ሰው የመሆን ልኬት እንዳይታጣ!

0
1065

ሰውነት በአካል ከሚታየው መገለጫውና መታወቂያው ባለፈ በሰብአዊነት ሚዛን ግዘፍ ይነሳል። ሰው ሆኖ ለመታሰብ ወይም ሰው ለመባል ሰው የመሆን ደረጃ የለም የሚሉት በኃይሉ ኢዮስያስ፣ በተጓዳኝ ግን ልኬት አያጣውም ሲሉ ያስረዳሉ። ከዚህም አንዱ ማስተዋልና ባለአእምሮ መሆን ነው ሲሉ፣ ይህን ከፍታም በማሳያ ይጠቅሳሉ። በአንጻሩም ከሰውነት ዝቅ የሚያደርጉትንም ጠቅሰው ሰው ከመሆን የሚያልቀው ልኬት እንዳይታጣ ሲሉ ከዕይታቸው ከፍለው አካፍለዋል።

ሰው ከእንስሳ የሚለየው በማሰቡና በማሕበራዊ አኗኗሩ ነው ይላሉ፣ የማሕበራዊ ሳይንስ ምሁራን። የቤተ እምነት ሰዎች ደግሞ ሰው አምሳለ ፈጣሪ የሆነ ፍጡር ነው በማለት ይናገራሉ። ኹለቱም በአንድነት የተሰፉበትን ሰበዝ ስንመዝ የሰው ልጅ ከፍጡራን ሁሉ የተለየ ብቻ ሳይሆን የላቀ ፍጡር መሆኑን አሰምተው የሚናገሩበትን ማዕሰረ ነገር እናገኛለን። ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ባለ አዕምሮ እንስሳ ነው። ይህ በእውነትም የሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ቢወድም ቢጠላም የሚቀበለው “ሐቅ” ይመስላል።

እርግጥ ሕልውና እግዚአብሔርን (የእግዚአብሔርን መኖር) ወይም የፈጣሪን መኖር የማያምኑ ቢኖሩም እንኳ የሰው ልጅ አዕምሮው የሠለጠነ እንስሳ (rational being) እንደሚያሰኘው ይስቱት አይመስለኝም። እንዲያውም አጬኸው ባያስተጋቡት!!! አዎ ሰው ሰው ነው፤ አይወጣም አይወርድም!!! የሰው ንዑስ በቅርቡ እንደሰማሁትም የ”ሰው ጷግሜ” እንዳይኖር ሰው ነኝ የሚል ፍጡር ሁሉ ሌላውንም በዚህ እንዳይበይን አዕምሮው ይቃኘዋል። ሰው ሆኖ ለመታሰብ ሰው የመሆን ደረጃ ፈጽሞ የለም። ሰው መሆንን ተፈጥሮ እንደ ፍጡርነት (ወዳ በወላጆች፣ ተገዳ በፈጣሪና በምድራዊ ሕግ) የተቀበለችው ገና በእናት ማሕጸን ሳለ ነው፣ የአንዱን ሰውነት የካደ ራሱን የካደ ነው።

ሰው የመሆን ደረጃ ባይኖርም ቅሉ ልኬት ግን አያጣውም፤ የሰውነት ልኬት! ወደ መጀመሪያው ጠቃሻችን ስንመለከት እንዲህ ነው፤ የሰው ልጅ አገናዛቢ/ ባለአዕምሮ መሆኑን ቀድመን እንጠቅሳለን። ይህ አዕምሮአዊ ፍጡር እንግዲህ በተቀረው ሁሉ ፍጥረት ላይ በአዕምሮው ይሠለጥናል፤ በቅንነት።

በቀሪው ዓለም ፍጡራን ላይ የሠለጠነ ይህ ፍጡር ታዲያ አሠለጣጠኑ በአስተውሎትና በቅንነት ሊሆን ግዱ ነው። ለራሱ ሕላዌ ሲል ማለት ነው። በሌላው ፍጡራን ላይ በሠለጠነበት አግባብና ሁናቴ ግን በምንም መልኩ በሌላ ሰው ላይ ሊሠለጥን አይገባውም። ለፍጡራኑ የራራበት ሐሳብ የፍጥረት ሐሳብ እንጂ የስብዕና ስላይደለ።

