በተለያዩ ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ፣በመንገድ ላይ፣ በልብስ መሸጫ (ቡቲክ) እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚስተዋለውን የድምጽ ብክለት ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ይተገበር ያልነበረው የምሽት የቁጥጥር ስራ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ለመጀመር ማቀዱን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ለአዲሰ ማለዳ አስታወቀ።
የቁጥጥር ስራው ቅዳሜ እና እሁድን በመጨመር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ተግባዊ እንደሚሆንም ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
የድምፅ ብክትን በተመለከተ አብዛኛው ጊዜ ከሕህብረተሰቡ የሚቀርቡልን ቅሬታዎች ችግሩ በብዛት የሚስተዋለው በምሽት ላይ እንደሆነ የሚገልጹልን ቢሆንም በእኛ በኩል ግን ቅሬታዎች ስለመጡ ብቻ ሳይሆን የድምጽ ብክለት አለባቸው ብለን የለየናቸው ቦታዎች በመኖራቸው የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር አቅደናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት በአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ቡድን መሪ ለሜሳ ጉደታ ናቸው ።
የቁጥጥር ስራውን ለመስራት ከዚህ በፊት ምሽት ላይ የቁጥጥር ስራውን ለመስራት የተመቻቸ ሁኔታ እና ለተቆጣጣሪዎች የአበል ክፍያ የማይፈጸም ቢሆንም አሁን ግን የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ለመክፈል መወሰኑንና በደብዳቤም ያሳወቀን በመሆኑ የምሽት ቁጥጥሩን አጠናክረን እንሰራለን ሲሉ ለሜሳ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የምሽት አበል ክፍያ ለማስፈቀድ ብቻ ከሦስት ዓመት በላይ እንደፈጀ ያስታወቁት ለሜሳ በዚህም ሳቢያ ስንሰራ የነበረውን የቁጥጥር ስራውን ሲያስተጓጉል ነበር ፤ አሁን ግን ስራውን መስራት የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
በምሽት የሚሰራው ይህን የቁጥጥር ስራውን ለመስራትም ከማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ የድምጽ ብክለት ለመቆጣጠር ብቻ የሚሰሩ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ከ400 በላይ እንደሆነም ለሜሳ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ምሽት ብቻ ሳይሆን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ መንገድ ላይ መኪና በማቆም ከፍተኛ ድምጽን በማሰማት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ለመቆጣጠር እንዲሁም የተለያዩ መደብሮችን ጨምሮ በልብስ መሸጫ መደብሮች (ቡቲክ)ና በየቦታው የሚሰሙትን አላግባብ ድምጾችን ለመቆጣጠር አጠናክሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይም ቀን ላይ ከተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚወጡ እና የድምጽ ብክለትን ለመከላከል የሚሰራው ስራ በአደስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን ከደንብ ጽህፈት ቤት ጋር ሥራዎቻችንን በመለየት በጋራ ሊያሰሩ በሚችሉ ነገሮች ላይም ተወያይተናል ብለዋል።
ምንም እንኳን የድምጽ ብክለት ቁጥጥር ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ለሙስና የተጋለጡ እንደሆነና እንደዚህ ዓይነት ቅሬታዎች የሚነሱ መሆናቸውን የሚያነሱት ለሜሳ እስካሁን በነበረው የቁጥጥር ስራ ላይ ምንም ዓይነት የስነምግባር ጥሰት ፈጽሞ የተቀጣ ባለሙያ ባይኖሩም የችግሩ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለማድረግ ከኹለት በላይ ባለሙያዎችን ወይም እስከ አራት ባለሙያዎች በማሰመራት የቁጥጥር ስራውን እንዲያከናውኑ ለማድረግ እንደታሰበም ነው ያስረዱት።
የድምፅ ብክለት የአየር ብክለትን ተከትሎ በዓለም ኹለተኛው የአካባቢያችን ብክለት ዓይነት ነው ሲሆን ይህንን የብክለት ዓይነት የሚፈጥረው ድምፅ ያልተፈለገና በሰው መረበሽን የሚፈጥር ማንኛውም ዓይነት ድምፅ ነው።
እንዲህ ዓይነት ድምፆች የሰዎችን የሕይወታችን መደበኛውን እንቅስቃሴን በመጉዳት፣ በማስተጓጉላሉ፣ እንቅልፍ በመንሳት፣ ውይይቶቻችንንና መደማመጣችንን በመቀነስ በአጠቃላይ የሰዎችን የአኗኗርን ሁኔታ የተረበሸ እንዲሆን እንደሚያደርጉ ኮሚሽኑ አስታቋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የድምፅ ብክለት ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ይመለከታዋል ከተባሉት ባለድርሻ አካላት ከሚባሉ የንግድና የግንባታ ድርጅቶች፣ የዕምነት ተቋማት፣ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ሰጭዎች የመሣሰሉ አካላት ጋር በከተማና በፌደራል ደረጃ እየተሠራ እንደሚገኝም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012



