ለኮቪድ 19 ተብሎ ይለገስ የነበረው ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ

0
492

ኮቪድ 19 ከገባ ጀምሮ አቅመ ደካማ ተብለው እርዳታ ለሚቀርብላቸው ህብረተሰብ ክፍሎች እየተደረገ ያለው እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ።
ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ በተከሰተ በመጀመርያዎቹ ጊዜያት በህብረተሰቡ ዘንድ ድንጋጤ ተፈጥሮ ስለነበር ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳት ነበር ሲል የአዲስ አበባ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጊዜው ከስራቸው የተቀነሱ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ፤ ድጋፍ እየተደረገ ነበር ሲሉ አዲስ አበባ ከተማ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ሙሉጌታ ደበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚያነሱት አሁን ድጋፉ የቀነሰበት ምክንያት አብዛኛው ሰው ወደ ስራ መመለሱ በአይነትም በገንዘብም ይደረግ የነበረው ድጋፍ አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ ማሽቆልቆል እየታየበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በአይነት አስካሁን ከ345 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ድጋፎች የተሰበሰበ ሲሆን ፤ ሙሉ በሙሉ ተከፋፍሎ አለማለቁንና 55 ሚሊየን የሚገመት ድጋፍ እንዳለ ተናግረዋል። ለዚህም ቅድሚያ ማከፋፈል ላይ ትኩረት ያደረግነው ለመበላሸት ቅርብ የሆኑ የእህል አይነቶችን ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የገንዘብ ሚኒስቴር በአንድ ቋት እርዳታዎች ሁሉ እንዲገቡ ይደረጋል ባለው መሰረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው የሚሉት ሙሉጌታ ምክያቱም የማኅበራዊ ትስስር ፈንድ የሚባል በተቋም ደረጃ የተቋቋመ እንዳለ ገልፀው፤ በንግድ ባንክም በዳሽንም ብቸኛው ቋት ተብሎ በሱ ነው እየገባ ያለው ብለዋል።

እርዳታው ካካተታቸው ውስጥ በኮቪድ ምክንያት ከስራቸው የተገለሉትን ለይተን ፤ በተቋም ደረጃ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ ተረጂ (የደሃ ደሃ ) ተብለው የተለዩትን በቋሚነት እንደሚረዱ ጠቅሰዋል።

የኮሚቴው አባል እንደሚሉት አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፉ በመቀነሱ ምክንያት በዋናነት ሃብት ለማሰባሰብ (ሪሶርስ ሞቢላይዝድ) ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነን ፤ በተጨማሪም የአዲስ አመት መቃረቡን ምክንያት በማድረግ ከጳጉሜ አንድ አስከ ጳጉሜ አምስት (አምስቱን ቀን) ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሰባሰብ እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።

የሚሰበሰበው ሃብት የተቸግሩት እና በዓል መዋያ ለሌላቸው የሚውል እንደመሆኑ በአምስቱ ቀናት በዋናነት በሚሊኒየም አዳራሽ እና በኤካ ኮተቤ ድጋፍ የማሰባሰቡ ስራ ይሰራል ብለዋል። በተጨማሪም የተመረጡ ቦታዎች ጋር በመሄድ ህዝቡ ድጋፉን እንዲጀምር ስራዎች ይሰራሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በኮሚቴው ላይ ስለሚነሳበት ኢ- ፍትሃዊ የስርጭት ሂደት( እርዳታውን የማከፋፈል ሁኔታ) ላነሳችው ጥያቄ ከላይ ጀምሮ ያለ ዝርጋታ በመኖሩና ተረጂዎች አስከ ወረዳ የሚታወቁ በመሆናቸው ምክንያት እንደዛ አይነት ቅሬታ ሰምተው እንደማያውቁ የአዲስ አበባ ከተማ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ሙሉጌታ ደበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በ82ተኛ እትሟ ላይ እንዳወጣችው በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ከፍለ ከተማዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ መንግሥት አቅመ ደካማዎችን ለይቶ በመመዝገብ እርዳታ እንዲደርሰን እንደሚያደርግ ተነግሮን እየጠበቅን ቢሆንም ‹‹በእኛ ስም የሚደረገው ድጎማ ደርሶን አያውቅም ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ አቀረበው ነበር።

ከዛም በተጨማሪ ‹‹በአንዳንድ ወረዳዎች ምሽት ላይ እህሎች ሲወጡ እንታዘባለን እኛ ግን ተጠቅመን አናውቅም›› ብለው መጠቆማቸው የሚታወስ ነው። የአዲስ አበባ አስተዳደር የኮሚውኒኬሽን ዳይሬክተሩን በወቅቱ አዲስ ማለዳ አናግራ የነበረ ሲሆን 450 ሺህ የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍል እንደ ከተማ አስተዳደሩ በደረሳቸው መረጃ ድጋፍ ያስፈልገዋል መባሉንና 60 ሺህ ለሚጠጉ አባወራዎች ተለይተው የከፋ ችግር አለበት የተባለ መሆኑን ገልፀው፤ ‹‹በየወረዳዎች የአቅም ማነስ ያለባቸው ተብለን ብንለይም ድጋፉ በስፋት እየጠሰጠ ባለመሆኑ ለሁሉም ለማከፋፈል ተግዳሮት ሆኖብናል ሲሉ ተናግረው ነበር ።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here