የሰው ልጅ ለሰው ርሕራሔውን የሚያሳይበት መንገድ ለእንስሳ ከሚያሳይበት መንገድ ፍፁም ተፃራሪ ነው። እንስሳን የራሱ (ንብረት) አድርጎ በሕይወቱ፣ በአካሉ፣ በኑሮው፣ አስተዳደጉ ላይ ፍፁማዊ ጌታ ሆኖ ሊኖር የመቻሉን ያህል እንደራሱ ባለ የሰው ፍጥረት ሰው ላይ ግን ያንን ሊከውን አይቻለውም። በተለይ በሕይወቱ ላይ በፍትሕ አደባባይ እስካልተበየነበት ድረስ አንድ ሰው በሌላ ሰው ነፍስ ላይ ሊሠለጥን ምግባርም አይደለም።

እንዲያውም በዚህ በኻያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የአንዳንድ አገራትን የፍትሕ መዛግብታቸውን ስንፈትሽ የሞት ብይን እንዳይሰጥ በመወሰን የሞት ቅጣት ማንሳታቸው ሰው (በፍትሕ አግባብ ቢሆን እንኳ) በሰው ነፍስ ላይ እንዳይሠለጥን መትጋታቸውን ልብ ይሏል። ያም ሆኖ ይኸኛውም እሳቤ የራሱ ጠለስ ሳይኖረው አይቀርምና ፍጹም የስብዕና ዕሴት ተደርጎ ይወሰድ ዘንድ ተገቢ አይመስልም።

የሰው ልጅን ሐይማኖት/ ዕምነት ያለው ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ መኖር የማይስማማው ሰው ጭምር በአንድ ቋሚ የመርህ እሳቤ ላይ በአብሮነት ይፀናል። ‹ለአንተ እንዲሆንልህ የምትሻው መልካም ለሌሎችም ይገባቸዋል፤ በአንተም ላይ ሊሆን የማትወደው ክፉ ነገር ደግሞ በሌሎች ሰዎች ላይ ትፈጽመው ዘንድ አይገባም።› በሚለው። አዎ! ሌሎች ከአንተ አቅምና ፍላጎት ውጪ በሆነ ጉልበታም ኃይል መጎሳቆልና በደል ቢደርስባቸው ምን ልታደርግ ትችላለህ? ቁምነገሩ ያንን በደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንተው ፈፃሚ ወይም አስፈፃሚ በመሆን ተሳታፊ አለመሆንህ አንድ ነገር ነው።

በእውነትም እነዚህን ወገኖች የመርዳትና የመታደግ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ላይኖርህ ይችላል። በዚህ ግዜ ታዲያ በአንድ ነገር ልታግዛቸው ትችላለህ፤ በመንፈስ/ በሐሳብ (emotional support)። ሰው ነህና መቼም አንድን ነገር ልታከናውን ከመነሳትህ ቀድሞ የምትሠራውን ነገር አስበህ ነው፤ ይኸው ነው እዚህም የሚያስፈልገው። የሰውነት የመጀመሪያው ልኬት ስለሰዎች ሰብዓዊነት ከመቆርቆር አልፎ (እነሱ ማሟላት ሳይችሉ የቀሩ ነገሮቻቸውን እነሱን በመሆን) ስለተከታይ ነገሮቻቸው ማሰብ ነው።

‹‹ራስሕን ስትታመም ከተሰማህ በሕይወት አለህ ማለት ነው፤ የሌሎች ሕመም ከዘለቀህ ግን እውነትም አንተ ሰው መሆንክን ታረጋግጣለህ›› የሚለው አባባል በምልልስ የምናነበውና የምንሰማው እውነትነት ያለው ብሒል ነው። ይህንን ድንቅ ደግሞ (ጤናንና ዕድሜን አብዝቶ ይስጣቸውና) አንዳንድ መልካም ሰዎች ሲኖሩት አይተናል፤ እያየንም ነው።

