ። በዚህም ሳቢያ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ ቀረ። በኤርትራ በኩል የገቡትም ቢሆን ካምፕ ውስጥ ትንሽ ችግር ገጥሟቸው ነበር። ያ ደግሞ ትግል ሜዳ ላይ የነበሩት እንዳይመለሱ ችግር ሆነባቸው።

እንደዚህ እያለ ግንኙነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ አየወረደ እየወረደ መጥቶ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደረስን። እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ እና ሌሎች ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለው መገፋት በፊት ወደ ነበርንበት ቦታ እንዳይመለሱ ስጋት አለን።

በኦነግ አመራሮች መሀል የሥልጣን ሽኩቻ አለ። በተለይ የምዕራብ እና የምሥራቅ ኦሮሚያ አካባቢ አባላት እየተባለ ይህ ነገር እውነትነት አለው?
አመራሮች ላይ ያለው ከአካባቢ ጋር ከተገናኘ አይደለም። ከዚህም በፊት የነበሩት መሪ የወለጋ ሰው ሆኖ እያለም መገፋፋቶች ነበሩ። የአሁኑ ደግሞ በጭራሽ ያ ስእል የለውም። ስለዚህ ያለው መሠረታዊ ልዩነት የርዕዮተ ኣለም ነው።

እንደዚህ ብለው የሚያነሱት ሰዎች ለማሳያነት የሚያነሱት አንድም የምሥራቅ ኦሮሚያ ሰው ኦነግን መርቶት አያውቅም ብለው ነው?
ጉባኤዎች ስንት ጊዜ ነው የተካሄዱት ብለህ ብትወስድ የተወሰነ ጊዜ ነው፤ ከአራት ያልበለጡ።በትጥቅ ትግል በነበርንበት ጊዜ ጉባኤ የሚደርገው በተራዘመ ጊዜ ነው። በዚህም አንድ ሰው አንድ ጊዜ ከተመረጠ ሌላ ጉባኤ ተሰናድቶ እስኪመረጥ ረጅም ዓመት ይወስዳል። በነገራችን ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በ1968 ሲመሠረት የመጀመርያው ሰው የተመረጠው ከወለጋ አይደለም።
መገርሳ መሪ የሚባል የመሃል ሰው፣ ከቱለማ ሄዶ ባሌ ያደገ ድርጅቱን መርቶት ያውቃል።

ደርግ ሊወድቅ ኹለት ዓመት ሲቀረው፣ 1998 ትንሽ ጉባኤ ሞቃድሾ ላይ ተደርጎ ነው ዳውድ የተመረጠው። ዳውድ ኢብሳ 22 ዓመታት በሊቀመንበርነት እያገለገለ ነው። በእርግጥ የአንድ ሰው ረዘም ላለ ጊዜ ኃላፊነት ላይ መቆየት በምዕራብ ሆነ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ጥያቄ ሲያስነሳ ይሰማል። ግን ችግሩ ጉባኤ በወቅቱ ለማድረግ መቸገራችን ነው። ትግል ላይ ሆኖ በሰዓቱ ጉባኤ ማድረግ ፈታኝ ነው።

ስለዚህ የአካባቢ ሰው የመሆን አለመሆን ጉዳይ አይደልም። የመጀመሪያው አመራር እኮ የምዕራብ ሰው አይደለም።
በኦነግ ውስጥ አዲስ ትውልድ ወደ ፊት የማምጣት ጉዳይ ታስቦበት የሚያውቅ አይመስልም። አሁን ድርጅቱ ሲመሰረት የነበረ የ1960 ትውልድ ነው መንበሩን የያዘው። ይህ ለምን ሆነ?
ይሄ በኦሮሞ ብቻ አይደለም፤ በሁሉም ውስጥ ያለ ነው። በኦሮሞ ለሁሉም ትውልድ ሕግ ተቀምጧል። ለሁሉም። በገዳ ስርዓት አንድ ልጅ ሲወለድ እስከ ስምንት ዓመት ድረስ ከእናቱ ጉያ አይወጣም። ከስምንት እስከ አስራ ስድስት የተወሰነ የሥራ ድርሻ አላቸው። ከአስራ ስድስት እስከ 24 በገዳ ስርዓት ውስጥ ገቡ ማለት ነው።

