በቀድሞው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እና በአሁኑ አማራ ብልጽግና ስር የሚተዳደረው የልማት ድርጅት ጥረት ኮርፖሬት መለያ ስያሜውንና የመለያ ምልክቱን ለመቀየር በኮርፖሬቱ ቦርድ ወሳኔ ማስተላለፉንና ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡
ኮርፖሬቱ ስያሜውንና መለያ አርማውን ለመቀየር በቦርድ ያጸደቀው በየጊዜው በተለያዩ መድረኮች ህዝቡ ሲያነሳው የነበረውንና ለተለያዩ ትርጓሜዎች ሲጋለጥ የቆየውን የመጠሪያ ስያሜና መለያ ምልክቱን ወካይና ግልጽ ለማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት ጥረት የተቋቋመበትን ዓላማና የሀብቱ ባለቤት የሆነውን የአማራ ክልል ህዝብን የመልማትና የመበልጸግ ፍላጎት መዳረሻን ሊያመላክትና ሊያደርስ የሚያስችል አዲስ ስያሜና ልዩ ምልክት አስፈልጓል ሲሉየጥረት ኮርፖሬት የኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አንተነህ ደምሰው የስያሜውን አላማ አብራርተዋል፡፡
ወደፊት አዲስ የሚሰየመው የጥረት ስያሜና ምልክት የጥረትን ዓላማ፣ ተልዕኮ፣ ራዕይና ዕሴት በሰራተኛውና በህዝቡ ዘንድ በሚገባ በማስረጽ የተቋሙን የማህበራዊ ልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮግራሞችን በፍጥነት ለማሳካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡ በዚህም መሰረት የጥረትን ስያሜና ሎጎ ለመቀየር /ሪብራንድ/ የቀረበው ምክረ ሀሳብ በጥረት ሥራ አመራር ቦርድ ተቀባይነት ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል ፡፡
ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የጥረት ሥራ አመራር ቦርድ ስብሰባ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢና የቦርዱ አባላት የሆኑት የክልሉና የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ምክር ሀሳቡ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ተብሏል፡፡ በውጤቱም የቀረበው ምክረ ሀሳብ በማዳበሪያ ሀሳብ ጎልብቶ የጸደቀ ሲሆን የሪብራንዲንግ(የስያሜና መለያ ቅያሬ) ስራዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው እንዲቀርቡ የሥራ አመራር ቦርዱ ውሳኔ ማስተላለፉ ተመላክቷል፡፡
ኮርፖሬቱ የጀመረው የሪብራንድ ሥራ ሲጠናቀቅ ወይንም እንደ አስፈላጊነቱ ስራው ሲጋመስ ተጨማሪ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል፡፡
ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት የሆነው ጥረት ኮርፖሬት የሚያስተዳራቸው ከ20 ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች በላይ ቢኖሩም በውስጣቸው በነበረው ብልሹ አሰራር ምክኒያት ውጤታማ እንዳልነበሩ ከዚህ ቀደም መገምገሙ የሚታወስ ነው፡፡
ተቋሙን በአዲስ ለማደራጀት ከጥረት ዋና መስሪያ ቤት ጅምሮ በሁሉም ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች ላይ አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሪፎርም ስራና በሰለጠነ ሰው ኃይል የማደራጀት ሥራ ተጀምሯል፡፡
ጥረት የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣በማህበራዊ አገልግሎትና በትራንስፎርሜሽን ትግበራ ላይ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ይስራልም መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
ጥረት ኮርፖሬት በስሩ 26 በስራ ላይ ያሉ እና በሒደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ያሉት ግዙፍ ተቋም ነው:: ኮረፖሬቱ የሚስተዳድራቸው ድርጅቶች አምባሰል የንግድ ስራዎች ድርጅት፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣ ዋሊያ ቆርኪ ፋብሪካ፣ ገንደ ውሃ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ፣ ጎንደር ብቅል ፋብሪካ፣ ጣና ኮሙኒኬሽን የሞባይል መገጣጠሚያ፣ አዞላ ኤሌትሮኒክስ ፋብሪካ፣ ቲ ቲ እንጂኔሪንግ እና ማህበር፣ ላፓልማ ዳይቶማይት ፋብሪካ፣ ጀሪ የተፈጥሮ ምንጭ ውሀ ፋብሪካ፣ ተላጅ የልብስ ስፌት ፋብሪካ፣ የቆቦ ዘለቀ እርሻ መካናይዜሽን፣ የዓሳ ልማት ፕሮጀክት፣ የትመን የጂፕሰምና የጅብሰም ውጤቶች ማምረቻ፣ ማዕድ የምግብ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት፣ ቲአይ ሜታልስ ፈርማንግ፣ የጁ ማርና የማር ውጤቶች ማምረቻ፣ የወተት ሀብት ልማት ማቀነባበሪያና የወተት ዱቄት ማምረቻ፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርት አ.ማ፣ እሸት ስታርችና የስታርች ውጤቶች ማምረቻ ፕሮጀክት፣ ጀርባ ፖኬጂንግ ፕሮጀክትና በለሳ የሎጂስቲክ አ.ማ ናቸው፡፡
የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ አመራር የነበሩት ታደሰ ካሳ (ታደሰ ጥንቅሹ) በድርጅቱ ውስጥ ብልሹ አሰራሮችን ፈጽመዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የዕስር ቅጣት እንደተፈረደባቸውም የሚታወስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012