በተለይ በዚህ አስጨናቂ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት አንዳንድ የመልካም ሰው ተምሳሌት ግለሰቦችና ይህን አስጨናቂ ግዜ ረዳት አልቦ በሆኑ አረጋውያንና የዕለት ጉርሳቸውን ዕለት በዕለት በመሯሯጥ ያገኙ የነበሩ ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ችግር ፈጥነው በመረዳት፣ በመልካም ሐሳብ በመነሳሳት ተባብረው ቡድንን የፈጠሩ የወጣቶች ስብስብን በየሰፈሩ፥ በየማሕበራዊው መገናኛ ላይ ማየትን ችለናል።

አገራችን በዚህ ጊዜ ፖለቲካና ወረርሽኝ ከፍተው በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ሰቆቃን እያስከተሉ የምናይበት የፈተና ወቅት ላይ ትገኛለች። የርዕሰ ከተሞቿ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ የሚያዘው ሰው በአስጊ ሁኔታ ቁጥሩ እየናረ መጥቷል። ሆኖም ከጥንቃቄ አንጻር አዲስ አበቤዎች ግን ዳተኝነትን እያሳየን ነው። በተናጥል ሆነ በቡድን በየሰፈራችንና በማሕበራዊ ድረ-ገጾች ሰዎችን ከተለያዩ የዓለም ንፍቆች እና ማዕዘናት በማስተባበር የወገንን ችግር ለመቅረፍ የባተልነውንና እየለፋነው ያለው ነገር በምግብና በአልባሳት ዙሪያ እንጂ የጤና ቅድመ ጥንቃቄን ችላ ብለነዋል የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ።

ሐቅ ነው! የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገው ቅድመ ጥንቃቄ ከመንግሥት አስተዳደር አንስቶ እስከ ነዋሪው ድረስ እየላላ መጥቷል። ያም ሆኖ የአዲስ አበባች ወጣቶች የማሕበራዊ ተሳትፏቸው በገንዘብ ቢለካ የትየለሌ ሊሆን መቻሉ እሙን ነው።

በሚገርም ሁኔታ በተለይ በሰፈር ቡድን ውስጥ ታቅፈው በኑሮው ደረጃ በጥቂቱ ሻል ያለ ነዋሪን በተለያየ የምግብና አልባሳት ቁሳቁስ እንዲረዳ የአካባቢውን ማሕበረሰብ በማስተባበር እየተሯሯጡ የምታያቸው ራሳቸው ቋሚ ገቢ ሆነ ሥራ የሌላቸው፣ ጉብዝናቸውን (ወጣትነታቸውን) ገንዘብ አድርገው ጎስቋላ አረጋውያንንና በተለያየ ምክንያት በሕመም፣ ረዳት ልጅ በማጣትና በሌሎችም ምክንያቶች በየቤታቸው የሚገኙ ወገኖችን ለመታደግ የተሰለፉትን የአዲስ አበባ ልጆችን ነው።

ከእነርሱ ጋር በዚህ የእርዳታ ማሰባሰብ ጊዜ ከተገኘህ እርስ በእርስ ‹ውረዳ አንተም ራስህ!› ‹ጨላ ወዲህ በል!› ‹ገፍትር!› ‹አዋጡ እያሉ መዞር ብቻ…!› ሲባባሉና ከኪሳቸው አዋጥተው ሌላ የተጓደለ የምግብ ቁሳቁስ ገዝተው ሊሞሉ ከየአንዳንዳቸው ደግሞ ሰብሰበው የተፈለገውን ሲያሟሉ ‹‹እነዚህ ሰዎች ይህንን አድካሚ የማስተባበርና በየቤቱ እየዞሩ የማደልን ሥራ እንደታላቅ አስተዋፅኦ ሳይቆጥሩት ቀርተው ነው ዳግም ካለቻቸው ‘መገፍተራቸው?!’›› ትላለህ።