ከ24 አስከ 32 እድሜ ያለ ትውልድ የራሱ የልምምድ ጉዞ አለው። የተለያዩ የውትድርና የፖለቲካ የመሳሰሉት። ከ32 እስከ 40 ዓመት የጠነከረ ትውልድ ይሆንና ከ40 ዓመት በላይ አገር የማስተዳደር ደረጃ ላይ ደርሳል። አገር የሚያስተዳድሩት ባህል ላይ ያለው ትውልድ ነው። ነገር ግን ይሄ አልተጠበቀም። በኦሮሞ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ አሁንም የ60ዎቹና የ70ዎቹ ናቸው መሪነቱን የያዙት።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተቆጣጠረው አንድ ፓርቲ ብቻ ሁሉን ነገር መቆጣጠር አለበት የሚል እንጅ ሌሎችን ያሳተፈ አይደለም። በገዳ ስርዓት ቀኑ ሁሉ ተሰልቶ፣ በኦሮሞ አስቴሮኖመርስ መሰረት በስምንት ዓመት ነው የሚመረቁት። ያች ወሯና ቀኗ ተቆጥራ አንድ ቀን ካለፈች ነውር ነው። ያንን ወደ ዴሞክራሲ ትግል ለመቀየር ትግል ይጠይቃል። በኦሮሞ ነፃነት ግንባርም ብዙ ውድቀቶችና መነሳቶች ነበሩ። በዚያ ምክንያት የተረጋጋና ለረጅም ጊዜ አብሮ የመቀጠል ልምድ አልነበረም።

በኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ነበር ጉባኤዎች ይካሄዱ የነበረው። በጉባኤዎቹም ላይ ኢትዮጵያ ያለው አባል ለመሳተፍ እድል አልነበረውም። ሌሎች አመራሮችም ቢሆኑ ከውጭ መጥተው ነበር በኤርትራ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት። ምናልባት በሚቀጥሉት ወራት ትልቅ ኮንፍረንስ አድርገን ወጣቶችን ወደ ላይ እናመጣ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።

እንዳልከው በኃላፊነት ላይ ሆነው ሳይሠሩ ያረጁ አሉ። በዚያው ልክ ደግሞ ወደ ኃላፊነት መጥተው ያልተሳተፉ አሉ፤ እሱን እንቀበላለን። ሕዝቡ አዳዲሰ ሰዎችን ወደፊት አምጡ እያለ ይጠይቃል። ድርጅታችንም ለውጥ ላይ መሆኑን ገልጸናል። ከምናደርጋቸው ለውጦች ወስጥ አንዱ አዳዲስ ሰዎችን ወደ ፊት ማምጣት ነው። ኦሮሞ አቅም ያላቸው፣ ብዙ መሥራት የሚችሉ አሉ። ወደ አምራርነት ቢመጡ ብዙ መሥራት ይቻላል። ድርጅታችንም እየታገለለት ያለው ጉዳይ ነው።

ከቀድሞ አመራሮች ጋርስ ያላችሁ ግነኙነት ምን መልክ አለው?
የቀድሞ አመራሮች የሉም። መሥራቾቹ እንደ እነ ባሮ ቱምሳ፣ እነ መገርሳ በሪ ያሉበት ነው። እነሱ አሁን ተሰውተዋል። በሕይወት የሉም። በሕይወት ያሉት መሥራቾች እንደ አቶ ሌንጮ ለታ ነበሩ። አሁን እነሱ በደርጅቱ አመራርነትም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ የሉም። የመጀመሪያውን የፖለቲካ ፕሮግራም የጻፉት ባሮ፣ ዲማና ሌንጮ ነበሩ። ከሦስቱ ኹለቱ በሕይወት አሉ፤ ግን ከእኛ ጋር በአመራርም በድርጅቱም የሉም።

