ቦሌ መንገድ ቅርንጫፍ ለገበታ ለሀገር ተከፍቶ የነበረው አካውንት ሐሰተኛ አለመሆኑ ተገለጸ

0
1129

በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ይፋ የተደረገውን የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለመደገፍ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ መዋጮ የሚያደርግበት የባንክ የሂሳብ ቁጥር በአዲስ አበባ ቦሌ መንገድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ተከፍቶ የነበረው ሀሰተኛ ነው የተባለ የገቢ ማሰባሰቢያ የሂሳብ ቁጥር ሀሰተኛ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የሂሳብ ቁጥሩ(አካውንት) በሀገር ደረጃ ለህዝብ ይፋ እንዳልነበር አስታውቆ፤ ነገር ግን በወቅቱ ሀሰተኛ የሂሳብ ቁጥር በገበታ ለሀገር ስም ተከፍቶ ተገኘ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑንና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማንኛውም የሂሳብ ቁጥር መቼ ተከፈተ፣ ማን ከፈተው፣ ለምን አላማና መቼ ይዘጋል የሚለውን የሚከታተል ባለሙያ ስላለ ሀሰተኛ አካውንት የለም ሲል አስታውቋል።

ባንኩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በንግድ ባንክ ቦሌ መንገድ ተከፍቶ የነበረው የገበታ ለሀገር ገቢ ማሰባሰቢያ የሂሳብ ቁጥር(አካውን) ሰኞ ነሐሴ 18/2012 እና ማክሰኞ ነሐሴ 19/2012 ለኹለት ቀናት ክፍት ሆኖ በሦስተኛው ቅን ማለትም ነሀሴ 20/2012 በገንዘብ ሚኒስቴር ፍላጎት መዘጋቱን አስታውቋል። ነገር ግን የሂሳብ ቁጥሩ ለህዝብ ይፋ አለመደረጉን ባንኩ አስታውሷል።

በወቅቱ ቦሌ መንገድ በገበታ ለሀገር ተከፍቶ የነበረው ኹለት የሂሳብ ቁጥር ሲሆን አሁን ላይ የሂሳብ ቁጥሩ ዝግ መደገሩን የባንኩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የአብስራ ከበደ ጠቁመዋል። ለኹለት ቀን ክፍት ሆኖ በቆየው የሂሳብ ቁጥሩ ከባንኩ ሰራተኞች ተሰብስቦ የነበረው የገንዘብ መጠን 4 ሺህ 500 ብር እንደነበርም የአብስራ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። የሂሳብ ቁጥሩ መዘጋቱን ተከትሎ የተሰበሰበው ብር ወደ አዲስ የሂሳብ ቁጥር ገቢ መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል።

በምትኩም የገንዘብ ሚኒስቴር ባቀረበው አማራጭ ሀሳብ በኢትዮጰያ ንገድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ አዲስ የገበታ ለሀገር የሂሳብ ቁጥር መከፈቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የአብስራ ከበደ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሂሳብ ቁጥሩ የተዘጋበት ምክንያ የገንዘብ ሚኒስቴር ለገቢ ማሰባሰብ ቀድሞ ተከፍቶ የነበረው ቦታ ምቹ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።

የባንኩ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ አንደገለጹት የገበታ ለሀገር እንቅስቃሴ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ቀድሞ ተከፍቶ የነበረው የሂሳብ ቁጥር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት የስራ ኃላፊዎች፣ የማኔጅመንቶች፣ የዲስትሪክት ኃላፊውና የቦሌ መንገድ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ እንዲሁም ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ባደረጉት ሰምምነትና ፈቃድ እንደነበር ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ገቢ ማሰባሰቢያ ሂሳብ ቁጥሩ 100339911267 የሆነ “በገንዘብ ሚኒስቴር-ገበታ ለሀገር”/ Minister of finance-Dine Ethiopia` በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለአግልግሎት ክፍት ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና ሌላ ምንም አይነት ሂሳብ ቁጥር እንደሌለ ተገልጿል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪና በደቡብ ክልል ኮይሻ የፕሮጀክቱ አካል ናቸው። ለገበታ ለሀገር ፕሪጀክት 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። በትልቁ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር የ10 ሚሊዮንና የ5 ሚሊዮን ብር የእራት ግብዛ መዘጋጀቱን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ይፋ አድረገዋል።

እስካሁን በነበረው የገበታ ለሀገር የገንዘብ ማሰባሰብ መርሀ ግብር የተለያዩ የመንገስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን በማስተባበር የአንድ ወር ደምወዛቸውን እየለገሱ ነው ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here