ይኸውልኽ የሰውነት ሌላው እፁብ ልኬት ይኸውልህ! ‹‹…ያላትን ሁሉ ሰጠች!›› ሲል አይደል የመሰከረላት፤ መሲሁ በታላቁ መጽሐፍ ላይ።
ወገኔ ሰው ስለመሆንህ ምስክር መቁጠርን አትድከም። ሰው ነኝ ለማለት ማሰብ ይቀድማል። ሰናይ ሐሳቦችን ልታስብና ላንተ ሊሆን የምትሻው መልካም ለሌላው ይገባው ዘንድ የምታምን፥ አንተም ላይ ሊሆን የማትፈቅደውን ግፍ በሌላው እንዳታደርግ ሰው የሆንክበት አዕምሮ ያግድሃል።

አዕምሮህ ከማሰላሰሉ ሲዘገይና በእገሌ ሰላማዊ ሕላዌ (ኑሮ) ላይ መብሰልሰል ጀምረህ ‹እሱ እዚህ ለምን ይኖራል?!› የሚል የሰው ያይደለ የአውሬ ደመ-ነፍስ ሹክ ካለህ ማሰብህን እየተነጠቅህ ነውና ራስህን በፈጣሪ ቃል ገስፀው። አልያም በሰብአዊ አመክንዮ ግራው።

እንጂማ ‹ኢትዮጵያ የምትባል አገር ብትንትኗ ካልወጣ…›› ‹‹ከእንትን ካልተወለድክ የኔ ወገን አይደለህምና ልትኖር አልፈቅድልህም።›› ‹‹…ቤተ እምነትህ እና አምልኮህ የኔን ስለማይመስል አንተ መ’ሸለት፥ አካልህ መሰባበር፥ መሳደድ፥ ቤተ እምነትህም መቃጠል አለበት!›› በሚል ከቤተ እምነትህ አስተምሕሮ ውጪ በመሆን ይህንን እኩይ ድርጊት ይሁነኝ ብለህ የምታደርግ ከሆንክ፣ የጆርጅ ኦርዌል ሽሙጣዊ ድርሰት ‹Animal Farm› ላይ የተገኙትን በኹለት እግር የተቆሙ እንስሳት ውስጥ ራስህን መድበሀል።
ይህ መጽሐፍ “የእንስሳት ዕድር” በሚል በአማርኛ ትርጉም ቀርቧል። የእንግሊዝኛውን ግን ከመረጃ-መረብ ላይ ታገኙታላችሁ።

ዋናው ቁምነገር እዚህ መጽሐፍ ላይ የተሠሩት ገጸ ባሕርያት የወቅቱን የአገራችንን ‹ጽንፈኛ› ፖለቲከኞችንና ጭፍን ተከታዮቻቸው ጋር ቃል ከግብራቸው መመሳሰላቸው ነው። እዚህ መጽሐፍ ላይ ‹እኩል› እና ‹የበለጠ እኩል› የሚለውን ዕሳቤ ስታይ፣ ‹ይህ ጸሐፊ እንዴት ይህችን የወቅቱን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ትናንትና ላይ ቆሞ አያቸው?!› ስትል ትደመማለህ።

ታዲያ እኚህ ‹የበለጠ እኩል የሆኑቱ› እንስሳት ‹ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው!› የተባሉትን ‹እንስሳት› እንደፈለጉት ማድረግና ማስደረግ፥ እንደተናገሩት ማስከወን ይችላሉ። ‹ኑ!› ሲሰኙ አቤት፤ ‹ሒዱ!› ሲባሉ ደግሞ መንጋጋት ነው እንጂ ጥያቄ ብሎ ነገር የለም። ታዲያ ስታስተውል እነዚህ ‹የበለጡ እኩል እንስሳት› የእንስሳት ደረጃ (standard) አላበጁም ትላለህ?!

