ፍትህ ‹ለእነማን› ሴቶች!?

0
785

በአገራችን የፖለቲካ ጡዘት በብሔር በመቃኘቱ ‹በተለየ የተጠቀመ ብሔር› የሚለው ሐረግ ቤተኛና የተለመደ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ‹በብሔር የተጠቀመ› ሕዝብ ኖሮ አያውቅም። በአንጻሩ በብሔሩ የተጠቀመ ባለሥልጣንና የባለሥልጣን የስጋ ዘመድ እንዲሁም በብሔሩ ብቻ የተሰደደ፣ ውጣልን የተባለና የተጎሳቆለ ግን አለ።

ጭራሽ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ‹በተለየ የተጠቀሙ የእገሌ ብሔር ሴቶች› ሲባል ሰምቼ አላውቅም። ኖሮ ሳልሰማ ቀርቼ እንደሆነ ይቅር በሉኝ። እንዳልሰማሁ እርግጠኛ ስለሆንኩኝ ግን ልቀጥል። በከተማም ይሁን በገጠር፣ በየትኛውም ብሔር ውስጥ ሴቶች ተጠቃሚ የሆኑበት ጊዜ የለም። ከቦታ ቦታ መጠኑና ሁኔታው ይለያይ እንጂ፣ በኢትዮጵያ አይደለም በድፍን ዓለም በብዙ አካባቢዎች የሴቶች መብት ጉዳይ አጀንዳ ነው።

በቅርቡ በተለይ በውጪ አገራት የታሰሩ ግለሰቦች ‹ይፈቱልን!› ብለው ሰልፍ የወጡ ሰዎች ከያዙት መፈክር መካከል ‹ፍትህ ለሴቶች› የሚል ተመለከትኩ። በአንድ ጎን ‹ጎሽ! እንዴት ትዝ አላቸው!› አሰኝቶኛል። ሴቶች ሲጠለፉ፣ ሲደፈሩ ወይም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ ሲባል ካልሆነ ይህ ቃል ‹በአዘቦቱ› የፖለቲካ ጡዘት ውስጥ በአደባባይ መፈክር ሆኖ ብዙም አይታይማ!

ነገር ግን ‹ፍትህ› እና ‹ሴቶች› በሚሉት ቃላት መካከል የብሔር ሥም ተጠቅሷል። ያም እነዛ ሰዎች ፍትህ የሚጠይቁት በብሔራቸው ጥላ ስር ስላሉት ነው የሚል ትርጉም ይሰጣል። እንግዲህ ‹የእኛ ሴቶች…የእነርሱ ሴቶች!› የሚባል ነገር ሊመጣ፣ ጎልቶም ሊታይ ነው ማለት ነው?

በሁሉም ክልል የሚገኙ ሴቶች በብጥብጥ፣ ባለመረጋጋትና ሰላም ማጣት ተጎጂ ናቸው። ልጃቸውን ሁሉም መስዋዕት አድርገዋል፤ ቤተሰባቸው ተበትኗል። በአንድም በሌላም በኩል እንባቸው ፈስሷል። ‹የእገሌ ክልልና ብሐየር ሴቶች ግን የእገሌን ያህል አላለቀሱም፣ አልተጎዱም!› የሚል ካለ፤ እያፌዘ ይሆናል እንጂ ቃሉ በእውነት የሚረጋገጥ እንዳይደለ ግልጽ ነው።

በአገራችን በብሔር ሥም ትግል ከጀመረ የአንድ ትውልድ ዘመን ዘልቋል። አሸናፊ ግን እስከአሁን የለም፤ ተሸናፊ ላይ ግን ሁሉም ሊጠቀስ ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ ትግሉ ሥልጣን መያዝ እንጂ ደሃውን ከድህነቱ ማላቀቅ አይደለም። በዚህ ትግል ትምህርት ቤት የተገነባለት፣ ውሃና መንገድ መሠረተ ልማት የተሟላለት ብሔርና ክልል እንጥቀስ ብንል፤ እናገኛለን?

ግን የድሃውን እንባ፣ ሐዘን፣ መከራ፣ ችግርና ድህነት ይጠቀሙበታል። ቁስሉን አደባባይ እያሳዩ ያለቅሱና ይለምኑበታል። አንዳች ጠብታ ከተገኘች ግን፣ የሚካፈሉት እነርሱ ናቸው። ይህን ዓይነት ፖለቲካ ማመን ከባድ ነው። እናም ስጋቴ ወዲህ ነው። ‹ፍትህ ለሴቶች› ብሔርን ይዞ ከተነሳ፣ መቼም መፍትሄ የማያገኝ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል ባይ ነኝ። ከዚህም ወደባሰ ጥፋት ያደርሳል።
ሲከፋ ደግሞ አንድ ሰሞን እንደታዘብነው ሴቶች ሲደፈሩ ብሔራቸው ሊጠየቅ ነው? ሴቶች በብሔራቸው ምክንያት ብቻ የተለየ ጥቃት ሊደርስባቸው ነው?

ብዙ ጊዜ እንደ አገር ሕዝብ ድምጹን ተነጥቆ ያውቃል። ድምጽ ከኮሮጆ ብቻ የሚነጠቅ አይደለም። ድምጽ በ‹ተወካይም› ይነጠቃል። ንገርልን ያሉትን ትቶ፣ በነዛ ሰዎች ሥም የራሱን አጀንዳ የሚያስኬድ፤ ያ የሌሎችን ድምጽ እንደነጠቀ ነው። ወይም ለፖለቲካው ማጣቀሻ እውነተኛውን ጩኸት አላሰማም ማለትም ነው።

ብሔር ጠቅሶ ‹የእገሌ ብሔር ሴቶች› ፍትህ ያሻቸዋል ማለት ግን፤ ትክክል አይደለም። ‹መብቴ ነው!› በበዛበት ጊዜ፤ ‹መብታቸው ነው!› ባይ አይጠፋም። እርግጥ ስርዓትና ሕግ ሳይኖር፣ ግለኝነት ሲበዛ፣ ሰዎችን በአደባባይ ብሔርና ሐይማኖትን ጠቅሶ ‹ውጡልኝ!› ማለት፤ አልፎም መግደል ከ‹መብት› ሲማሰል እየታዘብን ነውና፤ መብታቸው ነው። ግን ትክክልና አግባብ ነው ማለት አይደለም።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here