ትግል ሜዳ ወይም አስመራ ብዙ ሥራ የለም። አሁን ላይ ግን በቅርበት የሚሠሩ ብዙ ሥራዎች አሉ። ይሄንን ሥራ ባለን ልምድ ለመሥራት ወጣቶችን ማደራጀት አለብን። ለውጥ ቀላል አይደለም፤ አመራር ለመቀየር ብዙ ይፈልጋል። የአመራርነት ቦታ ሽግግር ባህል መለመድ አለበት። ነገር ግን አመራርነትን በሙሉ መልቀቅ ጥሩ ውጤት አያመጣም። አሻጋሪ ያስፈልጋል።

ባለፈው በነበረው መግለጫ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ ለመሥራት ጥሪ አቅርባችኋል ምን ማለት ነው?
ቀደም ሲል የነበረው ፖሊሲ ነው፤ አዲስ አይደለም። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የፖለቲካ ፕግሮራሙን ሲቀርጽ ወዳጆችን የትግል አጋሮች ብሎ የሚጠቅሳቸው አሉ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጋር ተመሳሳይ ፕሮግራም ያላቸው የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ፓርቲ የትግል አጋሮች ናቸው ብሎ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ተቀምጧል።

ኤርትራ እያለን ትብብር ለነፃነትና ዴሞክራሲ የሚል ጥምረት ነበረን። አሁን አገር ወስጥ ከገባን ደግሞ ትብብር ለኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ኅብረት የሚል እንደ ኦብነግ የተካተቱበት ጥምረት ፈጥረናል። ከኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ጥምረት ለመፍጠር ቢቻል ደግሞ ወደ ውህደት ልንሄድ የምንችልበት አቅጣጫዎች ነበሩ።

ይህን አይነት ጥሪ ወይም የአብረን እንሥራ ጥያቄ ከሕወሃት በኩል ቢደርሳችሁ፣ አብራችሁ መሥራት ትፈልጋላችሁ?
ከሕውሃት ጋር ለመሥራት ትልቅ ችግር አለ፤ ምከንያቱም ያለፉት ታሪኮች አሉ። የነበረው ታሪክ የግጭት እና የልዩነት ነው። ቅድም ሲነሳ እንደነበረው ብዙ የሚባል ጉዳት ደርሷል፤ በሕወሃት። ሕወሓት የፀደቀውን ቻርተር ቢያከብር እና ኦነግን ባይገፋው ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ያን ያክል አይከብድም ነበር።

ወደ ተረጋጋ መንግሥት ግንባታ ልንሄድ እንችል ነበር። ሕወጣት የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ (የራስን እድል በራስ የመወሰን የምንለውን) ጥያቄ ለመመለስ ጊዜ ነበረው። 27 ዓመት ጊዜ ነበረው። አልተጠቀመበትም። ዛሬ ተመልሶ ስለ ፌዴራሊዝም፣ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች መብት ተቆርቋሪ ቢሆን እውነታው ላይ ጥያቄ ያስነሳል። ምናልባት ተገፍቶ ወደ ክልሉ ስለሄደ ይሆን? እና አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ፈልጎ ነው? የሚለውንም።

ስለዚህ ያለፉት ነገሮችን ሁላ ሂሳብ ሳይወራረድ ዝም ብሎ ሄዶ መቀላቀል ሁኔታ አይኖርም። ያለፉትን ስህተቶች ንግግር ተደርጎ መቀበል አለበት። የተፈፀሙ በደሎች መካስ አለባቸው። ቢያንስ ቢያንስ የኢትዮጵያን ህዝብ በአጠቃላይ ሕወሓት ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ምናልባት የዛኔ ቁጭ ብለን መነጋገር እንችል ይሆናል።

እንጂ ለኛ የዘላለም ጠላት አይደለም። ነገር ግን ችግሮቹ ሳይፈቱ እና መግባባት ላይ ሳይደረስ አንድ ሰልፍ ውስጥ መግባት አያስኬድም የሚል አቋም ነው ያለን። ስለ ቀጣዩ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መተላለፉ ግዴታ መሆኑን እንረዳለን። በሽታውም አዲስ እንደመሆኑ፤ መተላለፉ ላይ አቋም ሰስደናል። ግን ሲተላለፍ የተወሰነ ጊዜ መቀመጥ አለበት።

ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሆን ካልቻለ እና ከተራዘመ ደግሞ ለስድስት ወርም ከሆነ፤ ለስድስት ወር ማለት ከዛም ከጨመረ ትክክለኛ ምን ያህል ጊዜ ይራዘማል የሚለውን ጊዜ ማሳወቅ ተገቢ ነው። ላልተወሰነ ጊዜ ተብሎ መተላለፍ የለበትም። አሁን ባለው ሁኔታ አስር ዓመትም ሊቆይ ይችላል። ውሳኔውም ሕጋዊ አካሄድ አልተከተለም። ምክያቱም መሆን የነበረበት ምርጫው ራሱ ሲራዘም ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማወያየት ነበረባቸው።

ስለ ምርጫ ገዢው ፓርቲን ብቻ አይደለም የሚመለከተው። ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንጂ። ነገር ግን ይሄ ውሳኔ ለዚህች አገር ‹እኔ ብቻ ነው ያለሁት፣ እኔ ብቻ ነኝ የቆምኩት› የሚል ነዉ የሚመስለው። አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው ይካሄድ አይካሄድ አይታወቅም። ስለምርጫም ተነስቶ አይወራም። ሚዲያዎችም ተቀይረዋል (የመንግሥት ሚዲያዎች) እንደ ከዚህ ቀደሙ ተፎካካሪ ፓርቲዎችንም አቅርቦ ማወያየት እና መጠየቅ አቁሟል።

ይሄም ማለት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፅ በኮሮና ቫይረስም ይሁን በሌላ አዝማሚያ ተገድቧል። ሚዲያው ላይ አሁን የብልፅግና ፓርቲ አባላቶች ደጋፊዎች እና ካድሬዎች ይሄ መሆኑ ደግም መልሶ አገሪቷን ወደ ግጭት ነው የሚመራት። ፓርቲን ከፓርቲ ያጋጫል፣ ከሕገ መንግሥቱም ጋር ያጋጫል።

ከዛም ባለፈ ፖለቲከኞችን ማሰር ተገቢ ያልሆነ እና የሚያሳስብ ነገር ነው። ወደ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ እንሄዳለን እያልን የዲሞክራሲ ተቋማት ተብለው እየተገነቡ ይሄ ተግባር ባለበት ሁኔታ ፖለቲከኞችን ማሰር ምን አንድምታ እንዳለው መገመት ቀላል ነው። መሆን ያለበት መንግሥትም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት መጀመር፣ የምርጫ ጉዳይ ተነስቶ መወራት አለበት።

እንዴት እናድርግ እና እንዴት ወደ ፊት እንሂድ የሚለው ላይ በጋራ ነው መወሰን ያለበት። በቁጥጥር እና ዲሲፒሊን ኮሚቴ ጉዳያቸውን አጣርቶ ለማእከላዊ ኮሚቴ እስኪያቀርብ ድረስ ነው። ይህ ማለት የስራ አስፈፃሚው ያደረገው ግምገማ አለ። ግምገማው ሲደመደም ሊቀ መንበሩን ተጠያቂ አድርጓል። ከነምክንያቶቹ ማስረጃዎችን በመደርደር።

የዲሲፒሊን ኮሚቴው አጣርቶ እስኪያቀርብ ማለት ላልተወሰነ ጊዜ ማለት አይደለም። የሚፈጀው ጊዜ አጭር ነው። ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠራል፣ ማጣራቱን አይቶ የውሳኔ ሐሳቡን ሊያቀርብ ይችላል። ያንን የውሳኔ ሐሳብ ማፅደቅ ይችላል፤ መጣልም ይችላል። ጠቅላላ ጉባኤውን ታኅሳስ 10 ነው የሚያከናውነው። ሆኖም በየጊዜው የተለያዩ ውሳኔዎች ይወሰናሉ፣ ተግባራዊ አይሆኑም።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here