ሊቃውንት፤ ‹ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል› ሲሉ ተክለ ቁመናውን ብቻ አይደለም፤ የዶሮ ዘሮችም በኹለት እግሮቻቸው የተቆሙ እንስሳት ናቸውና በሰው ግብር (በሰብአዊ ማንነትህ) እስካልተገኘህ ዶሮ ከመሰኘት አትተርፍም። ጭንቅላትንም መሸከምህ አዕምሮህን ለማሰቢያነት በአመክንዮ (ቢያንስ ሕገ – ልቦና በሚኖርበቱ ዘመን ልክ) ካላንቀሳቀስከው በየማሕበራዊ አውታሩ ላይ ባለ”ግብዳ” ጭንቄዋ ጧቷን፥ አይኗን ወይ ከንፈሯን ለፌዝ የምትወነጭፈው አሻንጉሊት “emoji” ወገን መሆንህን ከማረጋገጥ አትተርፍም።

ሰው ስትሆንና በአምሳሉ ተፈጥሬአለሁ ስትል የሰውኛ ባሕርይ ይኖርሃል። ከወገኔ አልተወለደም ባልከው ሌላ ሰው ላይ ለግብር አይደለም ለዐይን የሚያስፈራ ስለት መዝዘህ ሊከላከልህ ዝግጅቱም፥ አቅሙም ሆነ፣ ታደርገዋለህ የሚል ዕምነት በሌለው ሰላማዊ ሰው ሕይወት ላይ የሠለጠንክ እለት አንተ ሰብዓዊነትህን በራስህ ያረገፍክ ነፍሰ-በላ (cannibal) ሆነሀል።

ይህንን ያንተን አረመኔያዊ ድርጊት ራሱ ማውሳቱ እንዴት ያሳቅቃል! አረመኔነት እንዴት ከቶ ይለመዳል?! በምንስ ጥቅሙ ተኮርጆ ይተገበራል?! አንተ ራስህን (ከሰዎች ሰውነት/ ሰው መሆን) አልቀህ ደረጃ የሰጠህ ዕለት ምንም ነገር በሌሎች ሰዎች ላይ ለማድረግ ክሽፍ ሰበብ እያበጀህና ከሰብዓዊነት ማማ ላይ ቁልቁል እየተምዘገዘክ ሲሆን በግብር ስትገልጠው ደግሞ ከማሕበረ እንስሳት መካከል መገኘትህን ታረጋግጣለህ።

የሰው ልኬት እንጂ የሰው ደረጃ እንዳይኖረው ልቦናህ ማስተዋሉን ተነጥቋል። ባይሆንማ ኖሮ ኹለተኛው የዓለም ጦርነትን የጀመሩት ናዚዎች “Arian Race” በማለት የነዙት የበላይነትን ሰይጣናዊ የዛር መንፈስ አይጣባህም ነበር። የሚደንቀው አንተ ኮራጅነትህን እንጂ በነሱ እሳቤ አንተም እንደሌሎቹ ያለልዩነት ‹ወራዳ ባሪያ/ ጥቁር (filthy negro/ black)› ተደርገህ መታሰብህን ያለማስተዋልህ ከስብዕና የተዋረደ “የእንስሳነትህ” ግብር ነው ብለው ሰብዓዊ ፍጡራን በአመክንዮ ይሞግቱሃል።

መሰል ኢ-ሰብአዊ ግብር ሠልጥኖባቸው ያሰየጠናቸው ፍጡራን ይህ እንዲሆን ወደው አይመስልም፤ ሰው መሆን አቅቷቸው ቢሆን እንጂ! ሰው መሆን ውጣ ውረድ የተሞላበት ኑሮና ከሞት በኋላም እንኳ የሚዘልቅ ዋጋና ፍጻሜ አለ፤ ክብር ይሰኛል! ሰው መሆን ፈተና ሆኖባቸው በእንስሳት ግብር ራሳቸውን ለገለጡቱ እና ወደፊት እየቀደመ ሰብዓዊነት እየተፈተነ እንደሚመጣ ለማመላከት ይመስላል ከያኒው፦

‹‹እኔስ ኖሬያለሁኝ ሲከፋኝ ሲደላኝ፣
ከእንግዲህ ተወልዶ ሰው ለሚሆን ይብላኝ።›› ሲሉ የተቀኙት። ሰብዓዊነት ይቅደም!

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here